የወጣቶች ጥያቄ
በቂ እንቅልፍ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
በሒሳብ ፈተና ብትወድቅ መፍትሔው በርትቶ ማጥናት እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። በአንድ ዓይነት የስፖርት ውድድር ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ሳታደርግ ብትቀር መፍትሔው ተጨማሪ ልምምድ ማድረግ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከሁለቱም ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ መፍትሔው በቂ እንቅልፍ ማግኘት ሊሆን ይችላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
እንቅልፍ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች ሌሊት ከስምንት እስከ አሥር ሰዓት ያህል እንቅልፍ ማግኘት እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ። በቂ እንቅልፍ ማግኘት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
እንቅልፍ የማሰብ ችሎታን ያጎለብታል። እንቅልፍ “የአእምሮ ምግብ” ተብሎ ተጠርቷል። በትምህርት ቤት የተሻለ ውጤት ለማምጣት፣ በስፖርት ጥሩ እንቅስቃሴ ለማድረግና መፍትሔ የመፈለግ ችሎታን ለማዳበር ይረዳል።
እንቅልፍ በስሜትና በአመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በቂ እንቅልፍ የማያገኙ ሰዎች የስሜት መዋዠቅ ሊያጋጥማቸው፣ ሊያዝኑ ወይም በመንፈስ ጭንቀት ሊዋጡ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ለመግባባት ሊቸገሩ ይችላሉ።
እንቅልፍ አደጋን ለመከላከል ይረዳል። በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከ16 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ አሽከርካሪዎች ከ40 እስከ 59 ዓመት ዕድሜ ላይ ከሚገኙ አሽከርካሪዎች ጋር ሲነጻጸሩ “ከግጭት በፊት አንቀላፍተው የሚሆንበት አጋጣሚ በእጥፍ ገደማ ይበልጣል።”
እንቅልፍ ለተሻለ ጤንነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንቅልፍ ሰውነታችን ሕዋሳቱን፣ ሕብረ ሕዋሳቱንና የደም ቧንቧዎቹን እንዲያድስና እንዲጠግን ይረዳል። በተጨማሪም ጥሩ እንቅልፍ መተኛት ከልክ ባለፈ ውፍረት፣ በስኳር በሽታና በደም ግፊት የመጠቃት አጋጣሚን ይቀንሳል።
እንቅልፍ እየነሳህ ያለው ምንድን ነው?
እንቅልፍ ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ጥቅሞች ቢኖሩትም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በቂ እንቅልፍ እያገኙ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ የ16 ዓመቷ ኢሌን እንዲህ ብላለች፦
“አስተማሪያችን ስንት ሰዓት ላይ እንደተኛን የክፍሉን ተማሪዎች በሙሉ ጠየቀች። አብዛኞቹ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ገደማ ላይ እንደተኙ ተናገሩ። ሌሎቹ ደግሞ ከንጋቱ 11 ሰዓት አካባቢ እንደተኙ ገለጹ። ከምሽቱ 3:30 ላይ እንደተኛ የተናገረው አንድ ተማሪ ብቻ ነበር።”
እንቅልፍህን እያስተጓጎለብህ ያለው ምን ሊሆን ይችላል?
ማኅበራዊ ሕይወት። “ምንም ሳይታወቀኝ የማመሽበት ጊዜ አለ፤ በተለይ ከጓደኞቼ ጋር በምሆንበት ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥመኛል።”—ፓሜላ
ልታከናውናቸው የሚገቡ ሥራዎች። “እንቅልፍ እወዳለሁ፤ ግን ብዙ የምሠራቸው ነገሮች ስላሉ በቂ እንቅልፍ ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንብኛል።”—አና
ቴክኖሎጂ። “እንዳልተኛ እንቅፋት የሚሆንብኝ ዋነኛው ነገር ስልኬ ነው። አልጋ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ስልኬን ለማየት እፈተናለሁ።”—አኒሳ
በቂ እንቅልፍ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
ስለ እንቅልፍ ያለህን አመለካከት ገምግም። መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል” ይላል። (መክብብ 4:6) እንቅልፍ ቅንጦት ሳይሆን ለሕይወት የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። በቂ እንቅልፍ ካላገኘህ ሥራህን በጥራት ለማከናወን ትቸገራለህ፤ ሌላው ቀርቶ ከመዝናኛ የምታገኘው ደስታም ይቀንሳል!
በቂ እንቅልፍ እንዳታገኝ እንቅፋት እየሆነብህ ያለው ትልቁ ነገር ምን እንደሆነ ለይተህ እወቅ። ለምሳሌ ከጓደኞችህ ጋር ብዙ ታመሻለህ? የቤት ሥራ ወይም ሌሎች ሥራዎች ይበዙብሃል? ተንቀሳቃሽ ስልክህ አምሽተህ እንድትተኛ ወይም ከእንቅልፍህ እንድትነቃ ያደርግሃል?
