በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ በልሳን ስለ መናገር ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ በልሳን ስለ መናገር ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ‘በልሳን መናገር’ የሚለው አገላለጽ፣ አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች በተአምር ያገኙትን ሌላ ቋንቋ የመናገር ችሎታ ያመለክታል፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ሌላ ቋንቋ መናገር የቻሉት ቋንቋውን ሳይማሩ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 10:46 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) በልሳን የሚናገረው ሰው የሚያወራውን ነገር፣ ቋንቋውን የሚያውቁ ሰዎች በቀላሉ መረዳት ይችሉ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:4-8) በልሳን መናገር፣ አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ ለነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አንዱ ነው።—ዕብራውያን 2:4፤ 1 ቆሮንቶስ 12:4, 30

 በልሳን መናገር የተጀመረው የትና መቼ ነው?

 ይህ ተአምር መጀመሪያ የተከናወነው በ33 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም በተከበረው ጴንጤቆስጤ የተባለ የአይሁዳውያን በዓል ላይ ነው። በዚህ ወቅት 120 የሚያህሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንድ ላይ ተሰብስበው ነበር፤ በድንገት “ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”፤ ከዚያም “በተለያዩ ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር።” (የሐዋርያት ሥራ 1:15፤ 2:1-4) “በምድር ዙሪያ ካለ አገር ሁሉ የመጡ” ብዙ ሰዎች በዚህ ጊዜ የተሰበሰቡ ሲሆን “እያንዳንዱም ሰው ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ [ሰማ]።”—የሐዋርያት ሥራ 2:5, 6

 በልሳን መናገር ለምን አስፈለገ?

  1.   ክርስቲያኖች የአምላክ ድጋፍ እንዳላቸው ለማሳየት። ቀደም ባሉት ዘመናት አምላክ እንደ ሙሴ ያሉ ታማኝ ሰዎችን እሱ እንደላካቸው ለማረጋገጥ ተአምራዊ ምልክቶችን የማሳየት ችሎታ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፀአት 4:1-9, 29-31፤ ዘኁልቁ 17:10) በተመሳሳይም አምላክ፣ አዲስ የተቋቋመውን የክርስቲያን ጉባኤ እንደሚደግፍ ለማሳየት በልሳን የመናገር ችሎታን ተጠቅሞበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ልሳን ለአማኞች ሳይሆን አማኝ ላልሆኑት ምልክት ነው።”—1 ቆሮንቶስ 14:22

  2.   ክርስቲያኖች የተሟላ ምሥክርነት እንዲሰጡ ለመርዳት። በጴንጤቆስጤ ዕለት የኢየሱስ ተከታዮችን የሰሙ ሰዎች “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እየሰማናቸው ነው” ብለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:11) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው የዚህ ተአምር ሌላ ዓላማ፣ ክርስቲያኖች ‘በተሟላ ሁኔታ መመሥከር’ እንዲሁም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት” ማድረግ እንዲችሉ መርዳት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 10:42፤ ማቴዎስ 28:19) ደግሞም በጴንጤቆስጤ ዕለት የተከናወነውን ተአምር የተመለከቱና ደቀ መዛሙርቱ የሰጡትን ምሥክርነት የሰሙ ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎች በዚያው ዕለት የክርስቶስ ተከታዮች ሆነዋል።—የሐዋርያት ሥራ 2:41

 በልሳን መናገር ሁልጊዜ የሚቀጥል ነገር ነው?

 አይደለም። በልሳን የመናገር ችሎታን ጨምሮ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ዓላማ ለተወሰነ ጊዜ እንዲያገለግሉ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “የመተንበይ፣ በልሳን የመናገርም ሆነ የእውቀት ስጦታ ይቀራል” ሲል ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 13:8

 በልሳን መናገር ያበቃው መቼ ነው?

 በጥቅሉ ሲታይ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ወደ ሌሎች ክርስቲያኖች የሚያስተላልፉት ሐዋርያት ሲሆኑ በአብዛኛው ይህን የሚያደርጉትም አማኝ በሆኑ ወንድሞቻቸው ላይ እጃቸውን በመጫን ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 8:18፤ 10:44-46) ይህን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከሐዋርያቱ ያገኙት ክርስቲያኖች ግን ይህን ስጦታ ወደ ሌሎች ሰዎች ያስተላለፉ አይመስልም። (የሐዋርያት ሥራ 8:5-7, 14-17) ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ለአንድ ሰው የመንጃ ፈቃድ ሊሰጠው ይችላል፤ ይህ ግለሰብ ግን ለሌላ ሰው የመንጃ ፈቃድ የመስጠት ሕጋዊ መብት የለውም። በልሳን የመናገር ችሎታ ሐዋርያትና ይህን ስጦታ ከእነሱ የተቀበሉት ሰዎች ሲሞቱ ያበቃ ይመስላል።

 በዛሬው ጊዜ በልሳን መናገር ይቻላል?

 ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ ተአምራዊ ስጦታ የሆነው በልሳን የመናገር ችሎታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ አብቅቷል። በዛሬው ጊዜ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ከአምላክ ባገኘው ኃይል በልሳን መናገር እንደሚችል ቢገልጽ ትክክል አይሆንም። a

 እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት በምንድን ነው?

 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ተለይተው የሚታወቁት እርስ በርስ ባላቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:34, 35) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ቢሆን ተለይተው የሚታወቁት ፍቅር በማሳየታቸው መሆኑን አስተምሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:1, 8) ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች “የመንፈስ ፍሬ” ተብለው የሚታወቁትን ባሕርያት እንዲያፈሩ የአምላክ መንፈስ እንደሚረዳቸው ጠቁሟል፤ ከእነዚህ ባሕርያት የመጀመሪያው ፍቅር ነው።—ገላትያ 5:22, 23

aበልሳን መናገር ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት