በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተፈጥሮ አደጋዎች ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተፈጥሮ አደጋዎች ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚያመጣው አምላክ አይደለም፤ እንዲያውም አምላክ በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ያስባል። የአምላክ መንግሥት ከሚያስወግዳቸው ችግሮች መካከል የተፈጥሮ አደጋዎች ይገኙበታል። እስከዚያ ድረስ ግን አምላክ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ማጽናኛ ይሰጣል።—2 ቆሮንቶስ 1:3

 የተፈጥሮ አደጋዎች የአምላክ ቁጣ እንዳልሆኑ እንዴት እናውቃለን?

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሰዎችን ለማጥፋት የተፈጥሮ ኃይሎችን የተጠቀመባቸው ጊዜያት እንዳሉ ይናገራል፤ ያም ሆኖ የተፈጥሮ አደጋዎች ከዚህ የተለዩ ናቸው።

  •   የተፈጥሮ አደጋዎች በሁሉም ዓይነት ሰዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። በአንጻሩ ግን አምላክ የተፈጥሮ ኃይሎችን ተጠቅሞ ያጠፋው ክፉ ሰዎችን ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ በጥንት ዘመን ሰዶምንና ገሞራን ሲያጠፋ ጻድቅ ሰው የነበረውን ሎጥንና ሁለት ልጆቹን አድኗቸዋል። (ዘፍጥረት 19:29, 30) አምላክ በወቅቱ የነበሩትን ሰዎች ልብ በማንበብ ክፉ ሰዎችን ብቻ መርጦ አጥፍቷል።—ዘፍጥረት 18:23-32፤ 1 ሳሙኤል 16:7

  •   የተፈጥሮ አደጋዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰቱት ያለምንም ማስጠንቀቂያ ነው። በአንጻሩ ግን አምላክ የተፈጥሮ ኃይሎችን ተጠቅሞ ሰዎችን ከማጥፋቱ በፊት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ማስጠንቀቂያውን የሰሙ ሰዎች ከጥፋቱ መትረፍ ይችሉ ነበር።—ዘፍጥረት 7:1-5፤ ማቴዎስ 24:38, 39

  •   የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲከሰቱ ሰዎችም አስተዋጽኦ አድርገዋል። እንዴት? ሥነ ምህዳሩን በማበላሸት እንዲሁም ለምድር መናወጥ፣ ለጎርፍና ለከባድ የአየር ሁኔታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በመገንባት ነው። (ራእይ 11:18) ሰዎች ባደረጉት ነገር ምክንያት ለመጣው ችግር አምላክ ተጠያቂ አይደለም።—ምሳሌ 19:3

 የተፈጥሮ አደጋዎች የመጨረሻው ዘመን ምልክት ናቸው?

 አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ወይም “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ የተፈጥሮ አደጋዎች እንደሚከሰቱ ይናገራል። (ማቴዎስ 24:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) ለምሳሌ ኢየሱስ ዘመናችንን አስመልክቶ ሲናገር “በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:7) በቅርቡ አምላክ የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ መከራና ሥቃይ የሚያስከትሉብንን ነገሮች በሙሉ ከምድር ላይ ጠራርጎ ያስወግዳል።—ራእይ 21:3, 4

 አምላክ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የሚረዳው እንዴት ነው?

  •   አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያጽናናቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እንደሚያስብልንና መከራ ሲደርስብን እንደሚያዝን ይናገራል። (ኢሳይያስ 63:9፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7) በተጨማሪም የተፈጥሮ አደጋዎች የማይኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል።—“ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች” የሚለውን ተመልከት።

  •   አምላክ በአገልጋዮቹ አማካኝነት ይረዳቸዋል። አምላክ በምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹ የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ ይፈልጋል። ኢየሱስ “ልባቸው የተሰበረውን” እና “የሚያለቅሱትን” እንደሚያጽናና መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 61:1, 2) የአምላክ አገልጋዮችም እንደዚያው ለማድረግ ይጥራሉ።—ዮሐንስ 13:15

     በተጨማሪም አምላክ አገልጋዮቹን ተጠቅሞ የተፈጥሮ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ እርዳታ እንዲያገኙ ያደርጋል።—የሐዋርያት ሥራ 11:28-30፤ ገላትያ 6:10

የይሖዋ ምሥክሮች በፖርቶ ሪኮ የተፈጥሮ አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ሲረዱ

 መጽሐፍ ቅዱስ ለተፈጥሮ አደጋ እንድንዘጋጅ ይረዳናል?

 አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለአደጋ ዝግጁነት የተጻፈ መጽሐፍ ባይሆንም በውስጡ ያለው ምክር በዚህ ረገድ ይረዳናል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦

  •   አደጋ ቢከሰት ምን እንደምታደርጉ ተዘጋጁ። መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) አደጋ ቢከሰት ምን እንደምናደርግ አሰቀድመን መዘጋጀታችን ጠቃሚ ነው። እንዲህ ያለው ዝግጅት ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠር ብድግ አድርገነው ልንወጣ የምንችል መሠረታዊ ነገሮችን የያዘ ቦርሳ ማዘጋጀትን እንዲሁም አደጋ ሲከሰት ቤተሰባችን የት እንደሚገናኝ መለማመድን ሊጨምር ይችላል።

  •   ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለሕይወታችሁ ዋጋ ስጡ። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለምና፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8) ከአደጋ በሕይወት ለመትረፍ ስንል ቤታችንንም ሆነ ንብረታችንን ትተን ለመሄድ ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል። ሕይወታችን ከየትኛውም ቁሳዊ ነገር እንደሚበልጥ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው።—ማቴዎስ 6:25