የይሖዋ ምሥክሮች ደም የማይወስዱት ለምንድን ነው?
የተሳሳቱ ግንዛቤዎች
የሚባለው፦ የይሖዋ ምሥክሮች መድኃኒትንም ሆነ ሕክምናን አይቀበሉም።
ሐቁ፦ ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን ከሁሉ የተሻለውን ሕክምና ማግኘት እንፈልጋለን። ጤናችን ሲታወክ፣ ያለ ደም ሊያክሙን ወይም ቀዶ ሕክምና ሊያደርጉልን ወደሚችሉ ሐኪሞች እንሄዳለን። በሕክምናው ዓለም እየታየ ያለውን መሻሻል እናደንቃለን። እንዲያውም ለይሖዋ ምሥክሮች በማሰብ የተዘጋጁ ያለ ደም የሚሰጡ ሕክምናዎች ዛሬ ኅብረተሰቡን በሙሉ እየጠቀሙ ነው። በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ፣ ማንኛውም ታካሚ ያለ ደም የሚሰጡ ሕክምናዎችን በመምረጥ ደም በመውሰድ ሳቢያ ከሚመጡ በሽታዎች፣ የሌላ ሰው ደም ከሰውነታችን ጋር ባለመጣጣሙ ምክንያት ከሚፈጠር ችግርና የሕክምና ባለሙያዎች ሊሠሩ ከሚችሉት ስህተት መዳን ይችላል።
የሚባለው፦ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ሰው በእምነት ብቻ ከበሽታው ሊፈወስ ይችላል ብለው ያምናሉ።
ሐቁ፦ ተአምራዊ ፈውስ አናከናውንም።
የሚባለው፦ ያለ ደም የሚሰጡ ሕክምናዎች በጣም ውድ ናቸው።
ሐቁ፦ ያለ ደም የሚሰጡ ሕክምናዎች ወጪን ይቀንሳሉ። a
የሚባለው፦ ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ልጆችን ጨምሮ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ ይሞታሉ።
ሐቁ፦ ይህ ሐሳብ መሠረተ ቢስ ነው። የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች የልብና የአጥንት ቀዶ ሕክምናዎች እንደማድረግ ብሎም የሰውነት ክፍሎችን እንደመቀየር ያሉ ውስብሰብ ሕክምናዎችን ያለ ደም በየጊዜው ያደርጋሉ። b አብዛኛውን ጊዜ ልጆችን ጨምሮ ደም ያልወሰዱ ታካሚዎች ደም ከወሰዱት ጋር እኩል አንዳንዴም ደም ከወሰዱት በተሻለ ፍጥነት ያገግማሉ። c ያም ሆነ ይህ ማንም ሰው እርግጠኛ ሆኖ፣ አንድ በሽተኛ ደም ካልወሰደ ይሞታል ወይም ደም በመውሰዱ ሕይወቱ ይተርፋል ማለት አይችልም።
የይሖዋ ምሥክሮች ደም የማይወስዱት ለምንድን ነው?
ዋነኛ ምክንያቱ ሃይማኖታዊ አቋማችን እንጂ የሕክምና ጉዳይ አይደለም። ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን ከደም እንድንርቅ በግልጽ ያሳስቡናል። (ዘፍጥረት 9:4፤ ዘሌዋውያን 17:10፤ ዘዳግም 12:23፤ የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) በተጨማሪም አምላክ ደም ሕይወትን እንደሚወክል ተናግሯል። (ዘሌዋውያን 17:14) በመሆኑም ደም የማንወስደው አምላክን ለመታዘዝ ብለን ብቻ ሳይሆን የሕይወት ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ለእሱ አክብሮት ስላለን ጭምር ነው።
የአመለካከት ለውጦች
በአንድ ወቅት የሕክምናው ዓለም ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምናን መምረጥ ጽንፈኝነት አልፎ ተርፎም ራስን ማጥፋት እንደሆነ አድርጎ ያስብ ነበር፤ ይሁንና ይህ አመለካከት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቀይሯል። ለምሳሌ በ2004 በታተመ የሕክምና ትምህርት መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “ለይሖዋ ምሥክር ታካሚዎች ተብለው የተዘጋጁት አብዛኞቹ ዘዴዎች በቀጣዮቹ ዓመታት የተለመደ የሕክምና አሠራር መሆናቸው አይቀርም” ብሎ ነበር።” d ኸርት፣ ላንግ ኤንድ ሰርክዩሌሽን (ልብ፣ ሳንባና የደም ዝውውር) የተባለው መጽሔትም ቢሆን በ2010 እትሙ ላይ “‘ያለ ደም የሚሰጥ ቀዶ ሕክምና’ ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ የተለመደው የቀዶ ሕክምና አሠራር ዋነኛ ክፍል መሆን ይኖርበታል” የሚል ሐሳብ አውጥቶ ነበር።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሐኪሞች ውስብስብ ቀዶ ሕክምናዎችን ያለ ደም ለማድረግ ብዙ ደም እንዳይፈስ የሚረዱ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ነው። በማደግ ላይ ያሉ አገሮች እንኳ እንዲህ ያሉ ሕክምናዎችን እየሰጡ ሲሆን የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ በርካታ ታካሚዎች ከዚህ ተጠቃሚ ሆነዋል።
a የሚከተለውን ጽሑፍ ተመልከት፦ ትራንስፊውዥን ኤንድ አፌረሲስ ሳይንስ፣ ጥራዝ 33፣ ቁ. 3፣ ገጽ 349
b የሚከተሉትን ጽሑፎች ተመልከት፦ ዘ ጆርናል ኦቭ ቶራሲክ ኤንድ ካርዲዮቫስኩላር ሰርጀሪ፣ ጥራዝ 134፣ ቁ. 2፣ ከገጽ 287-288፤ ቴክሳስ ኸርት ኢንስቲትዩት ጆርናል፣ ጥራዝ 38፣ ቁ. 5፣ ገጽ 563፤ ቤዚክስ ኦቭ ብለድ ማኔጅመንት ገጽ 2፤ እንዲሁም ከንቲኒዩዊንግ ኤጁኬሽን ኢን አነስቴዥያ፣ ክሪቲካል ኬር ኤንድ ፔይን፣ ጥራዝ 4፣ ቁ. 2፣ ገጽ 39
c የሚከተሉትን ጽሑፎች ተመልከት፦ ዘ ጆርናል ኦቭ ቶራሲክ ኤንድ ካርዲዮቫስኩላር ሰርጀሪ፣ ጥራዝ 89፣ ቁ. 6፣ ገጽ 918፤ እንዲሁም ኸርት፣ ላንግ ኤንድ ሰርክዩሌሽን፣ ጥራዝ 19፣ ገጽ 658
d ከንቲንዩዊንግ ኤጁኬሽን ኢን አነስቴዥያ፣ ክሪቲካል ኬር ኤንድ ፔይን፣ ጥራዝ 4፣ ቁ 2፣ ገጽ 39