የይሖዋ ምሥክሮች በዓለ ትንሣኤን የማያከብሩት ለምንድን ነው?
የተሳሳቱ ግንዛቤዎች
የሚባለው፦ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለ ትንሣኤን የማያከብሩት ክርስቲያን ስላልሆኑ ነው።
ሐቁ፦ ኢየሱስ አዳኛችን እንደሆነ እናምናለን፤ ‘የእሱን ፈለግ በጥብቅ ለመከተልም’ ጥረት እናደርጋለን።—1 ጴጥሮስ 2:21፤ ሉቃስ 2:11
የሚባለው፦ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ አታምኑም።
ሐቁ፦ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እናምናለን፤ የእሱ ትንሣኤ ለክርስትና እምነት መሠረት እንደሆነ ስለምንገነዘብ በስብከታችን ላይ ትልቅ ቦታ እንሰጠዋለን።—1 ቆሮንቶስ 15:3, 4, 12-15
የሚባለው፦ በዓለ ትንሣኤን ስለማታከብሩ ልጆቻችሁ እንዲደሰቱ አትፈልጉም።
ሐቁ፦ ልጆቻችንን እንወዳቸዋለን፤ እነሱን ለማሠልጠንና ለማስደሰት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።—ቲቶ 2:4
የይሖዋ ምሥክሮች በዓለ ትንሣኤን የማያከብሩት ለምንድን ነው?
በዓለ ትንሣኤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የለውም።
ኢየሱስ እንድናከብር ያዘዘን የሞቱን መታሰቢያ እንጂ ትንሣኤውን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተገለጸው የጨረቃ አቆጣጠር መሠረት የሞቱን መታሰቢያ በየዓመቱ እናከብራለን።—ሉቃስ 22:19, 20
ከበዓለ ትንሣኤ ጋር የተያያዙ ልማዶች ምንጫቸው ጥንታዊ የመራባት አምልኮ ሥርዓት በመሆኑ በዓሉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። አምላክ “ቀናተኛ” በመሆኑ እሱ የማይፈልጋቸው ልማዶች ያሉበት የአምልኮ ሥርዓት ያሳዝነዋል።—ዘፀአት 20:5፤ 1 ነገሥት 18:21
በዓለ ትንሣኤን ላለማክበር ያደረግነው ውሳኔ የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ወግ ከመመራት ይልቅ ‘አስተውለን እንድንለይ’ ያበረታታናል። (ምሳሌ 3:21፤ ማቴዎስ 15:3) ሰዎች ስለ በዓለ ትንሣኤ ያለንን አመለካከት ከጠየቁን አቋማችንን ከመናገር ወደ ኋላ ባንልም እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳለው ስለምናውቅ የሌሎችን ምርጫ እናከብራለን።—1 ጴጥሮስ 3:15