የወጣቶች ጥያቄ
ወጪዎቼን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?
“በቅርቡ አዲስ ነገር ለማየት ስል ወደ አንድ የገበያ አዳራሽ ገብቼ ነበር። ከአዳራሹ ስወጣ ግን፣ ወደዚያ ስገባ ለመግዛት ያላሰብኩትን ውድ ዕቃ ገዝቼ ነበር!”—ኮሊን
ኮሊን በሚያወጣቸው ወጪዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ አቅቶት እንደነበር ተናግሯል። አንተስ ተመሳሳይ ችግር አለብህ? ከሆነ ይህ ርዕስ ሊረዳህ ይችላል።
ወጪዎችህን መቆጣጠር ያለብህ ለምንድን ነው?
የተሳሳተ አመለካከት፦ ስለምታወጣው ገንዘብ የምታስብ ከሆነ ነፃነትህን ታጣለህ።
እውነታ፦ ወጪዎችን መቆጣጠርህ ይበልጥ ነፃነት እንድታገኝ ያስችልሃል። አይ አም ብሮክ! ዘ መኒ ሃንድቡክ የተባለ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ስለ ገንዘብህ ይበልጥ ባወቅክ መጠን አሁንም ሆነ ወደፊት የምትፈልጋቸውን ነገሮች ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ይኖርሃል።”
ወጪዎችህን መቆጣጠርህ የሚከተሉትን ጥቅሞች ያስገኝልሃል፦
በርከት ያለ ገንዘብ በሚያስፈልግህ ወቅት አትቸገርም። ኢነዝ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ወደፊት ወደ ደቡብ አሜሪካ ለመሄድ እፈልጋለሁ፣ ይህን ዕቅዴን በማሰብ ገንዘብ እያስቀመጥኩ ነው።”
ዕዳህን መቀነስ ወይም ከዕዳ ነፃ መሆን ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “[ተበዳሪ] የአበዳሪው ባሪያ ነው” ይላል። (ምሳሌ 22:7) አና የተባለች ወጣት “ዕዳ ሕይወትህን ሊቆጣጠረው ይችላል” ብላለች። አክላም “ከዕዳ ነፃ ከሆንክ በግቦችህ ላይ ማተኮር ትችላለህ” በማለት ተናግራለች።
ብስለት ያለህ ሰው መሆንህን ታሳያለህ። ወጪያቸውን የሚቆጣጠሩ ወጣቶች፣ አዋቂ ሲሆኑ ለሚያጋጥሟቸው ነገሮች ይበልጥ ዝግጁ ይሆናሉ። ጂን የተባለች የ20 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ጥሩ ሥልጠና ነው፤ ምክንያቱም ወደፊት ራሴን ችዬ ስኖር ይጠቅመኛል። ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ለመሆን ጥረት እያደረኩ ነው፤ እንዲህ ማድረጌ ወደፊትም በዚህ መንገድ ለመቀጠል ይረዳኛል።”
ዋናው ነጥብ፦ ዘ ኮምፕሊት ጋይድ ቱ ፐርሰናል ፋይናንስ፦ ፎር ቲኔጀርስ ኤንድ ኮሌጅ ስቱደንትስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ገንዘብህን መቆጣጠር መቻልህ፣ ወደፊት ራስህን ችለህ ለመኖር የሚረዳህ የመጀመሪያው ትልቅ እርምጃ ነው። ገንዘብን በጥሩ መንገድ መያዝ ከቻልክ፣ ዕድሜ ልክህን የሚጠቅምህ ልዩ ችሎታ አዳበርክ ማለት ነው።”
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ድክመትህ ምን እንደሆነ እወቅ። ዘወትር ገንዘብ እያለቀብህ የምትቸገር ከሆነ፣ ገንዘብ ያወጣኸው ለየትኞቹ ነገሮች እንደሆነ መርምር። የአንዳንዶች ችግር በኢንተርኔት አማካኝነት ግዢ መፈጸማቸው ነው። ሌሎች ደግሞ በወሩ መጨረሻ ላይ ኪሳቸውን ባዶ የሚያደርጉባቸው ቶሎ ቶሎ የሚያወጧቸው ትንንሽ ወጪዎች ናቸው!
