ኢየሱስ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ምሁራን ያምናሉ?
ምሁራን፣ ኢየሱስ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ለማመን የሚያበቃ ጠንካራ ማስረጃ አላቸው። በመጀመሪያውና በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበሩ የታሪክ ምሁራን ስለ ኢየሱስና ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተናገሩትን ሐሳብ በተመለከተ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ በ2002 እትሙ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በጥንት ዘመን፣ የክርስትና ተቃዋሚዎች እንኳ ኢየሱስ በእርግጥ በታሪክ ውስጥ የነበረ ሰው መሆኑን ተጠራጥረው እንደማያውቁ እነዚህ ገለልተኛ የታሪክ ዘገባዎች ያረጋግጣሉ። ሰዎች፣ ኢየሱስ በሕይወት የነበረ ሰው ስለ መሆኑ መከራከር የጀመሩት በ18ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ፣ በ19ኛው መቶ ዘመን እንዲሁም በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው፤ ለዚህም ቢሆን በቂ ምክንያት አልነበራቸውም።”
ጂሰስ ኤንድ አርኪኦሎጂ የተሰኘው መጽሐፍ በ2006 እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ተደማጭነት ካላቸው ምሁራን መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የዮሴፍ ልጅ የሆነ ኢየሱስ የተባለ አይሁዳዊ በአንድ ወቅት በሕይወት መኖሩን አይጠራጠሩም፤ አብዛኞቹ ምሁራን፣ ኢየሱስ ስላከናወናቸው ነገሮችና መሠረታዊ ስለሆኑት ትምህርቶቹ አሁን ብዙ የምናውቀው ነገር እንዳለ ይስማማሉ።”
ኢየሱስ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። የቅድም አያቶቹና የቅርብ ቤተሰቦቹ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። (ማቴዎስ 1:1፤ 13:55) መጽሐፍ ቅዱስ፣ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ታዋቂ ገዥዎችንም ስም ይጠቅሳል። (ሉቃስ 3:1, 2) ምሁራን እነዚህን ዝርዝር ሐሳቦች መሠረት በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ትክክል መሆናቸውን ማረጋገጥ ይችላሉ።