የወጣቶች ጥያቄ
ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው” በማለት ጽፏል። (ሮም 7:21) አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ተገቢ ያልሆነ ነገር እንድታደርግ የሚገፋፉህን መጥፎ ምኞቶች ማሸነፍ እንድትችል ይረዳሃል።
ማወቅ የሚኖርብህ ነገር
አብዛኛውን ጊዜ መጥፎ ነገር ለማድረግ የምትፈተነው በእኩዮች ተጽዕኖ ምክንያት ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት ጥሩውን ሥነ ምግባር ያበላሻል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33 የግርጌ ማስታወሻ) ሌሎች ሰዎች ወይም የመገናኛ ብዙኃን የሚያሳድሩብህ ተጽዕኖ መጥፎ ነገር የማድረግ ምኞት ሊቀሰቅስብህ አልፎ ተርፎም “ብዙኃኑን ተከትለህ ክፉ ነገር [እንድታደርግ]” ሊገፋፋህ ይችላል።—ዘፀአት 23:2
“በሌሎች ዘንድ ተወዳጅነትና ተቀባይነት የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ካለህ፣ እነሱን ለማስደሰት ስትል በማንኛውም ድርጊት አብረሃቸው ልትካፈል ትችላለህ።”—ጄረሚ
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ሌሎች ስለ አንተ የሚያስቡት ነገር ከልክ በላይ የሚያስጨንቅህ ከሆነ ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ከባድ ሊሆንብህ የሚችለው ለምንድን ነው?—ምሳሌ 29:25
ዋናው ነጥብ፦ እኩዮችህ የሚያሳድሩብህ ተጽዕኖ፣ አቋምህን እንድታላላ እንዲያደርግህ ፈጽሞ አትፍቀድ።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ስለምታምንባቸው ነገሮች በሚገባ እወቅ። ስለምታምንባቸው ነገሮች በሚገባ የማታውቅ ከሆነ ሌሎች እንደፈለጉ የሚቆጣጠሩት አሻንጉሊት ትሆናለህ። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም ነገር መርምሩ፤ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ” በማለት የሚሰጠውን ምክር መከተልህ ምንኛ የተሻለ ነው! (1 ተሰሎንቄ 5:21) ስለምታምንባቸው ነገሮች ይበልጥ ባወቅክ መጠን በአቋምህ መጽናትና የምታምንባቸውን ነገሮች እንድትጥስ የሚፈትኑ ሁኔታዎችን መቋቋም ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በመከተል የምትጠቀመው አንተው ራስህ እንደሆንክ የምታምነው ለምንድን ነው?
“ለማምንበት ነገር በድፍረት ጥብቅና ስቆምና ፈተናዎችን ስቋቋም ሌሎች ይበልጥ እንደሚያከብሩኝ ማስተዋል ችያለሁ።”—ኪምበርሊ
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ዳንኤል። ዳንኤል የአምላክን ሕጎች ለመታዘዝ “በልቡ ቁርጥ ውሳኔ [አድርጎ ነበር]።” ይህን ውሳኔ ያደረገው ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለ ሳይሆን አይቀርም።—ዳንኤል 1:8
ደካማ ጎንህን ለይተህ እወቅ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ወጣትነት ምኞቶች” ማለትም በወጣትነት ዕድሜ ላይ ይበልጥ ስለሚያይሉ ምኞቶች ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) እነዚህ ምኞቶች የፆታ ፍላጎትን ብቻ የሚያመለክቱ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት እንዲሁም ያለወላጆችህ ድጋፍ ውሳኔ የማድረግና ገና ዝግጁ ሳትሆን ራስህን ችለህ የመኖር ፍላጎትንም ያካትታሉ።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል” ይላል። (ያዕቆብ 1:14) ለአንተ ይበልጥ ፈታኝ የሚሆንብህ የትኛው ምኞት ነው?
“ራስህን በሐቀኝነት በመመርመር ለአንተ ይበልጥ ፈታኝ የሚሆኑብህ ነገሮች ምን እንደሆኑ ለማሰብ ሞክር። እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች መቋቋም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ምርምር አድርግ፤ ከዚያም ጠቃሚ ሐሳቦችን ጻፍ። እንዲህ ማድረግህ በቀጣዩ ጊዜ ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለብህ እንድታውቅ ይረዳሃል።”—ሲልቪያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ዳዊት። በሌሎች ተጽዕኖ የተሸነፈባቸው እንዲሁም የራሱን ምኞቶች የተከተለባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ከስህተቶቹ በመማር መልካም ነገሮችን ለማድረግ ጥሯል። ዳዊት “አምላክ ሆይ፣ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል።—መዝሙር 51:10
በተጽዕኖው ላለመሸነፍ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ “በክፉ አትሸነፍ” ይላል። (ሮም 12:21) ይህ ጥቅስ፣ ለፈተናዎች እጅ ላለመስጠትና ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ መምረጥ እንደምትችል ይጠቁማል።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ በምትፈተንበት ጊዜ ሁኔታውን መቆጣጠርና ትክክል የሆነውን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
“በፈተና ተሸንፌ ትክክል ያልሆነ ነገር ባደርግ ምን ሊሰማኝ እንደሚችል አስባለሁ። ጥሩ ስሜት ይሰማኛል? ምናልባት ለአጭር ጊዜ ያህል እንደዚያ ይሰማኝ ይሆናል። የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላስ ይህ ስሜት ይቀጥላል? በጭራሽ! እንዲያውም ማዘኔ አይቀርም። ለቅጽበታዊ ደስታ ስል ይህን ያህል መሥዋዕትነት መክፈል አልፈልግም!”—ሶፊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ጳውሎስ። መጥፎ ዝንባሌዎች እንዳሉት በሐቀኝነት ቢናገርም በእነዚህ ዝንባሌዎች ላለመሸነፍ መርጧል። ጳውሎስ “ሰውነቴን አጥብቄ እየገሠጽኩ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 9:27 የግርጌ ማስታወሻ
ዋናው ነጥብ፦ ትክክል ያልሆነ ነገር እንድታደርግ በሚቀርብልህ ፈተና የመሸነፉ ወይም ያለመሸነፉ ጉዳይ በአንተ ላይ የተመካ ነው።
የሚያጋጥሙህ ፈታኝ ሁኔታዎች ጊዜያዊ እንደሆኑ አስታውስ። የ20 ዓመቷ ሜሊሳ እንዲህ ብላለች፦ “የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ በጣም ፈታኝ የሆኑብኝ ነገሮች አሁን እዚህ ግቡ የማልላቸው ነገሮች ሆነዋል። ይህን ማስታወሴ፣ አሁን የሚያጋጥሙኝ ፈታኝ ሁኔታዎችም ማለፋቸው እንደማይቀርና ወደፊት ይህን ጊዜ መለስ ብዬ ሳስብ ፈተናዎቹን በመወጣቴ በጣም ደስተኛ እንደምሆን እንድተማመን ያደርገኛል።”