የወጣቶች ጥያቄ
ከተጠመቅኩ በኋላ ምን ማድረግ ያስፈልገኛል?—ክፍል 1፦ ጥሩ ልማዶችህን ይዘህ ቀጥል
እንደ ቤት ወይም መኪና ያሉ ንብረቶች ሁልጊዜ ክትትል ይፈልጋሉ። ከአምላክ ጋር የመሠረትከው ወዳጅነትም እንዲሁ ነው። ታዲያ ከተጠመቅክ በኋላም ይህ ወዳጅነት እያደገ እንዲሄድ ምን ማድረግ ትችላለህ?
በዚህ ርዕስ ላይ
የአምላክን ቃል ማጥናትህን ቀጥል
ቁልፍ ጥቅስ፦ “በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጋችሁ [ሂዱ]።”—ቆላስይስ 1:10
ምን ማለት ነው? ከተጠመቅክ በኋላም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብህንና በተማርከው ነገር ላይ ማሰላሰልህን መቀጠል ይኖርብሃል።—መዝሙር 25:4፤ 119:97
ምን ሊያጋጥምህ ይችላል? አንዳንድ ጊዜ ማንበብ አያሰኝህ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ‘በቃ እኔ የንባብ ሰው አይደለሁም’ ብለህ ልትደመድም ትችላለህ።
ምን ማድረግ ትችላለህ? ማወቅ የምትፈልጋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች መርጠህ ምርምር አድርግ። ለአንተ የሚሆንህ የግል ጥናት ፕሮግራም አውጣ፤ ፕሮግራምህ የሚያጨናንቅ ሳይሆን አስደሳች እንዲሆንልህ አድርግ። ግብህ ለይሖዋና ለቃሉ ያለህን ፍቅር ማሳደግ ነው። ይህን ዓላማ ይዘህ ስታጠና ጥናቱ ጠቃሚም አስደሳችም ይሆንልሃል።—መዝሙር 16:11
ጠቃሚ ምክር፦ ከጥናትህ የተሻለ ጥቅም ማግኘት ከፈለግህ ትኩረትህ የማይከፋፈልበት ጸጥ ያለ ቦታ ለማግኘት ሞክር።
ተጨማሪ እገዛ ያስፈልግሃል?
ወደ ይሖዋ መጸለይህን ቀጥል
ቁልፍ ጥቅስ፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:6
ምን ማለት ነው? ከአምላክ ጋር መነጋገር ሁለት ነገሮችን ያካትታል፦ ቃሉን ስናነብ እያዳመጥነው ነው፤ ስንጸልይ ደግሞ ሐሳባችንን እንነግረዋለን። ስትጸልይ የሚያስፈልግህን ነገር አምላክን ልትለምነው ትችላለህ፤ ላገኘሃቸው መልካም ነገሮች እሱን ማመስገንም አትርሳ።
ምን ሊያጋጥምህ ይችላል? አንዳንዴ ጸሎትህ ድግግሞሽ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ‘ይሖዋ በእርግጥ እየሰማኝ ነው?’ ወይም ‘እኔን መስማትስ ይፈልጋል?’ የሚለውን እንኳ ልትጠራጠር ትችላለህ።—መዝሙር 10:1
ምን ማድረግ ትችላለህ? በቀኑ ውሎህ፣ ጸሎትህ ላይ ልትጠቅሳቸው የምትችላቸውን ነገሮች አስብ። አንድ ሐሳብ ሲመጣልህ፣ ስለዚያ ጉዳይ ረዘም ያለ ጸሎት ለማቅረብ በወቅቱ ሁኔታህ አይመችህ ይሆናል፤ ሆኖም በኋላ ላይ ስትችል ጸሎትህ ላይ እንድትጠቅሰው ጉዳዩን በአእምሮህ ያዘው። ስለ ራስህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ስለ ሌሎችም ጸልይ።—ፊልጵስዩስ 2:4
ጠቃሚ ምክር፦ ጸሎትህ ድግግሞሽ እየሆነ እንደመጣ ካስተዋልክ ይህንኑ ጉዳይ ራሱ አንስተህ ወደ ይሖዋ መጸለይ ትችላለህ። ይሖዋ የሚያሳስቡህን ነገሮች ሁሉ እንድትነግረው ይፈልጋል፤ ከጸሎትህ ጋር የተያያዙትንም ጭምር።—1 ዮሐንስ 5:14
ተጨማሪ እገዛ ያስፈልግሃል?
