የወጣቶች ጥያቄ
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
ኢሌን የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፎሎወሮች እንዳሏቸው ሳይ ‘ዋው! በጣም ታዋቂ ናቸው!’ ብዬ አሰብኩ። እውነቱን ለመናገር ትንሽ ቀንቼባቸው ነበር።”
አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ፣ ይህ ርዕስ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ ለመሆን መጣጣር ከሚያስከትለው አደጋ እንድትጠበቅ ይረዳሃል።
ምን አደጋዎች አሉት?
መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 22:1 ላይ “መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይመረጣል” ይላል። ስለዚህ ጥሩ ስም ለማትረፍ፣ አልፎ ተርፎም ተወዳጅ ለመሆን መፈለግ ምንም ችግር የለውም።
አንዳንድ ጊዜ ግን ተቀባይነት ለማግኘት ያለን ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ታዋቂ ካልሆንን ደስታ እንደማናገኝ ሊሰማን ይችላል። ታዲያ ይህ ስሜት አደጋ ሊኖረው ይችላል? የ16 ዓመቷ ኦንያ አደጋ እንዳለው ይሰማታል፦
“ሰዎች ታዋቂ ለመሆን ሲሉ ብቻ የማይሆን ነገር ሲያደርጉ አይቻለሁ፤ ለምሳሌ በትምህርት ቤታችን ከአንደኛ ፎቅ ላይ የዘለሉ ልጆች አሉ።”
አንዳንድ ወጣቶች የእኩዮቻቸውን ትኩረት ለመሳብ ሲሉ አደገኛ የሆኑ የሞኝነት ድርጊቶችን ሲፈጽሙ በቪዲዮ ተቀርጸው ኢንተርኔት ላይ ይለጥፋሉ። ለምሳሌ አንዳንድ ወጣቶች የልብስ ማጠቢያ ሳሙና ሲበሉ ተቀርጸው ኢንተርኔት ላይ ቪዲዮውን ለቀዋል፤ እንዲህ ያለውን መርዛማ ነገር መብላት ማንም ሰው ሊያደርገው የማይገባ ነገር ነው!
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የምትሠሩትን ነገር ለዝና ስትሉ አትሥሩ።”—ፊልጵስዩስ 2:3 ሕያው ቃል
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ መሆን ለአንተ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
የእኩዮችህን ትኩረት ወይም አድናቆት ለማትረፍ ስትል ጤናህን ወይም ሕይወትህን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ታደርጋለህ?
“ታዋቂ መስለው ይታያሉ”
ታዋቂ ለመሆን ሲሉ አደገኛ ነገር የሚያደርጉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። የ22 ዓመቷ ኤሪካ እንደገለጸችው ሌላ ዘዴ የሚጠቀሙ ሰዎችም አሉ፦
“በሕይወታቸው ውስጥ የተከናወኑ ነገሮችን በሙሉ በየጊዜው የሚለጥፉ ሰዎች ሁልጊዜ አብረዋቸው የሚዝናኑ ብዙ ጓደኞች ያሏቸው ይመስላሉ። በዚህ መልኩ ታዋቂ መስለው ይታያሉ።”
የ15 ዓመቷ ካራ አንዳንድ ሰዎች ታዋቂ መስለው ለመታየት ሲሉ እንደሚዋሹ ተናግራለች፦
“አንዳንድ ሰዎች ፓርቲ ላይ እንደነበሩ የሚያስመስል ፎቶ ይለጥፋሉ፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከቤታቸውም አልወጡም።”
የ22 ዓመቱ ማቲው እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳደረገ ሳይሸሽግ ተናግሯል፦
“አንድ ፎቶ ለጠፍኩና ቦታው የኤቨረስት ተራራ እንደሆነ ጻፍኩ፤ እኔ ግን እስያ ሄጄ እንኳ አላውቅም!”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦
ማኅበራዊ ሚዲያ የምትጠቀም ከሆነ ይበልጥ ታዋቂ ለመሆን ስትል ትዋሻለህ?
የምትለጥፋቸው ፎቶግራፎችና የምትጽፋቸው ሐሳቦች ማንነትህንና የምታምንበትን ነገር የሚወክሉ ናቸው?
“ፎሎወር” እና “ላይክ” ማግኘት ምን ያህል ቦታ ሊሰጠው ይገባል?
ብዙ ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ ለመሆን ቁልፉ በጣም ብዙ ፎሎወርና ላይክ ማግኘት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ማቲውም እንደዚያ ይሰማው እንደነበር ተናግሯል፦
“‘ስንት ፎሎወር አለህ?’ ወይም ‘በአንድ ፖስት እስከ ስንት ላይክ አግኝተህ ታውቃለህ?’ ብዬ ሰዎችን እጠይቃለሁ። የፎሎወሮቼን ብዛት ለማሳደግ ስል የማላውቃቸውን ሰዎች ፎሎው አደርግ ነበር፤ እነሱም መልሰው ፎሎው እንዲያደርጉኝ አስቤ ማለት ነው። ታዋቂ የመሆን ጥም አደረብኝ፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ደግሞ ይህን ጥሜን አባባሰው።”
የ25 ዓመቷ ማሪያ እንደገለጸችው አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት የተመካው ‘ምን ያህል ፎሎወርና ላይክ አለኝ?’ በሚለው ላይ ነው፦
“አንዲት ልጅ የለጠፈችው ሰልፊ ብዙ ላይክ ካላገኘ አስቀያሚ እንደሆነች ይሰማታል። ይሄ የተሳሳተ ድምዳሜ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ግን በዚያ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች እንደዚያ ይሰማቸዋል። እነዚህ ወጣቶች ሌላ ሰው ሳይሰድባቸው ራሳቸውን እየሰደቡ ነው ሊባል ይችላል።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።”—ገላትያ 5:26
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦
ማኅበራዊ ሚዲያ የምትጠቀም ከሆነ ራስህን ከሌሎች ሰዎች ጋር እንድታወዳድር እንደሚያደርግህ ይሰማሃል?
የሚያሳስብህ ከልባቸው የሚያስቡልህ እውነተኛ ጓደኞች ያሉህ መሆኑ ነው ወይስ የፎሎወሮችህ ብዛት?