የወጣቶች ጥያቄ
የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?
አንድ ሰው ሕግ የሚፈቅድለት እስከሆነና የሚጠጣው በመጠኑ እስከሆነ ድረስ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ይችላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አይከለክልም። መስከርን ግን ያወግዛል።።—መዝሙር 104:15፤ 1 ቆሮንቶስ 6:10
የአገሩ ሕግ ወይም ወላጆችህ እንድትጠጣ የማይፈቅዱልህ ቢሆንም ለመጠጣት ብትፈተን ምን ታደርጋለህ?
ውጤቱን አስብ
አንዳንድ እኩዮችህ ለመዝናናት የግድ የአልኮል መጠጥ መጠጣት እንዳለባቸው ይሰማቸው ይሆናል። ሆኖም ከጠጣህ በኋላ ምን ሊከሰት ይችላል?
በሕግ ልትጠየቅ ትችላለህ። ሕጉ ሳይፈቅድልህ የአልኮል መጠጥ ከጠጣህ እንደየአገሩ ሁኔታ የገንዘብ ቅጣት ሊጣልብህ፣ በወንጀል ልትከሰስ፣ መንጃ ፈቃድህን ልትቀማ፣ ማኅበረሰባዊ አገልግሎት እንድትሰጥ ልትገደድ አልፎ ተርፎም ልትታሰር ትችላለህ።—ሮም 13:3
ስምህ ይበላሻል። የአልኮል መጠጥ ራሳችንን መቆጣጠር እንዲሳነን ያደርጋል። ስትሰክር ውሎ አድሮ የምትቆጭበትን ነገር ልትናገር ወይም ልታደርግ ትችላለህ። (ምሳሌ 23:31-33) በተለይ ማኅበራዊ ድረ ገጾች በተስፋፉበት በዛሬው ዘመን፣ አንዴ ያደረግከው ነገር በስምህ ላይ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
ራስህን የመከላከል ችሎታህ ይዳከማል። የአልኮል መጠጥ ለአካላዊ ወይም ለፆታዊ ጥቃት እንድትጋለጥ ሊያደርግህ ይችላል። እንዲሁም በሌሎች ተጽዕኖ በቀላሉ ልትሸነፍና አደገኛ ወይም ሕገ ወጥ የሆነ ነገር ልታደርግ ትችላለህ።
ሱስ። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በልጅነታቸው መጠጥ መጠጣት የሚጀምሩ ሰዎች በሱስ የመያዝ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው። ውጥረትን፣ ብቸኝነትን ወይም ድብርትን ለማሸነፍ ስትል መጠጥ መጠጣት፣ ማቆሚያ የሌለው ሽክርክሪት ውስጥ ሊከትህ ይችላል፤ ጊዜ ባለፈ ቁጥር ደግሞ ከዚህ ሽክርክሪት ውስጥ መውጣት እየከበደህ ይሄዳል።
ሞት። በ2013 በዩናይትድ ስቴትስ በየ52 ደቂቃው አንድ ሰው አልኮል ጠጥቶ በማሽከርከር ምክንያት በሚከሰት አደጋ ሕይወቱ አልፏል። በአምስት ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው ሪፖርት እንደሚያሳየው በየዓመቱ፣ ከ21 ዓመት በታች የሆኑ 1,500 ወጣቶች ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። አንተ አልኮል ባትጠጣም እንኳ የጠጣ ሰው በሚነዳው መኪና ከተሳፈርክ ራስህን ለአደጋ ታጋልጣለህ።
ቁርጥ ውሳኔ አድርግ
ምን እንደምታደርግ አስቀድመህ ከወሰንክ ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥን በመጠጣት ምክንያት ከሚከሰተው አደጋ እንዲሁም ከሌሎች መዘዞች መዳን ትችላለህ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል።” (ምሳሌ 22:3) ከማሽከርከርህ ወይም ሙሉ ትኩረት ማድረግን የሚጠይቅ ማንኛውንም ሥራ ከመሥራትህ በፊት መጠጣት ጥበብ የጎደለው ድርጊት ነው።
ቁርጥ ውሳኔ፦ ‘ለመጠጣት ብወስን እንኳ እንዲህ የማደርገው ሕጉ የሚፈቅድልኝና ያለሁበት ሁኔታ አመቺ ከሆነ ብቻ ነው።’
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለዚያ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች [ናችሁ]።” (ሮም 6:16) እኩዮችህ ስለጠጡ ብቻ የምትጠጣ ከሆነ ሌሎች እንዲቆጣጠሩህ እየፈቀድክ ነው። ከድብርት ለመላቀቅ ወይም የሚሰማህን ውጥረት ለመቀነስ ብለህ መጠጣትህ ችግሮችህን ለመቋቋም የሚረዱህን ክህሎቶች እንዳታዳብር ያደርግሃል።
ቁርጥ ውሳኔ፦ ‘እኩዮቼ እንድጠጣ እንዲገፋፉኝ አልፈቅድም።’
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ . . . ጋር አትወዳጅ።” (ምሳሌ 23:20 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ከመጥፎ ጓደኞች ጋር መግጠምህ ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያዳክምብህ ይችላል። ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ ከሚጠጡ ሰዎች ጋር ጊዜ ካሳለፍክ ራስህን አደጋ ላይ ትጥላለህ።
ቁርጥ ውሳኔ፦ ‘ከመጠን በላይ አልኮል ከሚጠጡ ሰዎች ጋር ጓደኝነት አልመሠርትም።’