የወጣቶች ጥያቄ
መኖር ቢያስጠላኝስ?
“ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ በጭንቀት ከመወጠሬ የተነሳ ውስጤ በእሳት የሚጋይ ያህል ሆኖ ይሰማኝ ነበር። በዚያ ወቅት ራሴን ስለማጥፋት አስብ ነበር። እውነቱን ለመናገር መሞት ፈልጌ አይደለም። የፈለግኩት ከሥቃዬ መገላገል ነበር።”—ጆናታን፣ 17
በ14,000 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት ከ5ቱ 1ዱ ባለፈው ዓመት ውስጥ ራሱን ስለማጥፋት አስቦ እንደነበር ተናግሯል። a አንተስ መኖር ቢያስጠላህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
ታገሥ። እንዲህ ዓይነት ስሜት ሲመጣብህ በችኮላ እርምጃ ላለመውሰድ ለራስህ ቃል ግባ። ያጋጠሙህ ችግሮች ምንም መፍትሔ የሌላቸው መስለው ይታዩህ ይሆናል። ሆኖም ችግሮችህን ለመቋቋም የሚረዳህ መላ አይጠፋም።
መውጫ ቀዳዳ የሌለው ሁኔታ ውስጥ እንደገባህ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለው ስሜት ከእውነታው የራቀ ሊሆን ይችላል። ያጋጠሙህን ችግሮች ለመቋቋም የሚረዱ መፍትሔዎች መኖራቸው አይቀርም። ተገቢውን እርዳታ ማግኘት ብትችል መፍትሔው እጅህ ላይ ሊሆን ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በየአቅጣጫው ብንደቆስም መፈናፈኛ አናጣም፤ ግራ ብንጋባም መውጫ ቀዳዳ አናጣም።”—2 ቆሮንቶስ 4:8
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ራስህን የማጥፋት ሐሳብ በተደጋጋሚ የሚመጣብህ ወይም በጣም የሚያስቸግርህ ከሆነ እርዳታ ለማግኘት ሞክር፤ ምናልባትም ራሳቸውን የማጥፋት ሐሳብ ያላቸውን ሰዎች የሚረዱ ተቋማትን ማማከር ትችላለህ። እነዚህ ተቋማት እርዳታ ለመስጠት የሠለጠኑ ባለሙያዎች አሏቸው፤ ደግሞም ሊረዱህ ዝግጁ ናቸው።
ስሜትህን ለሌላ ሰው ተናገር። ስለ አንተ በጥልቅ የሚያስቡና ሊረዱህ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል ጓደኞችህና የቤተሰብህ አባላት ይገኙበታል። ሆኖም ስሜትህን ካልነገርካቸው ያለህበትን ሁኔታ እንዴት ማወቅ ይችላሉ?
አንዳንድ ሰዎች አጥርተው ለማየት መነጽር ያስፈልጋቸዋል። ጓደኛም ልክ እንደ መነጽር ሊሆን ይችላል፤ ስላጋጠሙህ ችግሮች ተገቢው እይታ እንዲኖርህና በሕይወት የመቀጠል ፍላጎትህ እንዲቀሰቀስ ሊረዳህ ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነተኛ ወዳጅ . . . ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ለጓደኛህ ጉዳዩን ለማንሳት እንዲህ ልትለው ትችላለህ፦ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሮዬ እየመጣ እያስቸገረኝ ነው። ላዋራህ ፈልጌ ነበር፤ ጊዜ ይኖርሃል?” ወይም ደግሞ “የሆነ ችግር ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛል፤ ልትረዳኝ የምትችል ይመስልሃል?” ልትለው ትችላለህ።
ሐኪም ጋ ሂድ። እንደ መንፈስ ጭንቀት ያሉ የጤና ችግሮች ሰዎች ሕይወት እንዲያስጠላቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። ጥሩው ነገር ግን እነዚህ የጤና ችግሮች መታከም ይችላሉ።
ጉንፋን የምግብ ፍላጎትህን እንደሚያጠፋው ሁሉ የመንፈስ ጭንቀትም የመኖር ፍላጎትህ እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ለሁለቱም የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይቻላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።”—ማቴዎስ 9:12
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በቂ እንቅልፍ ተኛ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ ለመመገብ ጥረት አድርግ። ጤንነትህ ስለ ሕይወት ባለህ አመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።
ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን “ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል” ይላል። (1 ዮሐንስ 3:20) ታዲያ ለምን አሁኑኑ ወደ እሱ አትጸልይም? ይሖዋ የሚለውን ስሙን ተጠቅመህ የልብህን አውጥተህ ንገረው።
አንዳንድ ሸክሞችን ብቻህን ልትሸከማቸው አትችልም። ፈጣሪህ ይሖዋ ሊረዳህ ፈቃደኛ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ለይሖዋ ስለ ችግሮችህ ከመናገር ባለፈ በዛሬው ዕለት ያደረገልህን ቢያንስ አንድ ነገር አንስተህ አመስግነው። (ቆላስይስ 3:15) አመስጋኝነት ለሕይወት ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል።
በሕይወት መኖር ዋጋ እንደሌለው የሚሰማህ ከሆነ የሌሎችን እርዳታ ጠይቅ። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ጆናታን ያደረገው ልክ እንደዚህ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “ከወላጆቼ ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ ማውራትና የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስፈልጎኝ ነበር። አሁን በጣም ጥሩ ስሜት ይሰማኛል። ችግሮች አሁንም ያጋጥሙኛል፤ ራሴን ለማጥፋት ግን አላስብም።”
a ይህን ጥናት በ2019 ያካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ነው።