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ እንቅፋት እየሆነብህ ላለው ነገር መፍትሔ ማበጀት ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ውጤቱ ይክስሃል። ምሳሌ 21:5 “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል” ይላል።
እርግጥ ነው፣ ለአንዱ የሚሠራው ነገር ለሌላው ላይሠራ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች ቀን ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ማሸለብ ማታ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት እንደሚረዳቸው ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ቀን ላይ መተኛት ማታ እንቅልፍ እንደሚከለክላቸው ይናገራሉ። ለአንተ የተሻለው የቱ እንደሆነ ለማወቅ ሞክር። ቀጥሎ የቀረቡትን ምክሮች ጠቃሚ ሆነው ልታገኛቸው ትችላለህ፦
ሰውነትህ ዘና የሚልበት ጊዜ እንዲያገኝ አድርግ። የእንቅልፍ ሰዓትህ ከመድረሱ በፊት ባለው ጊዜ ሰውነትህ ዘና እንዲል ካደረግክ በተሻለ ፍጥነት እንቅልፍ ሊወስድህ ይችላል።
“የቤት ውስጥ ሥራዎቻችሁንም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎቻችሁን ቀደም ብላችሁ መጨረሳችሁ የእንቅልፍ ሰዓታችሁ ላይ እንዳትጨነቁ ይረዳችኋል።”—ማሪያ
ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር ሞክር። ሁኔታዎች እንዲቆጣጠሩህ ከመፍቀድ ይልቅ ፕሮግራምህን በማስተካከል በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ጥረት አድርግ።
“በየቀኑ ቢያንስ የስምንት ሰዓት እንቅልፍ ያስፈልገኛል። ስለዚህ ከሌላው ጊዜ ቀደም ብዬ መነሳት ካለብኝ ስንት ሰዓት ላይ መተኛት እንደሚያስፈልገኝ አሰላለሁ።”—ቪንሰንት
በተመሳሳይ ሰዓት ላይ ለመተኛት ጥረት አድርግ። ሰውነታችን በተፈጥሮ ያገኘው ጊዜ ጠቋሚ ሰዓት አለው፤ ሆኖም ይህ ሰዓት የሚሠራው በሚገባ ከተቃኘ ነው። ባለሙያዎች በየዕለቱ በተመሳሳይ ሰዓት ላይ መተኛትና መነሳት ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። እስቲ ለአንድ ወር ያህል እንዲህ ለማድረግ ሞክር፤ ከዚያም ለውጡን ታየዋለህ።
“ሁሌም በተመሳሳይ ሰዓት ላይ የምትተኙ ከሆነ በቀጣዩ ቀን አእምሯችሁ ንቁ ይሆናል። ይህም በምታከናውኑት በማንኛውም እንቅስቃሴ ይበልጥ ውጤታማ እንድትሆኑ ይረዳችኋል።”—ጃሬድ
በማኅበራዊ ሕይወትህ ላይ ሚዛናዊ ገደብ አብጅ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በልማዳችን ልከኛ እንድንሆን’ ይመክረናል፤ ይህ ደግሞ በትርፍ ጊዜያችን የምናከናውነውንም ነገር ይጨምራል።—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 11
“ምሽት ላይ በሚኖሩኝ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ ማበጀት እንዳለብኝ ተምሬያለሁ። ለመዝናኛ በማውለው ጊዜ ላይ ገደብ ካላበጀሁ የሆነ ነገር መሥዋዕት ማድረጌ አይቀርም፤ በአብዛኛው ደግሞ መሥዋዕት የማደርገው እንቅልፌን ነው!”—ሪቤካ
ስልክህም “ይተኛ”! ከመተኛትህ ቢያንስ ከአንድ ሰዓት በፊት ጀምሮ ኢንተርኔት ከማሰስ ወይም ለጓደኞችህ የጽሑፍ መልእክት ከመላክ ተቆጠብ። እንዲያውም አንዳንድ ባለሙያዎች ከስልክ፣ ከቴሌቪዥን ወይም ከታብሌት የሚወጣው ብርሃን እንቅልፍ እንደሚከለክል ያስጠነቅቃሉ።
“ሰዎች በሚፈልጓችሁ ጊዜ ሁሉ እንድትገኙላቸው ይጠብቃሉ። ሆኖም በቂ እረፍት ማግኘት ከፈለጋችሁ ስልካችሁን ከአጠገባችሁ ማራቅ አለባችሁ።”—ጁሊሳ