የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ በዓላትን የማያከብሩት ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች፣ አንድን በዓል ማክበር ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን የሚወስኑት በምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች አንድን በዓል ለማክበር ወይም ላለማክበር ከመወሰናቸው በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። አንዳንድ በዓላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በቀጥታ ይጋጫሉ። የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያሉ በዓላትን አያከብሩም። ከዚህ ውጭ የሆኑ በዓላትን በተመለከተ ግን እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር የራሱን ውሳኔ ያደርጋል፤ ይህን በሚያደርግበት ወቅት “በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ንጹሕ ሕሊና” እንዲኖረው ጥረት ያደርጋል።—የሐዋርያት ሥራ 24:16
የይሖዋ ምሥክሮች አንድን በዓል ለማክበር ወይም ላለማክበር ከመወሰናቸው በፊት ራሳቸውን የሚጠይቋቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ከታች ተዘርዝረዋል። a
በዓሉ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆነ ትምህርት ላይ የተመሠረተ ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “‘ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ርኩስ የሆነውንም ነገር አትንኩ።’”—2 ቆሮንቶስ 6:15-17
የይሖዋ ምሥክሮች በመንፈሳዊ ርኩስ ከሆኑ ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከሚጋጩ ትምህርቶች ሙሉ በሙሉ ይርቃሉ፤ በመሆኑም ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ዓይነት በዓላት አያከብሩም።
የበዓሉ አመጣጥ ለሐሰት አማልክት ከሚቀርብ አምልኮ ጋር የተያያዘ ከሆነ። ኢየሱስ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” ብሏል። (ማቴዎስ 4:10) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ትእዛዝ ስለሚከተሉ እንደ ገና፣ በዓለ ትንሣኤ ወይም ሜይ ዴይ ያሉ በዓላትን አያከብሩም፤ ምክንያቱም የእነዚህ በዓላት አመጣጥ ለይሖዋ ሳይሆን ለሐሰት አማልክት ከሚቀርብ አምልኮ ጋር የተያያዘ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚከተሉት ያሉ በዓላትን አያከብሩም።
ክዋንዛ። ይህ በዓል ስያሜውን ያገኘው “ማቱንዳ ያ ክዋንዛ ከሚሉት የስዋሂሊ ቃላት ነው፤ ትርጉሙም ‘የፍሬ በኩራት’ ማለት ነው።” ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ በዓሉ አፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያው አዝመራ መድረሱን አስመልክቶ ይከበሩ ከነበሩ ጥንታዊ በዓላት የመጣ ነው። (ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ብላክ ስተዲስ) አንዳንዶች፣ ክዋንዛ ምንም ሃይማኖታዊ ይዘት የሌለው በዓል እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ሆኖም ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ አፍሪካን ሪሊጅን ይህን በዓል አፍሪካውያን “ለአማልክትና ለሞቱ ቅድመ አያቶቻቸው [የመጀመሪያውን አዝመራ] ስጦታ አድርገው በማቅረብ ምስጋናቸውን ከሚገልጹበት” በዓል ጋር ያመሳስለዋል። አክሎም ኢንሳይክሎፒዲያው እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ለሞቱ ቅድመ አያቶች ምስጋናን የመግለጽ ልማድ የአፍሪካ አሜሪካውያን በሚያከብሩት ክዋንዛ በዓል ላይም ይታያል።”
