የወጣቶች ጥያቄ
ወላጆቼ ስላወጧቸው ሕጎች ከእነሱ ጋር መነጋገር የምችለው እንዴት ነው?
“የ15 ዓመት ልጅ እያለሁ የወላጆቼን ሕግ መቀበል ምንም አይከብደኝም ነበር። አሁን ግን 19 ዓመቴ ነው፤ ስለዚህ ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጠኝ እንደሚገባ ይሰማኛል።”—ሲልቪያ
አንተስ እንደ ሲልቪያ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ከወላጆችህ ጋር ስለዚህ ጉዳይ ለመወያየት ይረዳሃል።
ማወቅ የሚኖርብህ ነገር
ወላጆችህ ያወጧቸውን ሕጎች በተመለከተ ከእነሱ ጋር ከመነጋገርህ በፊት የሚከተሉትን ነጥቦች አስብባቸው፦
ሕግ ከሌለ ሁሉ ነገር ይተራመሳል። ብዙ መኪና የሚመላለስበትን መንገድ ወደ አእምሮህ አምጣ። መንገዱ ላይ ምልክት፣ የትራፊክ መብራት ወይም የፍጥነት ገደብ ባይኖር ምን የሚፈጠር ይመስልሃል? እንደ ትራፊክ ሕጎች ሁሉ የቤት ውስጥ ሕጎችም ሥርዓት ለማስፈን ይረዳሉ።
ወላጆችህ ሕግ የሚያወጡት ስለሚያስቡልህ ነው። ወላጆችህ ምንም ሕግ ካላወጡልህ ስለሚደርስብህ ነገር ግድ የላቸውም እንደማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ወላጆች ቢኖሩህ ደስ ይልሃል?
ይህን ታውቅ ነበር? ወላጆችህም የሚመሩባቸው ሕጎች አሉ! ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 2:24ን፣ ዘዳግም 6:6, 7ን፣ ኤፌሶን 6:4ን እና 1 ጢሞቴዎስ 5:8ን ተመልከት።
ይሁንና የወላጆችህ ሕጎች ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆኑ ቢሰማህስ?
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ወላጆችህን ከማነጋገርህ በፊት ቆም ብለህ አስብ። የወላጆችህን ሕጎች በማክበር ረገድ ምን ዓይነት ስም አትርፈሃል? በዚህ ረገድ ጥሩ ስም ካላተረፍክ ወላጆችህ ተጨማሪ ነፃነት እንዲሰጡህ ባትጠይቃቸው ይሻላል። ከዚህ ይልቅ “ወላጆቼ እምነት እንዲጥሉብኝ ምን ላድርግ?” የሚለውን ርዕስ ማንበብህ ይጠቅምሃል።
የወላጆችህን ሕጎች በማክበር ረገድ ጥሩ ስም አትርፈህ ከሆነስ? እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ለእነሱ መናገር የምትፈልገውን ነገር አስቀድመህ ተዘጋጅ። ሐሳብህን ቀደም ብለህ ለማቀናበር መሞከርህ የምታቀርበው ጥያቄ የሚያስኬድ መሆኑን ለመገምገም ይረዳሃል። ቀጥሎም ሁላችሁም ዘና ብላችሁ ስለ ጉዳዩ መነጋገር የምትችሉበትን ጊዜና ቦታ እንዲመርጡ ወላጆችህን ጠይቃቸው። ከዚያም ከወላጆችህ ጋር ስትነጋገር የሚከተሉትን ምክሮች አስታውስ፦
አክብሮት አሳይ። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ቃል . . . ቁጣን ያነሳሳል” ይላል። (ምሳሌ 15:1) ልብ በል፦ ከወላጆችህ ጋር መጨቃጨቅ ወይም ያወጧቸውን ሕጎች መተቸት ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ እንዳይቋጭ ያደርጋል።
“ወላጆቼን ሳከብራቸው እነሱም ያከብሩኛል። እርስ በርስ የምንከባበር ከሆነ ደግሞ ስምምነት ላይ መድረስ አይከብደንም።”—ቢያንካ፣ 19
አዳምጥ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመስማት የፈጠንንና ለመናገር የዘገየን’ እንድንሆን ይመክረናል። (ያዕቆብ 1:19) ከወላጆችህ ጋር እየተወያየህ እንጂ ለእነሱ ንግግር እያቀረብክ እንዳልሆነ አትርሳ።
“እያደግን ስንሄድ ከወላጆቻችን ይበልጥ እንደምናውቅ ሊሰማን ይችላል፤ ግን ይህ ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ነው። የሚሰጡንን ምክር መስማታችን ይጠቅመናል።”—ዴቫን፣ 20
ስሜታቸውን ተረዳ። ራስህን በወላጆችህ ቦታ አስቀምጠህ ጉዳዩን ለማየት ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ” በማለት የሚሰጠውን ምክር በመከተል ለወላጆችህ ፍላጎት ትኩረት ስጥ።—ፊልጵስዩስ 2:4
“ወላጆቼን የምመለከታቸው እንደ ደጋፊ ሳይሆን እንደ ተቃዋሚ አድርጌ ነበር። አሁን ግን፣ እኔ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ለመሆን እየሞከርኩ እንደነበረ ሁሉ እነሱም ጥሩ ወላጅ ለመሆን ይጥሩ እንደነበረ ተረድቻለሁ። ሁሉንም ነገር ያደርጉ የነበረው ስለሚያስቡልኝ ነው።”—ጆሹዋ፣ 21
የመፍትሔ ሐሳብ አቅርብ። ለምሳሌ ወላጆችህ ምሽት ላይ በሚካሄድ አንድ ግብዣ ላይ ለመገኘት ስትጠይቃቸው ከለከሉህ እንበል። ያሳሰባቸው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ሞክር፦ ቅር ያላቸው ግብዣው ምሽት ላይ መካሄዱ ነው? ወይስ ግብዣው ራሱ ነው?
ያሳሰባቸው ምሽት ላይ መካሄዱ ከሆነ ሌላ ሰው አብሮህ እንደሚሄድ ብትነግራቸው ሐሳባቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ?
ያሳሰባቸው ግብዣው ራሱ ከሆነ ደግሞ በግብዣው ላይ እነማን እንደሚገኙና ምን ዓይነት ቁጥጥር እንደሚደረግ ብትነግራቸው ስጋታቸው ይቀንስ ይሆን?
አነጋገርህ አክብሮት የሚንጸባረቅበት ይሁን፤ እንዲሁም ወላጆችህ ሲናገሩ በትዕግሥት አዳምጣቸው። በምትናገረው ነገርም ሆነ በምትናገርበት መንገድ “አባትህንና እናትህን [እንደምታከብር]” አሳይ። (ኤፌሶን 6:2, 3) ታዲያ ይህን ካደረግክ ወላጆችህ ሐሳባቸውን ይቀይራሉ ማለት ነው? ሊሆን ይችላል። ላይሆንም ይችላል። ያም ሆነ ይህ . . .
የወላጆችህን ውሳኔ በአክብሮት ተቀበል። ይህ በጣም አስፈላጊ ሆኖም ብዙ ጊዜ ችላ የሚባል እርምጃ ነው። ወላጆችህ ሐሳብህን ስላልተቀበሉ ከእነሱ ጋር መጨቃጨቅ ብትጀምር በቀጣዩ ጊዜ የምትፈልገውን ነገር ማግኘት ከባድ ይሆንብሃል። በሌላ በኩል ደግሞ ውሳኔያቸውን ካከበርክ ተጨማሪ ነፃነት ለመስጠት ሊነሳሱ ይችላሉ።