የወጣቶች ጥያቄ
ጭንቀትን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
የሚያስጨንቅህ ምንድን ነው?
የሚከተሉት አስተያየቶች አልፎ አልፎ አንተን የሚሰማህን ስሜት የሚገልጹ ናቸው?
“ሁልጊዜ ‘እንዲህ ቢሆንስ?’ ‘የመኪና አደጋ ቢያጋጥመንስ?’ ‘የተሳፈርንበት አውሮፕላን ቢከሰከስስ?’ እያልኩ አስባለሁ። አብዛኛውን ሰው የማያስጨንቁት ነገሮች እኔን ያስጨንቁኛል።”—ቻርልስ
“መውጫ በሌለው ሽክርክሪት ውስጥ እንደገባች አይጥ እንደሆንኩ ስለሚሰማኝ እጨነቃለሁ። ሙትት እስክል ድረስ እሠራለሁ ግን ምንም የማከናውነው ነገር የለም!”—አና
“ሰዎች አሁንም ገና ተማሪ በመሆኔ እንደታደልኩ አድርገው ሲነግሩኝ ‘እነሱ ምን አለባቸው፣ ትምህርት ቤት ምን ያህል ውጥረት እንደሚፈጥር አይገባቸው!’ ብዬ አስባለሁ።”—ዳንኤል
“ሁልጊዜ ከፍተኛ ውጥረት ይሰማኛል። ‘ቀጥሎ ደግሞ ምን ይከሰት ይሆን ወይም አሁን ደግሞ ምን ማድረግ ይኖርብኝ ይሆን’ እያልኩ እጨነቃለሁ።”—ሎራ
የሕይወት እውነታ፦ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በመሆኑም እንደ አዋቂዎች ሁሉ ወጣቶችም ጭንቀት ሊያጋጥማቸው ይችላል።
ጭንቀት ሁልጊዜ መጥፎ ነው?
መልሱ አይደለም የሚል ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የሚወዷቸውን ሰዎች ለማስደሰት ሲሉ መጨነቃቸው ተገቢ እንደሆነ ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 7:32-34፤ 2 ቆሮንቶስ 11:28
ወደድንም ጠላንም ጭንቀት አንድ ዓይነት እርምጃ እንድንወስድ የሚገፋፋ ኃይል ሊሆንም ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚቀጥለው ሳምንት የትምህርት ቤት ፈተና አለህ እንበል። ፈተና እንዳለህ ማወቅህ ሊያስጨንቅህ ይችላል፤ ይህ ደግሞ በዚህ ሳምንት ጥሩ አድርገህ እንድታጠናና ጥሩ ውጤት እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል!
በተወሰነ ደረጃ መጨነቅህ ከአደጋ ለመራቅ ንቁ እንድትሆን ያደርግሃል። ሰሪና የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት “የተሳሳተ ጎዳና እየተከተላችሁ እንዳላችሁ ስታውቁ ትጨነቁ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሕሊናችሁ እረፍት እንዲያገኝ አካሄዳችሁን ማስተካከል እንዳለባችሁ እንድትገነዘቡ ይረዳችኋል” ብላለች።—ከያዕቆብ 5:14 ጋር አወዳድር።
የሕይወት እውነታ፦ ትክክለኛውን እርምጃ እንድትወስዱ እስካደረጋችሁ ድረስ ጭንቀት መጥፎ አይደለም።
ጭንቀት መውጫ ቀዳዳ የሌለው በሚመስል አሉታዊ አስተሳሰብ አእምሮህ እንዲወጠር ሊያደርግ ይችላል።
ምሳሌ፦ “አንድ ያሳሰበኝ ጉዳይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ሳስብ ጭንቅላቴ በጭንቀት ሊፈነዳ ይደርሳል” በማለት የ19 ዓመቱ ሪቻርድ ተናግሯል። አክሎም “ጉዳዩን መልሼ መላልሼ ስለማስበው ከመጠን በላይ ያስጨንቀኛል” ብሏል።
መጽሐፍ ቅዱስ “የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 14:30) በሌላ በኩል ደግሞ ጭንቀት እንደ ራስ ምታት፣ ማዞር፣ የሆድ ዕቃ መታወክና ከመጠን ያለፈ የልብ ምት የመሳሰሉ የጤና ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።
የተፈጠረብህ ጭንቀት እየጠቀመህ ሳይሆን እየጎዳህ እንዳለ ከተሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
ምን ማድረግ ትችላለህ?