ሚድ ኦተም ፌስቲቫል (የመጸው ወቅት አጋማሽ በዓል)። “ለጨረቃ አምላክ ክብር ለመስጠት” የሚከበር በዓል ነው። (ሆሊዴይስ፣ ፌስቲቫልስ ኤንድ ሰለብሬሽንስ ኦቭ ዘ ዎርልድ ዲክሽነሪ) ይህ በዓል ሲከበር “የቤቱ ሴቶች በእንስቷ አምላክ ፊት ይሰግዳሉ፤ ይህም በቻይንኛ ካውታው ተብሎ ይጠራል።”—ሪሊጅንስ ኦቭ ዘ ወርልድ—ኤ ኮምፕርሄንሲቭ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ብሊፍስ ኤንድ ፕራክቲስስ
ናውሩዝ (ኖውሩዝ)። “ይህ በዓል በተወሰነ መልኩ ከዞሮአስትሪያኒዝም የመነጨ ነው፤ በዓሉ የሚከበርበት ዕለት በጥንቱ የዞሮአስትሪያን ቀን መቁጠሪያ እጅግ ቅዱስ ተደርገው ከሚቆጠሩት ቀናት አንዱ ነው። . . . በዞሮአስትሪያን ወግ መሠረት በኖውሩዝ ዕለት እኩለ ቀን ላይ፣ [ራፒትዊን] ተብሎ ለሚጠራው የቀትር መንፈስ አቀባበል ይደረግለታል፤ እንዲህ ዓይነቱ አቀባበል የሚደረገው በቅዝቃዜው ወቅት የክረምት መንፈስ የቀትርን መንፈስ ቀብሮት እንደሚቆይ ይታመን ስለነበር ነው።”—የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት
ሻቤ ያልዳ። ይህ በዓል በቅዝቃዜው ወቅት የመጨረሻ ቀን ላይ የሚከበር በዓል ነው፤ የብርሃን አምላክ ከሆነው “ከሚትራ አምልኮ ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑ ምንም እንደማያጠራጥር” ሱፊዝም ኢን ዘ ሴክሬት ሂስትሪ ኦቭ ፐርዢያ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። በዓሉ ለሮማውያንና ለግሪካውያን የፀሐይ አማልክት ከሚቀርበው አምልኮ ጋርም ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል። b
ታንክስጊቪንግ (የምስጋና በዓል)። እንደ ክዋንዛ ሁሉ ይህ በዓልም ለተለያዩ አማልክት ክብር ለመስጠት ሲባል ይከበሩ ከነበሩ ጥንታዊ የመከር በዓላት የመጣ ነው። ከጊዜ በኋላ “ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ጥንታዊ ልማዶች ተቀብላለች።”—ኤ ግሬት ኤንድ ጎድሊ አድቬንቸር —ዘ ፒልግሪምስ ኤንድ ዘ ሚት ኦቭ ዘ ፈርስት ታንክስጊቪንግ
በዓሉ ከአጉል እምነት ወይም በዕድል ከማመን ጋር የተያያዘ ከሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “መልካም ዕድል ለተባለ አምላክ ማዕድ” የሚያሰናዱ ሰዎች ‘ይሖዋን እንደተዉ’ ሰዎች ይቆጠራሉ። (ኢሳይያስ 65:11) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉትን በዓላት አያከብሩም።
ኢቫን ኩፓላ። “በብዙዎች ዘንድ እንደሚታመነው፣ [ኢቫን ኩፓላ] በሚውልበት ዕለት ተፈጥሮ ምትሃታዊ ኃይል ትለቃለች፤ ጀግና የሆነና ዕድል የቀናው ሰው በዚህ ዕለት ይህን ኃይል በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ ይችላል” በማለት ዚ ኤ ቱ ዜድ ኦቭ ቤላሩስ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። በጥንት ጊዜ ይህ በዓል፣ በበጋ ወቅት ቀኑ በጣም ረጅም በሚሆንበት ዕለት ላይ የሚከበር አረማዊ በዓል ነበር። ክርስትና ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ ግን “ቤተ ክርስቲያን ከምታከብረው በዓል ጋር [የመጥምቁ ዮሐንስ በዓል ከሚውልበት ቀን ጋር] እንዲቀላቀል ተደረገ” በማለት ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ኮንቴምፖራሪ ራሺያን ካልቸር ይናገራል።
የጨረቃ አዲስ ዓመት (የቻይናውያን አዲስ ዓመት ወይም የኮሪያውያን አዲስ ዓመት)። “በዓመቱ ውስጥ ከሌላው ጊዜ ይበልጥ በዚህ ጊዜ ላይ፣ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ጥሩ ዕድል እንዲገጥማቸው የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ለአማልክትና ለመናፍስት አክብሮታቸውን ይገልጻሉ እንዲሁም ለመጪው ዓመት ጥሩ ጥሩ ነገር እንዲገጥማቸው ይመኛሉ።” (ሙንኬክስ ኤንድ ሀንግሪ ጎስትስ—ፌስቲቫልስ ኦቭ ቻይና) የኮሪያውያን አዲስ ዓመትም በተመሳሳይ መንገድ ይከበራል። በበዓሉ ላይ “ለሞቱ ቅድመ አያቶች የአምልኮ ሥርዓት ይካሄዳል፤ በአዲሱ ዓመት ክፉ መናፍስትን ለማባረርና ጥሩ ዕድል እንዲገጥም ለማድረግ አንዳንድ ሥርዓቶች ይከናወናሉ፤ እንዲሁም ሰዎች በአዲሱ ዓመት ምን እንደሚገጥማቸው [በጥንቆላ] ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ኒው ይርስ ሆሊዴይስ ወርልድዋይድ
በዓሉ፣ ‘ነፍስ አትሞትም’ በሚለው ትምህርት ላይ የተመሠረተ ከሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ነፍስ እንደምትሞት በግልጽ ይናገራል። (ሕዝቅኤል 18:4) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ከታች የተዘረዘሩትን በዓላት አያከብሩም፤ ምክንያቱም ‘ነፍስ አትሞትም’ በሚለው የተሳሳተ እምነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው።
ኦል ሶልስ ዴይ (የሙታን ቀን)። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚናገረው፣ ይህ ቀን “በሞት ያንቀላፉ ሰዎች በሙሉ የሚታሰቡበት” ቀን ነው። “በመካከለኛዎቹ ዘመናት፣ መንጽሔ ውስጥ ያሉ ነፍሳት በዚህ ዕለት እንደሚወጡና እንደ ጭራቅ፣ ጣረ ሞት፣ እንቁራሪት ወዘተ ሆነው በቀድሞ ሕይወታቸው ለበደሏቸው ሰዎች እንደሚገለጡ በስፋት ይታመን ነበር።”
ቺንግሚንግ ፌስቲቫል እና ሀንግሪ ጎስት ፌስቲቫል። እነዚህ ሁለት በዓላት የሚከበሩት ለሞቱ ቅድመ አያቶች ክብር ለመስጠት ሲባል ነው። ሰለብሬቲንግ ላይፍ ከስተምስ አራውንድ ዘ ወርልድ—ፍሮም ቤቢ ሻወርስ ቱ ፍዩነራልስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው፣ በቺንግሚንግ በዓል ወቅት “ሰዎች ምግብ፣ መጠጥና ብር ያቃጥላሉ፤ እንዲህ የሚያደርጉት፣ የሞቱ ሰዎች እንዳይራቡ፣ እንዳይጠሙ ወይም ገንዘብ እንዳያጡ ሲሉ ነው።” መጽሐፉ አክሎ እንደሚናገረው “ሀንግሪ ጎስት በሚከበርበት ወር በተለይ ደግሞ ጨረቃዋ ሙሉ በምትሆንበት ምሽት፣ በሞቱትና በሕይወት ባሉት ሰዎች መካከል የሚኖረው ትስስር ከሌላ ከየትኛውም ምሽት የበለጠ እንደሆነ ይታመናል፤ ስለዚህ የሞቱ ሰዎች እንዳይቆጡ ለማድረግ እንዲሁም የሞቱ ቅድመ አያቶችን ለማክበር አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ ያስፈልጋል።”
ቹሶክ። በዚህ በዓል ላይ “ለሞቱ ሰዎች ነፍስ ምግብና ወይን ጠጅ የማቅረብ” ልማድ እንዳለ ዘ ኮሪያን ትራዲሽን ኦቭ ሪሊጅን ሶሳይቲ ኤንድ ኤቲክስ ይናገራል። እነዚህን ነገሮች የሚያቀርቡት “ሰው ከሞተ በኋላ መኖሯን የምትቀጥል ነፍስ እንዳለች” ስለሚያምኑ ነው።
በዓሉ ከጥንቆላ ጋር ግንኙነት ካለው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ . . . በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው።” (ዘዳግም 18:10-12) የይሖዋ ምሥክሮች ከጥንቆላ ዓይነቶች አንዱ የሆነውን ኮከብ ቆጠራን ጨምሮ ከማንኛውም ዓይነት የጥንቆላ ድርጊት ጋር ንክኪ እንዲኖራቸው አይፈልጉም፤ በመሆኑም ሃሎዊን የተባለውን በዓልም ሆነ የሚከተሉትን በዓላት አያከብሩም፦
የሲንሃላ እና የታሚል አዲስ ዓመት። “በዚህ በዓል ላይ የተለያዩ የአምልኮ ሥርዓቶች ይካሄዳሉ፤ . . . ለምሳሌ፣ ሰዎች ኮከብ ቆጣሪዎች ጥሩ ዕድል ያመጣሉ ብለው በለዩአቸው ጊዜያት ላይ የተለያዩ ነገሮችን ያደርጋሉ።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ስሪ ላንካ
ሶንግክራን። ይህ የእስያውያን በዓል ስያሜውን ያገኘው “‘እንቅስቃሴ’ ወይም ‘ለውጥ’ የሚል ትርጉም ካለው የሳንስክሪት ቃል ነው፤ በኮከብ ቆጠራ ወይም በዞዲያክ ካርታ መሠረት ፀሐይ ወደ ኤሪስ ሕብረ ከዋክብት የምትንቀሳቀስበትን ጊዜ ምክንያት በማድረግ የሚከበር በዓል ነው።”—ፉድ፣ ፊስትስ ኤንድ ፌይዝ—አን ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ፉድ ካልቸር ኢን ወርልድ ሪሊጅንስ
በዓሉ በኢየሱስ መሥዋዕት በተሻረው በሙሴ ሕግ ላይ የተመሠረተ ከሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነው” ይላል። (ሮም 10:4) ክርስቲያኖች፣ ለጥንት እስራኤላውያን የተሰጠው የሙሴ ሕግ ከያዛቸው መሠረታዊ ሐሳቦች አሁንም ብዙ የሚማሩት ነገር አለ። ይሁንና ክርስቲያኖች በሕጉ ላይ የተጠቀሱትን በተለይ ደግሞ ከመሲሑ መምጣት ጋር የተያያዙትን በዓላት አያከብሩም፤ ምክንያቱም መሲሑ እንደመጣ ስለሚያምኑ እነዚህን በዓላት ማክበራቸው ትርጉም የለውም። “እነዚህ ለሚመጡት ነገሮች ጥላ ናቸው፤ እውነተኛው ነገር ግን የክርስቶስ ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ቆላስይስ 2:17) ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶቹ በዓላት መጽሐፍ ቅዱስ ከማይደግፋቸው ልማዶች ጋር ተቀላቅለዋል፤ በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ከማያከብሯቸው በዓላት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
ሀኑካ። ይህ በዓል የሚከበረው፣ በኢየሩሳሌም ያለው የአይሁዳውያን ቤተ መቅደስ እንደገና የተመረቀበትን ጊዜ ለማሰብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ግን፣ ኢየሱስ ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሾመው ‘በሰው እጅ ባልተሠራው ይኸውም ከዚህ ፍጥረት ባልሆነው ይበልጥ ታላቅና ፍጹም በሆነው ድንኳን’ ወይም ቤተ መቅደስ ላይ ነው። (ዕብራውያን 9:11) ክርስቲያኖች፣ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቀደስ በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ እንደተተካ ያምናሉ።
ሮሽ ሃሻና። ይህ በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን ነው። በጥንት ዘመን፣ ይህ በዓል ለአምላክ ልዩ መሥዋዕቶች የሚቀርቡበት በዓል ነበር። (ዘኁልቁ 29:1-6) ይሁንና መሲሕ ሆኖ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘መሥዋዕትንና የስጦታ መባን አስቀርቷል፤’ በሌላ አባባል በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው አድርጓል።—ዳንኤል 9:26, 27
በዓሉ ሃይማኖትን መቀላቀልን ያበረታታል?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ድርሻ አለው? እንዲሁም የአምላክ ቤተ መቅደስ ከጣዖቶች ጋር ምን ስምምነት አለው?”—2 ቆሮንቶስ 6:15-17
የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሰዎች ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን እምነት የመከተል መብት እንዳለው ይገነዘባሉ። ሆኖም በሚከተሉት መንገዶች ሃይማኖትን መቀላቀልን የሚያበረታቱ በዓላትን አያከብሩም።
