ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ፆታ ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ልጆችን ስለ ፆታ ማስተማር ያለበት ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ኃላፊነት የወላጆች እንደሆነ የሚናገር ሲሆን በርካታ ወላጆች ቀጥሎ የቀረቡት ሐሳቦች በዚህ ረገድ ጠቃሚ እንደሆኑ ተገንዝበዋል፦
አትፈሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነትም ሆነ ስለ ፆታ ብልቶች በግልጽ የሚናገር ሲሆን አምላክ “ልጆች” ጭምር ስለዚህ ጉዳይ መማር እንዳለባቸው ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር ተናግሮ ነበር። (ዘዳግም 31:12፤ ዘሌዋውያን 15:2, 16-19) ልጆቻችሁን ስለ ፆታ በምታስተምሩበት ወቅት ጨዋነት የሚንጸባረቅባቸውና የፆታ ግንኙነትን ወይም የፆታ ብልቶችን አሳፋሪ እንደሆኑ አድርገው እንዲመለከቱ የማያደርጉ ቃላትን መጠቀም ያስፈልጋችኋል።
ትንሽ ትንሽ አስተምሯቸው። ልጆቻችሁ ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲጠጉ ስለ ፆታ ሁሉንም ነገር በአንዴ ከምታዥጎደጉዱባቸው ይልቅ ከልጅነታቸው ጀምሮ፣ በሚረዱት መጠን ትንሽ ትንሽ አስተምሯቸው።—1 ቆሮንቶስ 13:11
የሥነ ምግባር መመሪያዎችን አስተምሯቸው። ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ ሥርዓተ ፆታ ይማሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ማስተማር ያለባቸው የፆታ ብልቶች የትኞቹ እንደሆኑ ብቻ ሳይሆን ከፆታ ጋር በተያያዘ ሊኖራቸው ስለሚገባው ዝንባሌና ምግባር ጭምር ነው።—ምሳሌ 5:1-23
ልጆቻችሁን አዳምጧቸው። ልጆቻችሁ ከፆታ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ሲያነሱ ለመቆጣት ወይም ደግሞ በእነሱ ላይ ለመፍረድ አትቸኩሉ። ከዚህ ይልቅ ‘ለመስማት የፈጠናችሁ ለመናገር ደግሞ የዘገያችሁ’ መሆን ይኖርባችኋል።—ያዕቆብ 1:19
ልጆቻችሁን ከፆታ ጥቃት መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
እውቀት ቅሰሙ። በልጆች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎች ስለሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች እወቁ።—ምሳሌ 18:15፤ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 32 ተመልከቱ።
በልጆቻችሁ ሕይወት ውስጥ ስለሚከናወኑ ነገሮች ለማወቅ ጥረት አድርጉ። አንድ ሰው እምነት የሚጣልበት መሆኑን ሳታረጋግጡ ልጃችሁ አብሮት ጊዜ እንዲያሳልፍ አትፍቀዱ፤ እንዲሁም ልጃችሁ ‘መረን እንዲለቅ’ አትፍቀዱ።—ምሳሌ 29:15
ስለ ታዛዥነት ሚዛናዊ አመለካከት እንዲይዙ አስተምሯቸው። ልጆች ወላጆቻቸውን መታዘዝ ሊማሩ ይገባል። (ቆላስይስ 3:20) ያም ቢሆን ልጃችሁ ትላልቅ ሰዎችን ምንጊዜም መታዘዝ እንዳለበት የምትነግሩት ከሆነ የጥቃት ሰለባ እንዲሆን ልታደርጉ ትችላላችሁ። ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጃቸውን “ማንም ሰው አምላክ የሚጠላውን ነገር እንድታደርግ ቢጠይቅህ ፈቃደኛ መሆን የለብህም” ብለው ሊያስተምሩት ይገባል።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
ጥበቃ ለማድረግ የሚረዱ ቀላል እርምጃዎችን ውሰዱ። እናንተ በሌላችሁበት አንድ ሰው ጥቃት ሊያደርስባቸው ከሞከረ ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ልጆቻችሁን አስተምሯቸው። ሊያጋጥሙ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎችን በሠርቶ ማሳያ መልክ መለማመዳችሁ ልጆቻችሁ “እረፍ! አለዚያ እናገርብሃለሁ!” ብለው ለመናገርና ከዚያ በፍጥነት ሸሽተው ለማምለጥ የሚያስችል ድፍረት ይሰጣቸዋል። “ለልጆቻችሁ ደግማችሁ ደጋግማችሁ” ማሳሰቢያ መስጠት እንዳለባችሁ አትርሱ።—ዘዳግም 6:7 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን