መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል ነው። (ሚክያስ 3:8፤ ሉቃስ 1:35) አምላክ ፈቃዱን ለመፈጸም ሲፈልግ እሱ በመረጠው ነገር ላይ ኃይሉን ያኖራል፤ መንፈሱን የሚልከው በዚህ መንገድ ነው።—መዝሙር 104:30፤ 139:7
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መንፈስ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ሩአህ ሲሆን የግሪክኛው ቃል ደግሞ ንዩማ ነው። እነዚህ ቃላት ብዙውን ጊዜ የተሠራባቸው በሥራ ላይ ያለውን የአምላክ ኃይል ይኸውም መንፈስ ቅዱስን ለማመልከት ነው። (ዘፍጥረት 1:2) ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እነዚህ ቃላት ሌሎች ነገሮችንም ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል፦
እስትንፋስ—ዕንባቆም 2:19፤ ራእይ 13:15
ነፋስ—ዘፍጥረት 8:1፤ ዮሐንስ 3:8
በሕያዋን ፍጥረታት ውስጥ የሚገኘው ወይም ሕይወት እንዲኖራቸው የሚያደርገው ኃይል—ኢዮብ 34:14, 15
የአንድ ሰው ባሕርይ ወይም ጠባይ—ዘኍልቍ 14:24
መንፈሳዊ አካላት (አምላክና መላእክት)—1 ነገሥት 22:21፤ ዮሐንስ 4:24
ሁሉንም የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፤ ሁሉም በሰው ዓይን ሊታዩ ባይችሉም የሚያሳድሩትን ውጤት ግን መመልከት እንችላለን። በተመሳሳይም የአምላክ መንፈስ “ልክ እንደ ነፋስ ሁሉ የማይታይና የማይዳሰስ እንዲሁም ኃይል ያለው ነው።”—አን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ
ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የአምላክ ‘እጅ’ ወይም ‘ጣት’ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። (መዝሙር 8:3፤ 19:1፤ ሉቃስ 11:20፤ ከማቴዎስ 12:28 ጋር አወዳድር) አንድ የእጅ ባለሙያ በእጁ እና በጣቶቹ ተጠቅሞ ሥራውን እንደሚያከናውን ሁሉ አምላክም በመንፈሱ ተጠቅሞ የሚከተሉት ውጤቶች እንዲገኙ አስችሏል፦
ጽንፈ ዓለም—መዝሙር 33:6፤ ኢሳይያስ 66:1, 2
መጽሐፍ ቅዱስ—2 ጴጥሮስ 1:20, 21
የጥንት አገልጋዮቹ የፈጸሟቸው ተአምራትና በቅንዓት ያከናወኑት የስብከት ሥራ—ሉቃስ 4:18፤ የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ 1 ቆሮንቶስ 12:4-11
እሱን የሚታዘዙ ሰዎች የሚያሳዩዋቸው ግሩም ባሕርያት—ገላትያ 5:22, 23
መንፈስ ቅዱስ አካል አይደለም
መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የአምላክ ‘እጅ፣’ ‘ጣት’ ወይም “እስትንፋስ” ተደርጎ መገለጹ አካል እንዳልሆነ ይጠቁማል። (ዘፀአት 15:8, 10) የአንድ የእጅ ባለሙያ እጆች ከአንጎሉ ወይም ከሰውነቱ ተነጥለው ብቻቸውን እንደማይሠሩ ሁሉ መንፈስ ቅዱስም መንቀሳቀስ የሚችለው በአምላክ አመራር ብቻ ነው። (ሉቃስ 11:13) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን መንፈስ ከውኃ ጋር የሚያነጻጽረው ሲሆን እንደ እምነትና እውቀት ካሉ ነገሮች ጋር ተያይዞ የተጠቀሰበት ጊዜም አለ። እነዚህ ሁሉ ንጽጽሮች መንፈስ ቅዱስ አካል እንዳልሆነ ይጠቁማሉ።—ኢሳይያስ 44:3፤ የሐዋርያት ሥራ 6:5፤ 2 ቆሮንቶስ 6:6
የአብ ስም ይሖዋ፣ የወልድ ስም ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል፤ ይሁንና መንፈስ ቅዱስ ስም እንዳለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የትም ቦታ አልተጠቀሰም። (ኢሳይያስ 42:8 NW፤ ሉቃስ 1:31) ሰማዕት የሆነው ክርስቲያኑ እስጢፋኖስ በሰማይ ላይ ያለውን ሁኔታ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በራእይ በተመለከተበት ወቅት ሁለት እንጂ ሦስት አካላትን አላየም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ወደ ሰማይ ሲመለከት የአምላክን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ ቆሞ አየ።” (የሐዋርያት ሥራ 7:55) መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነገሮችን ለማከናወን የሚጠቀምበት ኃይል እንደመሆኑ መጠን እስጢፋኖስ ራእዩን እንዲመለከት ያስቻለው ይኸው መንፈስ ነው።
መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ የሚነገሩ የተሳሳቱ እምነቶች
የተሳሳተ እምነት፦ “መንፈስ ቅዱስ” አካል ያለው ከመሆኑም በላይ የሥላሴ ክፍል ነው፤ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ በ1 ዮሐንስ 5:7, 8 ላይ ያለው ሐሳብ ይህን ያሳያል።
እውነታው፦ በ1879 ትርጉም ላይ 1 ዮሐንስ 5:7, 8 የሚከተለውን ሐሳብ ይዟል፦ “በሰማይ የሚመሰክሩ ሦስት ናቸውና እርሳቸውም አብ ቃልም መንፈስ ቅዱስም። . . . ሦስትም አንድም ናቸው።” ይሁንና ተመራማሪዎች ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ሐሳብ እንዳልተናገረ ደርሰውበታል፤ በመሆኑም ሐሳቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አይደለም። ፕሮፌሰር ብሩስ ማኒንግ ሜትስገር እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “እነዚህ ቃላት ውሸት በመሆናቸው የአዲስ ኪዳን ክፍል ሊሆኑ አይገባም።”—ኤ ቴክስቹዋል ኮሜንታሪ ኦን ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት
የተሳሳተ እምነት፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መንፈስ ቅዱስ፣ አካል ያለው ነገር የሚያደርጋቸውን ነገሮች እንዳከናወነ ተደርጎ መገለጹ አካል እንዳለው ያሳያል።
እውነታው፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መንፈስ ቅዱስ አካል ያለው ነገር የሚያደርጋቸውን ነገሮች እንዳደረገ ተደርጎ የተገለጸበት ጊዜ አለ፤ ይሁንና ይህ በራሱ መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል እንዳለው አያሳይም። ጥበብ፣ ሞትና ኃጢአትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አካል ያለው ነገር የሚያደርገውን ነገር እንዳከናወኑ ተደርገው ተገልጸዋል። (ምሳሌ 1:20፤ ሮም 5:17, 21) ለምሳሌ ያህል፣ ጥበብ “ሥራ” እንደምትሠራ እና ‘ልጆች’ እንዳሏት ተገልጿል፤ ኃጢአት ደግሞ እንደሚያታልል፣ እንደሚገድልና የመጎምጀት ፍላጎት እንደሚፈጥር ተደርጎ ተገልጿል።—ማቴዎስ 11:19፤ ሉቃስ 7:35፤ ሮም 7:8, 11
በተመሳሳይም ሐዋርያው ዮሐንስ እንደጻፈው ኢየሱስ፣ መንፈስ ቅዱስን ‘ረዳት’ ብሎ የጠራው ከመሆኑም ሌላ ይህ ረዳት አሳማኝ ማስረጃ የሚያቀርብ፣ የሚመራ፣ የሚናገር፣ የሚሰማ፣ የሚያሳውቅ፣ የሚያከብርና የሚወስድ ወይም የሚቀበል እንደሆነም ተናግሯል። (ዮሐንስ 16:7-15) ዮሐንስ በሌላ ጥቅስ ላይ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር የተጠቀመው ንዩማ የሚለው ግሪክኛ ቃል ፆታ አመልካች የሌለውና ለግዑዝ ነገር የሚያገለግል ቃል መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።—ዮሐንስ 14:16, 17
የተሳሳተ እምነት፦ ሰው የሚጠመቀው በመንፈስ ቅዱስ ስም መሆኑ መንፈስ ቅዱስ አካል እንደሆነ ያሳያል።
እውነታው፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ስም” የሚለው ቃል ሥልጣንን ወይም ቦታን ለማመልከት የተሠራበት ጊዜ አለ። (ዘዳግም 18:5, 19-22፤ አስቴር 8:10) ለምሳሌ ያህል፣ “በሕግ ስም” የሚል የተለመደ አባባል አለ፤ ይህ አባባል ሕግ አንድ ዓይነት አካል እንደሆነ የሚጠቁም አይደለም። አንድ ሰው “በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቁ መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም በማድረግ በኩል ያለው ሥልጣንና ድርሻ አምኖ መቀበሉን የሚያሳይ ነው።—ማቴዎስ 28:19
የተሳሳተ እምነት፦ የኢየሱስ ሐዋርያትና ሌሎች የጥንት ክርስቲያኖች፣ መንፈስ ቅዱስ አካል እንደሆነ ያምኑ ነበር።
እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ታሪክ ይህን ሐሳብ አይደግፍም። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ መለኮታዊ አካል እንደሆነ . . . የሚገልጸው ሐሳብ የመጣው በ381 ዓ.ም. ከተካሄደው የቁስጥንጥንያ ጉባኤ በኋላ ነው።” ይህም የሆነው የመጨረሻው ሐዋርያ ከሞተ ከ250 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ነው።