ለአንድ የሃይማኖት መሪ ክብር ለመስጠት የሚከበሩ በዓላት ወይም የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች በኅብረት ሆነው አምልኮ እንዲያከናውኑ የሚያበረታቱ ዝግጅቶች። አምላክ የጥንት ሕዝቦቹን እየመራ ሌሎች ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ሰዎች ወደሚኖሩባት ምድር ባስገባቸው ወቅት እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ከእነሱም ሆነ ከአማልክታቸው ጋር ቃል ኪዳን መግባት የለብህም። . . . አማልክታቸውን ብታገለግል ወጥመድ ይሆንብሃል።” (ዘፀአት 23:32, 33) ከዚህ አንጻር የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚከተሉት ባሉ በዓላት ላይ አይካፈሉም።
ሎይ ክራቶንግ። በዚህ የታይላንድ በዓል ላይ “ሰዎች የቅጠል ሳህኖች ሠርተው ሻማ ወይም ሰንደል ያስቀምጡባቸዋል፤ ከዚያም ሳህኖቹን ውኃ ላይ ይለቋቸዋል። ሳህኖቹ የሰዎቹን መጥፎ ገድ ይዘው እንደሚሄዱ ይነገራል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይህ በዓል ቅዱስ ተደርጎ የሚቆጠረው የቡድሃ የእግር ዱካ የሚከበርበት በዓል ነው።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ቡድሂዝም
ብሔራዊ የንስሐ ቀን (ናሽናል ሪፔንታንስ ዴይ)። በዚህ በዓል ላይ የሚሳተፉ ሁሉ “የክርስትናን እምነት መርሆዎች የሚቀበሉ ናቸው”፤ ይህን ያሉት ዘ ናሽናል በተባለው የፓፑዋ ኒው ጊኒ ጋዜጣ ላይ የተጠቀሱ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ናቸው። እኚህ ባለሥልጣን አክለው እንደተናገሩት፣ ይህ ዕለት “የክርስትና መርሆዎች በአገሪቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲሰጣቸው” አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ቪዛክ። “ይህ ዕለት፣ የቡድሂስት እምነት ተከታዮች ከሚያከብሯቸው የተቀደሱ ቀናት ሁሉ እጅግ ቅዱሱ ነው፤ ቡድሃ የተወለደበት፣ የእውቀት ብርሃን የተገለጠለትና የሞተበት . . . ጊዜ የሚታሰብበት በዓል ነው።”—ሆሊዴይስ፣ ፌስቲቫልስ ኤንድ ሰለብሬሽንስ ኦቭ ዘ ወርልድ ዲክሽነሪ
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባልተጠቀሱ ሃይማኖታዊ ወጎች ላይ የተመሠረቱ በዓላት። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች “ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ቃል ሽራችኋል” ብሏቸዋል። በተጨማሪም “የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ” የሚያቀርቡት አምልኮ ተቀባይነት እንደማያገኝ ተናግሯል። (ማቴዎስ 15:6, 9) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ማሳሰቢያ በቁም ነገር ስለሚመለከቱ እንደሚከተሉት ያሉ ሃይማኖታዊ በዓላትን አያከብሩም።
ጥምቀት (ኤፒፋኒ፣ ስሪ ኪንግስ ዳይ፣ ሎስ ሬይስ ማጎስ)። እነዚህ በዓላት የሚከበሩት፣ ኮከብ ቆጣሪዎች ኢየሱስን ለመጠየቅ የሄዱበትን ወይም ኢየሱስ የተጠመቀበትን ዕለት ለማሰብ ነው። ኤፒፋኒ “ለወንዞች፣ ለጅረቶችና ለምንጮች አማልክት ክብር ሲባል ይከበሩ የነበሩ አረማዊ የፀደይ በዓላት ከክርስትና ጋር እንዲቀላቀሉ” ያደረገ በዓል ነው። (ዘ ክሪስማስ ኢንሳይክሎፒዲያ) ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው የጥምቀት በዓልም “መሠረቱ ጥንታዊ ወጎች ናቸው።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሶሳይቲ ኤንድ ካልቸር ኢን ዚ ኤንሸንት ወርልድ
