የወጣቶች ጥያቄ
ትምህርት ላቋርጥ?
“ትምህርት ያስጠላኛል!” የሚል ስሜት ካለህ ለማቋረጥ ትፈተን ይሆናል። ይህ ርዕስ የተሻሉ አማራጮችን ለማግኘት ይረዳሃል።
አንዳንዶች ትምህርት የሚያቋርጡበት ምክንያት
ባለሙያዎች ከሚጠቅሷቸው የተለመዱ ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፦
ዝቅተኛ ውጤት። ‘የትምህርት ውጤቴ ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ ነው።’
መሰላቸት። ‘ትምህርት ቤት የምማረው ነገር ለሕይወቴ የሚጠቅመኝ አይመስለኝም።’
የኢኮኖሚ ችግር። ‘ቤተሰቤን ለመደገፍ መሥራት አለብኝ።’
መዘዙን አስብ
መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ . . . አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) ነጥቡ ምንድን ነው? ትምህርት ለማቋረጥ እያሰብክ ከሆነ በመጀመሪያ ይህ ውሳኔ የሚያስከትልብህን መዘዝ አስብ።
ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦
‘ትምህርት ማቋረጤ ወደፊት ሥራ ለመቀጠር ስሞክር ምን እንቅፋት ይፈጥርብኛል?’
“ወደፊት ሥራ መያዝና ለቤተሰብህ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማቅረብ እንደሚያስፈልግህ አስታውስ። ትምህርት ካቋረጥክ ግን እንዲህ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆንብሃል፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ አሠሪዎች የሚቀጥሩት ቢያንስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቀ ሰው ነው።”—ጁሊያ
‘ትምህርት ማቋረጤ ችግሮችን የመጋፈጥ ችሎታዬን የሚነካው እንዴት ነው?’
“ትምህርት ቤት ለወደፊቱ ሕይወት ያዘጋጅሃል። ወደፊት የምታገኛቸው ሰዎች፣ የሚያጋጥሙህ ፈተናዎችና የምትሠራው ሥራ አሁን በትምህርት ቤት እያጋጠመህ ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው።”—ዳንኤል
‘ትምህርት ማቋረጤ ለሕይወት የሚያስፈልጉኝን መሠረታዊ ችሎታዎች እንዳላዳብር እንቅፋት አይፈጥርብኝም?’
“የምትማረው ነገር ጥቅም አሁን ላይታይህ ይችላል። ግን 23 ዓመት ሞልቶህ ገቢህንና ወጪህን ማቀናነስ ሲኖርብህ ‘እንኳንም ሒሳብ ተማርኩ!’ ትላለህ።”—አና
የተሻለ አማራጭ
ምክር ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ አማካሪዎች ባሉበት . . . ስኬት ይገኛል” ይላል። (ምሳሌ 11:14) የትምህርት ውጤትህ እያሽቆለቆለ ከሆነ ወላጆችህ፣ አስተማሪህ፣ የተማሪዎች አማካሪ ወይም ሌላ የምታምነው አዋቂ ውጤትህን ለማሻሻል የሚረዳ ምክር እንዲሰጥህ ጠይቅ።
“ትምህርት ከከበደህ አስተማሪህን አነጋግር። አንዳንዴ ችግሩ ከአስተማሪህ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል፤ አብዛኛውን ጊዜ ግን ምክር በመጠየቅ ብቻ ውጤትህን ማሻሻል ትችላለህ።”—ኤድዋርድ
አርቀህ አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል” ይላል። (መክብብ 7:8) ትምህርት ስትጨርስ የሚኖርህ እውቀት ከተማርካቸው የትምህርት ዓይነቶች ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፤ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ችሎታዎችም ይኖሩሃል።
“አዋቂ ከሆንክ በኋላ የቤት ሥራ መሥራት ወይም ለፈተና ማጥናት ላይኖርብህ ይችላል። ሆኖም ትምህርት ቤት ሳለህ ውጥረትን የምትቋቋምበትን መንገድ መማርህ ወደፊት ከተመረቅክ በኋላ ለሚያጋጥሙህ ፈተናዎች ያዘጋጅሃል።”—ቬራ
ያሉህን አማራጮች አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “ችኩሎች ሁሉ . . . ለድህነት ይዳረጋሉ” ይላል። (ምሳሌ 21:5) ያለህ ብቸኛ አማራጭ ትምህርት ማቋረጥ እንደሆነ ለመደምደም አትቸኩል። በኢንተርኔት እንዲሁም በምሽት ወይም በርቀት ፕሮግራም አማካኝነት ትምህርትህን መጨረስ ትችል ይሆናል።
“ትምህርት ቤት በርትቶ መሥራትን፣ ችግሮችን መፍታትን እንዲሁም ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራትን ያስተምርሃል። እነዚህ ነገሮች ለወደፊት ሕይወትህም ይጠቅሙሃል። ትምህርትህን ለመጨረስ የቻልከውን ሁሉ ጥረት ማድረግህ አያስቆጭም።”—ቤንጃሚን
ዋናው ነጥብ፦ ትምህርትህን ከጨረስክ አዋቂ ስትሆን የሚኖሩህን ኃላፊነቶች ለመወጣት የተሻለ ብቃት ይኖርሃል።