የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ሕክምና ያላቸው አቋም ምንድን ነው?
ይሖዋ ምሥክሮች መድኃኒትንም ሆነ ሕክምናን ይቀበላሉ። ሰውነታችንን ለመንከባከብና ጤናማ ሆነን ለመኖር አንዳንዴ ወደ “ሐኪም” መሄድ ያስፈልገናል። (ሉቃስ 5:31) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደኖረው እንደ ሉቃስ ሁሉ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ሐኪሞች ናቸው።—ቆላስይስ 4:14
አንዳንድ ሕክምናዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር ስለሚጋጩ አንቀበላቸውም። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ደም ወደ ሰውነት ማስገባትን ስለሚያወግዝ ደም አንወስድም። (የሐዋርያት ሥራ 15:20) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪነት ያላቸውን ሕክምናዎች ይከለክላል።—ገላትያ 5:19-21
በሌላ በኩል ግን አብዛኞቹ የሕክምና ዓይነቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር አይጋጩም። በመሆኑም ምርጫው ለግል የተተወ ነው። ስለዚህ አንድ የይሖዋ ምሥክር አንድን የሕክምና ዓይነት ወይም መድኃኒት ሲቀበል ሌላው ግን ይህን አማራጭ ላይቀበለው ይችላል።—ገላትያ 6:5