ፍልሰታ (ፊስት ኦቭ ዚ አሰምፕሽን ኦቭ ዘ ቨርጅን ሜሪ)። ይህ በዓል፣ የኢየሱስ እናት ሥጋዊ አካሏን ይዛ ወደ ሰማይ አርጋለች በሚለው እምነት ላይ የተመሠረተ ነው። ሪሊጅን ኤንድ ሶሳይቲ—ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ፋንዳሜንታሊዝም እንደሚገልጸው “እንዲህ ያለው እምነት በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዘንድ አይታወቅም ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ላይም ስለዚህ ጉዳይ አልተጠቀሰም።”
ፅንሰታ (ፊስት ኦቭ ዚ ኢማኩሌት ኮንሴፕሽን)። “መጽሐፍ ቅዱስ፣ [ማርያም] ያለኃጢአት ተፀንሳለች ብሎ በቀጥታ አያስተምርም። . . . ይህ የቤተ ክርስቲያኗ ትምህርት ነው።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ
ሁዳዴ (ሌንት)። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው፣ ይህ የንስሐና የጾም ጊዜ መከበር የጀመረው “በአራተኛው መቶ ዘመን” ነው፤ ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀ ከ200 ዓመት በኋላ ማለት ነው። ይኸው ኢንሳይክሎፒዲያ ሌንት የሚጀምርበትን ዕለት በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ምዕመናን አሽ ዌንስዴይ በተባለው ዕለት አመድ የሚቀቡበት ልማድ በስፋት ተቀባይነት ያገኘው በ1091 ከተካሄደው የቤኔቬንቶ ሲኖዶስ በኋላ ነው።”
መስቀል። ይህ የኢትዮጵያውያን በዓል የሚከበረው “እውነተኛው መስቀል (ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል) የተገኘበትን ዕለት ለማሰብ ነው፤ በዓሉ የሚከበረው ደመራ በመደመርና ዙሪያውን በመጨፈር ነው።” ይህን ያለው ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሶሳይቲ ኤንድ ካልቸር ኢን ዘ ሚዲቫል ወርልድ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ግን መስቀልን ለአምልኮ አይጠቀሙም።
በዓሉ ለአንድ ሰው፣ ድርጅት ወይም ብሔራዊ አርማ ክብር የሚሰጥ ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በሰዎች የሚታመን፣ በሰብዓዊ ኃይል የሚመካና ልቡ ከይሖዋ የራቀ ሰው የተረገመ ነው።’”—ኤርምያስ 17:5
የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች አክብሮት አላቸው፤ አልፎ ተርፎም ስለ እነሱ ይጸልያሉ፤ ይሁንና እንደሚከተሉት ባሉ ዝግጅቶች ወይም በዓላት ላይ አይሳተፉም።
በዓሉ ለአንድ ገዢ ወይም ታዋቂ ሰው ክብር የሚሰጥ ከሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለራሳችሁ ስትሉ፣ ከአፍንጫው እንደሚወጣ እስትንፋስ በሆነ ሰው አትታመኑ። ለመሆኑ እሱ ያን ያህል ቦታ እንዲሰጠው የሚያደርግ ምን ነገር አለ?” (ኢሳይያስ 2:22) ከዚህ አንጻር የይሖዋ ምሥክሮች የአንድን አገር መሪ ልደት አያከብሩም፤ ወይም እንዲህ በመሳሰሉ በዓላት ላይ አይሳተፉም።
በዓሉ ለአንድ አገር ባንዲራ ክብር የሚሰጥበት ከሆነ። የይሖዋ ምሥክሮች የባንዲራ ቀን አያከብሩም። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ “ከጣዖቶች ራቁ” ስለሚል ነው። (1 ዮሐንስ 5:21) በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ሰዎች፣ ባንዲራ ጣዖት ወይም የሚመለክ ነገር እንደሆነ አይሰማቸውም፤ የታሪክ ምሁር የሆኑት ካርልተን ሄይዝ ግን “የብሔራዊ ስሜት ዋነኛ የእምነት ምልክትና የአምልኮ መሣሪያ ባንዲራ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
