የወጣቶች ጥያቄ
ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር በሰላም መኖር ያለብኝ ለምንድን ነው?
“ርቃችሁ የማትርቋቸው ጓደኞች”
ይህ አባባል ለወንድሞችህና ለእህቶችህም ሊሠራ ይችላል። እርስ በርስ እንደምትዋደዱ ጥያቄ የለውም፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ጨርሶ መግባባት ያቅታችኋል። የ18 ዓመቷ ሄለና እንዲህ ብላለች፦ “ታናሽ ወንድሜ ያበሳጨኛል። በጣም የሚያበሳጨኝ ነገር ምን እንደሆነ ስለሚያውቅ ሆን ብሎ ያንን ያደርጋል!”
በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል የሚፈጠሩ አንዳንድ ግጭቶች በመነጋገርና በመደራደር በቀላሉ ሊፈቱ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፦
አንድ መኝታ ቤት የሚጠቀሙ ሁለት ወንድማማቾችን እንውሰድ፤ ከሁለት አንዳቸው ክፍሉ ውስጥ ብቻቸውን መሆን ሲፈልጉ አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። መፍትሔው? የምትፈልጉትን ነገር ለሌላው ስትሉ መተውን ተማሩ። በሉቃስ 6:31 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተግባራዊ አድርጉ።
ሁለት እህትማማቾችን ደግሞ እንውሰድ፤ አንዳቸው የሌላዋን ልብስ ሳያስፈቅዱ በመልበሳቸው ችግር ይፈጠር ይሆናል። መፍትሔው? ጉዳዩን ተነጋገሩበትና ምክንያታዊ የሆነ ገደብ አብጁ። በ2 ጢሞቴዎስ 2:24 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተግባራዊ አድርጉ።
አንዳንድ ጊዜ ግን በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል የሚከሰቱ ችግሮች ይበልጥ ከባድ ይሆናሉ፤ ይህም አስከፊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት፦
ሚርያም እና አሮን በወንድማቸው በሙሴ የቀኑበት ሲሆን ይህም አስከፊ ውጤት አስከትሏል። በዘኁልቁ 12:1-15 ላይ የሚገኘውን ታሪክ አንብብ። ከዚያም ‘በወንድሜ ወይም በእህቴ እንዳልቀና ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
ቃየን በጣም ከመናደዱ የተነሳ ወንድሙን አቤልን ገድሎታል። በዘፍጥረት 4:1-12 ላይ የሚገኘውን ታሪክ አንብብ። ከዚያም ‘ወንድሜ ወይም እህቴ ሲያበሳጩኝ ንዴቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
ሰላም ለመፍጠር የሚያነሳሱ ሁለት ምክንያቶች
ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ተስማምቶ መኖር ምንም ያህል ከባድ ቢሆንብህ ይህን ለማድረግ ጥረት ማድረግህ ተገቢ ነው የምንልባቸው ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች አሉ።
ብስለት እንዳለህ ያሳያል። አሊክስ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ሁለቱ ታናናሽ እህቶቼ ቶሎ ያበሳጩኝ ነበር። አሁን ግን እነሱን ይበልጥ በእርጋታና በትዕግሥት መያዝ ችያለሁ። አሁን አድጌያለሁ ማለት ይቻላል።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ቶሎ የማይቆጣ ሰው ትልቅ ማስተዋል አለው፤ ትዕግሥት የሌለው ሰው ግን ሞኝነቱን ይገልጣል።”—ምሳሌ 14:29
ለወደፊቱ ጥሩ ሥልጠና ይሆንሃል። የወንድሞችህንና የእህቶችህን ጉድለት ማለፍ ካቃተህ ወደፊት ከትዳር ጓደኛህ፣ ከሥራ ባልደረባህ፣ ከአለቃህ ወይም ከሌሎች ጋር ተቻችለህ የምትኖረው እንዴት ነው?
የሕይወት እውነታ፦ ወደፊት ከሰዎች ጋር በሚኖርህ ግንኙነት ረገድ ስኬታማ መሆንህ የተመካው የመነጋገርና የመደራደር ችሎታ በማዳበርህ ላይ ነው፤ እነዚህን ችሎታዎች ለማዳበር ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ የምታገኘው ደግሞ ከቤተሰብህ አባላት ጋር ባለህ ግንኙነት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።”—ሮም 12:18
ከወንድምህ ወይም ከእህትህ ጋር የተፈጠረን ችግር እንዴት መፍታት እንደምትችል ማወቅ ትፈልጋለህ? “እኩዮችህ ምን ይላሉ?” የሚለውን ሣጥን አንብብ፤ ከዚያም “ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ተስማምቶ መኖር” የሚለውን በዚህ ርዕስ ላይ የሚገኘውን የመልመጃ ሣጥን ተመልከት።