አንብብ
አውርድ
ስለ እምነትህ ለሌሎች መናገርህን ቀጥል
ቁልፍ ጥቅስ፦ “ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ። . . . ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህና።”—1 ጢሞቴዎስ 4:16
ምን ማለት ነው? እምነትህን ለሌሎች ስታካፍል የአንተም እምነት ይጠናከራል። በዚህም የተነሳ የሚሰሙህን ሰዎች ብቻ ሳይሆን የራስህንም ሕይወት ታድናለህ።
ምን ሊያጋጥምህ ይችላል? አንዳንድ ጊዜ ስለ እምነትህ ለሌሎች መናገር ላያሰኝህ ይችላል። እንዲያውም ሊያስፈራህም ይችላል፤ በተለይ በትምህርት ቤት።
ምን ማድረግ ትችላለህ? እንደ ፍርሃት ያሉ አሉታዊ ስሜቶች ድርጊትህን እንዳይቆጣጠሩት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ሐዋርያው ጳውሎስ የስብከቱን ሥራ በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሳልወድ ባደርገውም እንኳ የመጋቢነት አደራ ተጥሎብኛል።”—1 ቆሮንቶስ 9:16, 17
ጠቃሚ ምክር፦ ወላጆችህን አስፈቅደህ ሊያሠለጥንህ የሚችል ሰው ፈልግ፤ በአገልግሎቱ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አንድ የእምነት አጋርህ እንዲህ ዓይነት አሠልጣኝ ሊሆንልህ ይችላል።—ምሳሌ 27:17
ተጨማሪ እገዛ ያስፈልግሃል?
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህን ቀጥል
ቁልፍ ጥቅስ፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ . . . መሰብሰባችንን ቸል አንበል።”—ዕብራውያን 10:24, 25
ምን ማለት ነው? ስብሰባዎች ላይ የምንገኝበት ዋነኛው ምክንያት ይሖዋን ማምለክ ነው። ሆኖም በስብሰባዎች ላይ መገኘት ሌሎች ሁለት ጥቅሞችም አሉት። አንደኛ፣ ከእምነት አጋሮችህ ማበረታቻ ታገኛለህ። ሁለተኛ፣ በስብሰባዎች ላይ ስትገኝና ተሳትፎ ስታደርግ እነሱም ይበረታታሉ።—ሮም 1:11, 12
ምን ሊያጋጥምህ ይችላል? ስብሰባ ላይ ሆነህ ትኩረትህ ሊከፋፈል ይችላል፤ ይህ ደግሞ የሚተላለፈው ጠቃሚ ትምህርት እንዲያመልጥህ ያደርጋል። የትምህርት ቤት ሥራ ወይም ሌሎች ጉዳዮች ሲያጋጥሙህ ከስብሰባ ለመቅረት ትፈተን ይሆናል፤ ወይም ከስብሰባ መቅረት ልማድ ሆኖብህ ሊሆን ይችላል።
ምን ማድረግ ትችላለህ? እርግጥ ነው፣ የትምህርት ቤት ሥራህን ቸል ማለት አይኖርብህም፤ ሆኖም ከስብሰባ ላለመቅረት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ደግሞም ከስብሰባዎች ሙሉ ጥቅም ለማግኘት የቻልከውን ሁሉ አድርግ። እጅህን አውጥተህ ተሳትፎ አድርግ። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ቢያንስ አንድ ሰው ጋ ሄደህ ለሰጠው ሐሳብ አመስግነው።
ጠቃሚ ምክር፦ አስቀድመህ ዝግጅት አድርግ። JW ላይብረሪን አውርድ፤ በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ምን ትምህርት እንደሚቀርብ ለማወቅ “ስብሰባዎች” የሚለውን ዓምድ ተመልከት።
ተጨማሪ እገዛ ያስፈልግሃል?