የወጣቶች ጥያቄ
የፆታ ጥቃትን በተመለከተ ማወቅ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው?—ክፍል 1፦ ቅድመ ጥንቃቄ
የፆታ ጥቃት ምንድን ነው?
“ለፆታ ጥቃት” ከሕግ አንጻር የሚሰጡት ፍቺዎች ከአገር ወደ አገር ቢለያዩም ይህ ድርጊት በጥቅሉ ያለፍላጎት የሚፈጸምን ወሲባዊ ድርጊት ያመለክታል፤ አንዳንድ ጊዜ ድርጊቱ የሚፈጸመው ኃይል በመጠቀም ነው። በልጆች ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት፣ በሥጋ ዘመዶች መካከል የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ አስገድዶ መድፈር እንዲሁም ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰዎች ለምሳሌ ሐኪሞች፣ አስተማሪዎች ወይም የሃይማኖት መሪዎች አምነው የቀረቧቸውን ሰዎች የፆታ መጠቀሚያ ማድረጋቸው በዚህ ድርጊት ውስጥ ሊካተት ይችላል። በንግግርም ይሁን በድርጊት የዚህ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ጉዳዩን ለሌላ ሰው እንዳይናገሩ ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል።
አንድ ጥናት እንደገለጸው ከሆነ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየዓመቱ ከሩብ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች የፆታ ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርት አድርገዋል። ከእነዚህ መካከል ግማሽ ገደማ የሚሆኑት ከ12 እስከ 18 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ልታውቂው የሚገባ ነገር
መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ጥቃትን ያወግዛል። ከ4,000 ዓመታት ገደማ በፊት የሰዶም ከተማ ነዋሪ የሆኑ በፆታ ስሜት ያበዱ ወንዶች ወደ ከተማይቱ በእንግድነት የመጡ ሁለት ወንዶችን አስገድደው ለመድፈር ጥረት አድርገው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ይህ ሁኔታ ይሖዋ ይህችን ከተማ ለማጥፋት የወሰነበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። (ዘፍጥረት 19:4-13) በተጨማሪም ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ለሙሴ የተሰጠው ሕግ በሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸምን የግብረ ሥጋ ግንኙነት ይከለክል ነበር፤ ይህም በቤተሰብ አባል ላይ የሚፈጸምን ወሲባዊ ጥቃት ያጠቃልላል።—ዘሌዋውያን 18:6
አብዛኞቹ ሰዎች የፆታ ጥቃት የሚፈጸምባቸው በሚያውቁት ሰው ነው። ቶኪንግ ሴክስ ዊዝ ዩር ኪድስ (ከልጆቻችሁ ጋር ስለ ፆታ ግንኙነት መነጋገር) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ተገድደው ከሚደፈሩ ሦስት ሴቶች መካከል ሁለቱ የሚደፈሩት በሚያውቁት ሰው ነው። ጥቃቱን የሚፈጽምባቸው ጨርሶ የማያውቁት ሰው [አይደለም]።”
በሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በወንዶችም ላይ የፆታ ጥቃት ይፈጸማል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የዚህ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት ሰዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ናቸው። የፆታ ጥቃትን ለመከላከል የተቋቋመ በአሜሪካ የሚገኝ አንድ ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ወንዶች “ጥቃቱ ግብረ ሰዶማዊ ሊያደርጋቸው እንደሚችል” ወይም “የወንድነት ባሕርያቸውን እንደሚያሳጣቸው” በማሰብ ይሰጋሉ።
የፆታ ጥቃት ይህን ያህል መስፋፋቱ የሚያስገርም አይደለም። “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ሰዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” እና “ጨካኞች” እንዲሁም “ራሳቸውን የማይገዙ” እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) እነዚህ ባሕርያት ደግሞ የፆታ ስሜታቸውን ለማርካት ሲሉ በሌሎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎችን በትክክል የሚገልጹ ናቸው።
