የወጣቶች ጥያቄ
ወላጆቼ ዘና እንድል የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?
ጓደኞችህ ቅዳሜ ቀን አንድ ግብዣ አዘጋጅተዋል፤ አንተንም ጠርተውሃል። ወላጆችህን ፈቃድ ስትጠይቅ ግን “አይቻልም!” አሉህ። ለነገሩ ይህን ጠብቀሃል። ባለፈውም እንዲሁ ነው ያሉህ።
በዚህ ርዕስ ውስጥ
ወላጆቼ ሁሌ “አይቻልም” የሚሉኝ ለምንድን ነው?
ወላጆችህ የምትጠይቀውን ነገር ሁሉ እንደሚከለክሉህ ይሰማሃል? ከሆነ ‘በቃ ደስ እንዲለኝ አይፈልጉም!’ ብለህ ታስብ ይሆናል።
ማሪ የተባለች ወጣት ስልክ እንደያዘች አካባቢ እንዲህ ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ ብዙ ነገሮች ነበር የከለከለኝ። ማውረድ የማይፈቀድልኝ አፕሊኬሽኖች ነበሩ፤ ማንን እንደማነጋግርና እስከ ስንት ሰዓት እንደማወራም ሕጎች አውጥቶልኝ ነበር። ጓደኞቼ ግን የፈለጉትን ማድረግ ይችሉ ነበር!”
እስቲ አስበው፦ በእርግጥ የማሪ አባት እንዲህ ያደረገው እሷ ደስ እንዲላት ስለማይፈልግ ነው? ወይስ ያሳሰበው ነገር ስላለ ነው?
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ወላጅ እንደሆንክ አድርገህ አስብ፤ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጅህ ገና ስልክ መያዙ ነው። ምን ነገሮች ያሳስቡሃል? ያሳሰቡህ ነገሮች በልጅህ ላይ እንዳይደርሱ ስትል ምን ገደቦች ታወጣ ነበር? ልጅህ ‘ደስ እንዲለኝ ስለማትፈልግ ነው!’ ቢልህ ምን ትለዋለህ?
“አባዬ ሁልጊዜ ‘እስቲ በእኔ ቦታ ሆነሽ እዪው’ ይለኝ ነበር። እንዲህ ማድረጌ ለእኔ ያወጣቸው ሕጎች ያላቸውን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ከበስተ ጀርባ ያለውን ምክንያትም እንዳስተውል አድርጎኛል። ልጆች ቢኖሩኝ፣ አባቴ ከእኔ የሚጠብቀውን ነገር ከእነሱ መጠበቄ አይቀርም።”—ታንያ
ወላጆቼ እንዲፈቅዱልኝ ምን ላድርግ?
“መጮኽ አንተንም ሆነ ወላጆችህን ከማድከም በቀር ምንም አይጠቅምህም። የምትጨቃጨቅ ከሆነ ወላጆችህ፣ እንደበሰልክና ተጨማሪ ነፃነት ለማግኘት እንደደረስክ አይሰማቸውም።”—ሪቻርድ
“ወላጆች እያንዳንዱን መመሪያ የሚያወጡት በአሳቢነት ነው። ወላጆቼ ዘና እንዳልል ሊከለክሉኝ ፈልገው አይደለም፤ ከሁሉ በተሻለውና በኋላ ላይ ጣጣ በማያመጣብኝ መንገድ እንድዝናና ስለሚፈልጉ ነው።”—አይቪ
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሞኝ ስሜቱን ሁሉ እንዳሻው ይገልጻል፤ ጥበበኛ ግን ስሜቱን ይቆጣጠራል።”—ምሳሌ 29:11
“አባቴ ከስልኬ ጋር በተያያዘ የከለከለኝን ነገር ሳላስነቃ ለማድረግ ሞከርኩ። ከመሸ በኋላ ለጓደኞቼ ቴክስት ለማድረግ ወይም አባቴ የከለከለኝን አፕሊኬሽኖች ለማውረድ መንገድ እፈልግ ነበር። በኋላ ላይ ግን ማወቁ አይቀርም። እንደዚያ ሲሆን ደግሞ በእኔ ላይ እምነት ስለሚያጣ ሕጎቹ ይበልጥ ጥብቅ ይሆናሉ። የተከለከላችሁትን ነገር ለማድረግ መሞከር መቼም አያዋጣም።”—ማሪ
“ታጋሽ ሁን። ወላጆችህ አንዴ ያወጡትን ሕግ ለማስተካከል ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ላወጧቸው ሕጎች ታዛዥ እንደሆንክ ሲመለከቱ ግን ተጨማሪ ነፃነት ለመስጠት ሊነሳሱ ይችላሉ።”—ሜሊንዳ
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።”—ቆላስይስ 3:20
“እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ወላጆችን መነዝነዝ ነገሩን ቢያከብደው እንጂ የምትፈልገውን ነገር አያስገኝልህም።”—ናታሊ
“አንድ ወላጅ፣ ልጁ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዳለው ሲያይ ደስ ይለዋል። ስለዚህ ወላጆቼን ሳነጋግር ጉዳዩን ከስሜት አንጻር ሳይሆን ምክንያታዊ ሐሳቦችን ጠቅሼ ለማስረዳት እሞክራለሁ። ይህን ሳደርግ ብዙውን ጊዜ እንደሚሳካልኝ አስተውያለሁ።”—ጆሴፍ
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አባትህንና እናትህን አክብር።”—ኤፌሶን 6:2