መጽሐፍ ቅዱስ ‘አንዴ የዳነ ለሁልጊዜው እንደዳነ’ ያስተምራል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ‘አንዴ የዳነ ለሁልጊዜው እንደዳነ’ አያስተምርም። በኢየሱስ ክርስቶስ በማመኑ ምክንያት የዳነ አንድ ሰው እምነቱን ሊያጣ ይችላል፤ በመሆኑም የመዳን ተስፋውንም ያጣል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው እምነቱን እንዳያጣ “ብርቱ ተጋድሎ” ማለትም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ይናገራል። (ይሁዳ 3, 5) ክርስቶስን የተቀበሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ” የሚል ምክር ተሰጥቷቸው ነበር።—ፊልጵስዩስ 2:12
‘አንዴ የዳነ ለሁልጊዜው ድኗል’ የሚለው ትምህርት የተሳሳተ እንደሆነ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው የአምላክን መንግሥት እንዳይወርስ ሊያደርጉት ስለሚችሉ ከባድ ኃጢአቶች ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ገላትያ 5:19-21) አንዴ የዳነ ሰው ለሁልጊዜው የሚድን ከሆነ ግን እንዲህ ያለውን ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈላጊ አይሆንም ነበር። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ መዳን ያገኘ ሰው ከዚህ በፊት ወዳስወገዳቸው የኃጢአት ድርጊቶች ከተመለሰ የመዳን ተስፋውን ሊያጣ እንደሚችል ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ዕብራውያን 10:26 እንዲህ ይላል፦ “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ካገኘን በኋላ ሆን ብለን በኃጢአት ጎዳና ብንመላለስ ለኃጢአታችን የሚቀርብ ሌላ መሥዋዕት አይኖርም።”—ዕብራውያን 6:4-6፤ 2 ጴጥሮስ 2:20-22
ኢየሱስ እምነታችንን እንዳናጣ ጥረት ማድረጋችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳየት አንድ ምሳሌ ተጠቅሟል፤ በዚህ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ ራሱን ከወይን ተክል ተከታዮቹን ደግሞ ከተክሉ ቅርንጫፎች ጋር አመሳስሏቸዋል። አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳላቸው በሚያፈሩት ፍሬ ማለትም በተግባራቸው ያሳዩ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ግን እንደዚያ ማድረጋቸውን አቁመዋል፤ በመሆኑም ‘ፍሬ እንደማያፈራ ቅርንጫፍ ተቆርጠው ይጣላሉ’ ማለትም የመዳን ተስፋቸውን ያጣሉ። (ዮሐንስ 15:1-6) ሐዋርያው ጳውሎስም ተመሳሳይ ምሳሌ የተጠቀመ ሲሆን እምነታቸውን እንደያዙ የማይቀጥሉ ክርስቲያኖች ‘ተቆርጠው እንደሚጣሉ’ ተናግሯል።—ሮም 11:17-22
ክርስቲያኖች ‘ምንጊዜም ነቅተው እንዲጠብቁ’ ታዘዋል። (ማቴዎስ 24:42፤ 25:13) “ከጨለማ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን” በመሥራት አሊያም ደግሞ ኢየሱስ እንዲሠሩ ያዘዛቸውን ነገሮች አሟልተው ባለመሥራት በመንፈሳዊ የሚያንቀላፉ ክርስቲያኖች የመዳን ተስፋቸውን ያጣሉ።—ሮም 13:11-13፤ ራእይ 3:1-3
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መዳን ያገኙ ሰዎች እስከ መጨረሻው ድረስ ታማኝ ሆነው መቀጠል እንዳለባቸው ያሳያሉ። (ማቴዎስ 24:13፤ ዕብራውያን 10:36፤ 12:2, 3፤ ራእይ 2:10) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የእምነት ባልንጀሮቻቸው በእምነታቸው ጸንተው እንደቆሙ በመስማታቸው ተደስተዋል። (1 ተሰሎንቄ 1:2, 3፤ 3 ዮሐንስ 3, 4) እስከ መጨረሻው ባይጸኑም እንኳ የሚድኑ ቢሆን ኖሮ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በታማኝነት መጽናት አስፈላጊ እንደሆነ ይህን ያህል አጥብቆ ማሳሰቡ ምክንያታዊ ይሆን ነበር?
ሐዋርያው ጳውሎስ መዳኑ እንደተረጋገጠ አድርጎ የተናገረው በቅርቡ እንደሚሞት ባወቀ ጊዜ ብቻ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:6-8) ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት ለሥጋዊ ምኞቶቹ እጅ ከሰጠ የመዳን ተስፋውን ሊያጣ እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ በሆነ መንገድ ተቀባይነት እንዳላጣ ሰውነቴን እየጎሰምኩ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 9:27፤ ፊልጵስዩስ 3:12-14