የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ቦታቸውን ቤተ ክርስቲያን ብለው የማይጠሩት ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቤተ ክርስቲያን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድን የአምልኮ ስፍራ ሳይሆን ለአምልኮ የተሰበሰቡ ሰዎችን የሚያመለክትበት ጊዜ አለ።
አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ሲጽፍ አቂላና ጵርስቅላ ለተባሉ ባልና ሚስት ሰላምታ ልኮ ነበር፤ ከዚያም “በእነርሱ ቤት ላለች ቤተ ክርስቲያንም ሰላምታ አቅርቡልኝ” ብሏል። (ሮም 16:5 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ጳውሎስ ሰላምታ የላከው ለቤቱ ወይም ለአንድ ሕንፃ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ ሰላምታ የላከው ለሰዎቹ ይኸውም በዚያ ቤት ለሚሰበሰበው ጉባኤ ነበር። a
ስለዚህ የአምልኮ ቦታችንን ቤተ ክርስቲያን ከማለት ይልቅ “የመንግሥት አዳራሽ” ብለን እንጠራዋለን።
ታዲያ “የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ” የሚለውን ስም የምትጠቀሙት ለምንድን ነው?
ይህ ስያሜ ተስማሚ የሆነባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፦
ሕንፃው አዳራሽ ወይም የመሰብሰቢያ ቦታ ነው።
እዚያ የምንሰበሰበው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን አምላክ ማለትም ይሖዋን ለማምለክና ስለ እሱ ለመመሥከር ነው።—ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም፤ ኢሳይያስ 43:12
በተጨማሪም እዚያ የምንሰበሰበው ኢየሱስ በትምህርቱ ላይ በተደጋጋሚ ይጠቅሰው ስለነበረው የአምላክ መንግሥት ለመማር ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14፤ ሉቃስ 4:43
በአካባቢህ ወደሚገኝ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ሄደህ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያካሂዱት ስብሰባ ምን እንደሚመስል እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።
a በ1 ቆሮንቶስ 16:19፤ በቆላስይስ 4:15 እና በፊልሞና 2 ላይም ተመሳሳይ አገላለጾች ይገኛሉ።