የሚሰማህ ጭንቀት ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ራስህን መርምር። “ስላሉብህ ኃላፊነቶች መጨነቅ አንድ ነገር ሲሆን ከሚገባው በላይ መጨነቅ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ‘ጭንቀት፣ በሚወዛወዝ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ እንደመወዛወዝ ነው’ የሚለውን አባባል ያስታውሰኛል። ዝም ብለህ ትወዛወዛለህ ግን የትም አትደርስም።”—ካትሪን
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ይኖራል?”—ማቴዎስ 6:27
ይህ ምን ማለት ነው? ጭንቀት መፍትሔ የማያስገኝልህ ከሆነ ችግርህን ከማባባስ ወይም ራሱ ችግር ከመሆን ባለፈ የሚፈይድልህ ነገር የለም።
ችግሮችን አንድ በአንድ ለመፍታት ሞክር። “እስቲ ቆም ብላችሁ አስቡ። ዛሬ ያሳሰበህ ነገር ነገ፣ ከወር በኋላ፣ ከዓመት በኋላ ወይም ከአምስት ዓመት በኋላ ያን ያህል ያሳስብሃል?”—አንተኒ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።”—ማቴዎስ 6:34
ይህ ምን ማለት ነው? የነገን ችግር ዛሬ አምጥተህ የምትጨነቅ ከሆነ ምንም ትርጉም የለውም፤ የተጨነቅንበት አንዳንዱ ነገር ጭራሽ ላይከሰት ይችላል።
ልትለውጠው የማትችለውን ነገር አምነህ ተቀበል። “ከሁሉ የተሻለው ነገር ለሚያጋጥሙህ ነገሮች ራስህን ማዘጋጀት ነው፤ ሆኖም አንዳንድ ነገሮች ከአንተ ቁጥጥር ውጭ እንደሆኑ አምነህ ተቀበል።”—ሮበርት
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ . . . እውቀት ያላቸው ሰዎችም ሁልጊዜ ስኬታማ አይሆኑም፤ ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።”—መክብብ 9:11
ይህ ምን ማለት ነው? አንዳንድ ጊዜ ያለህበትን ሁኔታ መለወጥ አትችል ይሆናል፤ ስለ ጉዳዩ ያለህን አመለካከት ግን መለወጥ ትችላለህ።
ስለገጠመህ ሁኔታ ትክክለኛ አመለካከት ይኑርህ። “በጥቃቅን ነገሮች ከመጨነቅ ይልቅ በዋናው ነገር ላይ ማተኮር የተሻለ እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ። ይበልጥ አስፈላጊው ነገር ምን እንደሆነ ከወሰንኩ በኋላ በዚያ ላይ ትኩረት አደርጋለሁ።”—አሌክሲስ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10
ይህ ምን ማለት ነው? ስለሚያስጨንቃቸው ነገር ትክክለኛ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በአብዛኛው ጭንቀቱ አይቆጣጠራቸውም።
ሰው አማክር። “ስድስተኛ ክፍል ሳለሁ ሁሌ ከትምህርት ቤት ስመለስ የሚቀጥለውን ቀን እያሰብኩ እጨነቅ ነበር። እናቴና አባቴ ያስጨነቀኝን ሁኔታ ስነግራቸው ያዳምጡኝ ነበር። የእነሱ መኖር በጣም ጠቅሞኛል። በእነሱ ስለምተማመን የተሰማኝን ሁሉ በግልጽ መናገር እችላለሁ። ይህም ስለ ቀጣዩ ቀን እያሰብኩ እንዳልጨነቅ ረድቶኛል።”—ሜረሊን
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።”—ምሳሌ 12:25
ይህ ምን ማለት ነው? ጭንቀትህ ቀለል እንዲልህ የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮችን ከወላጅህ ወይም ከጓደኛህ ማግኘት ትችላለህ።
ጸልይ። “ጮክ ብዬ መጸለዬ ረድቶኛል። ድምፄን ከፍ አድርጌ መጸለዬ ያስጨነቀኝን ነገር በውስጤ አምቄ ከመያዝ ይልቅ እንዳወጣው አጋጣሚ ይሰጠኛል። ይሖዋ ካለብኝ ጭንቀት የላቀ መሆኑን እንድገነዘብም ይረዳኛል።”—ሎረ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7
ይህ ምን ማለት ነው? ጸሎት አእምሮን ለማረጋጋት ተብሎ የሚደረግ ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ “እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ” ብሎ ቃል ከገባልን ከይሖዋ ጋር በቀጥታ የምንነጋገርበት መንገድ ነው።—ኢሳይያስ 41:10