ክርስቲያኖች የወሊድ መከላከያ መጠቀማቸው ስህተት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ልጆች እንዲወልዱም ሆነ እንዳይወልዱ አላዘዘም። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ እንዲህ ዓይነት መመሪያ አልሰጡም። መጽሐፍ ቅዱስ እርግዝናን መከላከልን አንድም ቦታ ላይ አያወግዝም። “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን” የሚለው በሮም 14:12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሐሳብ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይሠራል።
በመሆኑም ባለትዳሮች ልጆች ለመውለድ ወይም ላለመውለድ የመወሰን ነፃነት አላቸው። ከዚህም ሌላ ስንት ልጆች እንደሚኖሯቸውና መቼ እንደሚወልዱ መወሰን ይችላሉ። አንድ ባልና ሚስት ፅንስን የማያስወርዱ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን ለመጠቀም ከመረጡ ይህ የራሳቸው ውሳኔና ኃላፊነት ነው። ማንም ሰው ሊፈርድባቸው አይገባም።—ሮም 14:4, 10-13