“ትናንሽ ወጪዎች ተደማምረው ብዙ ይሆናሉ። ትናንሽ ስጦታዎችን ለመግዛት፣ ካፌዎች ውስጥ ለመዝናናት፣ በቅናሽ የሚሸጡ ዕቃዎችን ለመግዛትና ለሌሎች ቀላል የሚመስሉ ነገሮች ገንዘብ ሳወጣ እቆያለሁ፤ ለእነዚህ ነገሮች ከመቶ ዶላር በላይ እንዳወጣሁ የምገነዘበው በወሩ መጨረሻ ላይ ነው!”—ሄይሊ
በጀት አውጣ። መጽሐፍ ቅዱስ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) በጀት ማውጣትህ ወጪዎችህ ከገቢህ እንዳይበልጡ ለማድረግ ያስችልሃል።
“ወጪህ ከገቢህ የሚበልጥ ከሆነ ገንዘብህን ለየትኞቹ ነገሮች ማውጣት እንዳለብህ ወስን፤ በተጨማሪም አስፈላጊ ያልሆኑትን ነገሮች አስወግድ። ከወጪዎችህ የሚበልጥ ገቢ እስክታገኝ ድረስ ገንዘብ የሚያስወጡህን ነገሮች መቀነስ አለብህ።—ዳንየል
ጥሩ ልማድ አዳብር። ገንዘብህን በአግባቡ ለመያዝና አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስወገድ የሚረዱ በርካታ መንገዶች አሉ። እስቲ አንዳንድ ወጣቶች ጥሩ ሆነው ያገኟቸውን ዘዴዎች እንመልከት፦
“ብዙውን ጊዜ፣ ገንዘቤን ባንክ አስቀምጣለሁ፤ ምክንያቱም ገንዘቡ ባንክ ካለ ወጪ የማውጣት ፍላጎቴ እንደሚቀንስ አውቃለሁ።”—ዴቪድ
“ዕቃ ለመግዛት ስሄድ መጠነኛ ገንዘብ ብቻ ይዤ እወጣለሁ። ስለዚህ ካሰብኩት በላይ ወጪ አላወጣም።”—ኤለን
“አንድን ነገር ከመግዛቴ በፊት የተወሰነ ጊዜ በቆየሁ መጠን ‘በእርግጥ ይህ ነገር ያስፈልገኛል ወይስ አያስፈልገኝም’ የሚለውን ይበልጥ ለመለየት ያስችለኛል።”—ጄሲያ
“ጓደኞቼ ‘እንገናኝ’ ባሉኝ ቁጥር መሄድ አይጠበቅብኝም! ገንዘብ እስከሌለኝ ድረስ ‘አልችልም’ ማለት አያሳፍረኝም።”—ጄኔፈር
ዋናው ነጥብ፦ ገንዘብን በአግባቡ መያዝ ከባድ ኃላፊነት ነው። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ኮሊን ይህን በመገንዘብ እንዲህ ብሏል፦ “ወደፊት ቤተሰብ የማስተዳድር ከሆነ ገንዘብ የሚያባክን ሰው መሆን የለብኝም!” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ገና ሳላገባ ገንዘቤን በአግባቡ መያዝ ካልቻልኩ ካገባሁ በኋላም ቢሆን በዚህ ምክንያት ችግር ውስጥ ልገባ እንደምችል የታወቀ ነው።”
ጠቃሚ ምክር፦ “ያወጣችሁትን በጀት ለአንድ ሰው አሳዩት፤ ከዚያም በዕቅዳችሁ መሠረት እየሄዳችሁ ስለመሆኑ በየተወሰነ ጊዜ እንዲጠይቃችሁ አድርጉ። ተጠያቂነት መኖሩ ጥሩ ነገር ነው!”—ቨኔሳ