አንድ ሰው የፆታ ጥቃት የሚፈጸምበት በእሱ ጥፋት አይደለም። ማንም ሰው ቢሆን ያለፍላጎቱ ወሲባዊ ድርጊት ሊፈጸምበት አይገባም። ለዚህ ዓይነቱ ድርጊት ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው ድርጊቱን የፈጸመው ሰው ብቻ ነው። ያም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት እንዳይደርስብሽ ለመከላከል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ትችያለሽ።
ማድረግ የምትችዪው ነገር
ዝግጁ ሁኚ። ማንኛውም ሰው ሌላው ቀርቶ የፍቅር ጓደኛሽም ሆነ ዘመድሽ ወሲባዊ ድርጊት እንድትፈጽሙ ጫና ሊያደርግብሽ ቢሞክር ምን ማድረግ እንደምትችዪ አስቀድመሽ አስቢ። ኤሪን የተባለች አንዲት ወጣት ለማንኛውም ዓይነት የእኩዮች ግፊት እንዴት ራስን ማዘጋጀት እንደሚቻል ሐሳብ ሰጥታለች፤ ይህም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን በማሰብ ምን እርምጃ መውሰድ እንደሚቻል በድራማ መልክ መለማመድ ነው። ኤሪን እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ማድረግ የልጅ ሥራ እንደሆነ ይሰማሽ ይሆናል፤ በሕይወትሽ ውስጥ የጥቃት ሰለባ የመሆንሽ አጋጣሚ ግን በጣም ጠባብ ይሆናል።”
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሰዎች ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ ምክንያቱም ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው።’—ኤፌሶን 5:15, 16
ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ፦ ‘አንድ ሰው ደስ በማይል መንገድ ቢነካኝ ምን አደርጋለሁ?’
ከሁኔታው ማምለጥ የምትችዪበትን ዘዴ አስቀድመሽ አስቢ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው በአሜሪካ የሚገኝ ድርጅት ለዚህ መፍትሔ የሚሆን ሐሳብ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው ካላማራችሁ ለጓደኞቻችሁ ወይም ለቤተሰባችሁ ጉዳዩን የምታሳውቁበት የሚስጥር ኮድ ተነጋግራችሁ አዘጋጁ፤ ከዚያም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ስልክ በመደወል ግለሰቡ በማይረዳው መልኩ በኮድ ሁኔታውን አሳውቋቸው። በዚህ ጊዜ ጓደኞቻችሁ ወይም ቤተሰቦቻችሁ መጥተው ሊወስዷችሁ ወይም እንድትለያዩ የሚያደርግ ሰበብ ፈጥረው ለግለሰቡ ሊነግሩላችሁ ይችላሉ።” ከመጀመሪያውም ለአደጋ ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች የምትርቂ ከሆነ ከብዙ ሐዘን ትድኚያለሽ።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”—ምሳሌ 22:3
ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ፦ ‘እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመኝ ምን የማምለጫ ዘዴ አስቤያለሁ?’
ገደብ አውጪ፤ ከዚያም ያወጣሽውን ገደብ አክብሪ። ለምሳሌ እየተጠናናሽ ከሆነ የትኛው ድርጊት ተገቢ እንደሆነና የትኛው ደግሞ ተገቢ እንዳልሆነ ከጓደኛሽ ጋር ተነጋገሪበት። ጓደኛሽ ገደብ ማውጣት አስፈላጊ እንዳልሆነ አቃሎ የሚናገር ከሆነ ግን ከእሱ ጋር ያለሽን ግንኙነት አቁሚ፤ የአንቺን የሥነ ምግባር እሴቶች ከሚያከብር ሌላ ሰው ጋር መጠናናትሽ የተሻለ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ፍቅር . . . ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5
ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ፦ ‘የእኔ የሥነ ምግባር እሴቶች ምንድን ናቸው? ጨዋነት የጎደለው ምግባር ነው የሚባለው ምን ዓይነት ድርጊት ነው?’
a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በሴት ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።