በዓሉ ለቅዱሳን ክብር የሚሰጥ ከሆነ። አምላክን የሚፈራ አንድ ሰው ለሐዋርያው ጴጥሮስ በሰገደበት ወቅት ምን እንደተከሰተ እስቲ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ የተከሰተውን ሲገልጽ “ጴጥሮስ ግን ‘ተነስ፣ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ’ ብሎ አስነሳው” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 10:25, 26) ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ ሐዋርያት፣ ሰዎች የተለየ ክብር ሲሰጧቸው አልተቀበሉም፤ ከዚህ አንጻር የይሖዋ ምሥክሮች፣ ቅዱሳን ተደርገው ለሚቆጠሩ ሰዎች ክብር በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ አይካፈሉም። ለምሳሌ እንደሚከተሉት ያሉ በዓላትን አያከብሩም፦
የሁሉም ቅዱሳን ቀን (ኦል ሴንትስ ዴይ)። “ለሁሉም ቅዱሳን ክብር ለመስጠት የሚከበር በዓል ነው። . . . ይህ በዓል እንዴት እንደጀመረ በእርግጠኝነት አይታወቅም።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ
ፊዬስታ ኦቭ አወር ሌዲ ኦቭ ጉዋዳሉፔ (የጉዋዳሉፔ እመቤታችን በዓል)። ይህ በዓል “የሜክሲኮ ጠባቂ የሆነችው ቅድስት” የምትከበርበት ነው፤ አንዳንዶች፣ ይህች ቅድስት የኢየሱስ እናት ማርያም እንደሆነችና በ1531 ለአንድ ገበሬ በተአምር እንደተገለጠችለት ያምናሉ።—ዘ ግሪንዉድ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ላቲኖ ሊትሬቸር
ኔም ዴይ (የስም ቀን)። ይህ በዓል “አንድ ልጅ በተጠመቀበት ወይም ክርስትና በተነሳበት ዕለት ለሚከበረው ቅዱስ የሚዘጋጅ በዓል ነው።” ይህን ያለው ሰለብሬቲንግ ላይፍ ከስተምስ አራውንድ ዘ ወርልድ—ፍሮም ቤቢ ሻወርስ ቱ ፍዩነራልስ የተባለው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ አክሎ እንደተናገረው፣ ይህ በዓል “ሃይማኖታዊ ይዘት” ያለው በዓል ነው።
በዓሉ ፖለቲካዊ ወይም ማኅበራዊ ንቅናቄዎችን የሚደግፍ ከሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ “በሰው ከመታመን ይልቅ፣ ይሖዋን መጠጊያ ማድረግ ይሻላል” ይላል። (መዝሙር 118:8, 9) የይሖዋ ምሥክሮች የወጣቶች ቀን፣ የሴቶች ቀን ወይም እንዲህ የመሳሰሉ ፖለቲካዊ ወይም ማኅበራዊ ንቅናቄዎችን የሚደግፉ በዓላትን አያከብሩም፤ እንዲህ የማያደርጉት፣ ለዓለም ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣው አምላክ እንጂ የሰው ልጆች አይደሉም ብለው ስለሚያምኑ ነው። እንደ ኢማንሲፔሽን ዴይ (አንዳንድ አገሮች፣ ባርነት እንዲቆም የተወሰነበትን ዕለት ለማሰብ የሚያከብሩት በዓል ነው) ያሉትን መሰል በዓላት የማያከብሩትም በዚሁ ምክንያት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ዘረኝነት የሚወገደውና እኩልነት የሚሰፍነው በአምላክ መንግሥት አማካኝነት እንደሆነ ያምናሉ።—ሮም 2:11፤ 8:21
በዓሉ አንድን አገር ወይም ዘር ከሌላው ያስበልጣል?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35
የይሖዋ ምሥክሮች የትውልድ አገራቸውን ቢወዱም ከዚህ ቀጥሎ እንደተገለጹት ያሉ አንድን አገር ወይም ዘር ከሌላው የሚያስበልጡ በዓላትን አያከብሩም።
በዓሉ ለጦር ሠራዊት ክብር የሚሰጥ ከሆነ። ኢየሱስ ጦርነትን አላበረታታም፤ ከዚህ ይልቅ ተከታዮቹን “ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:44) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ከታች እንደተገለጹት ያሉ ለወታደሮች ክብር የሚሰጡ በዓላትን አያከብሩም፦
አንዛክ ዴይ። “አንዛክ ምህጻረ ቃል ሲሆን ፍቺው የአውስትራሊያ እና የኒው ዚላንድ ጦር ሠራዊት ማለት ነው።” አንዛክ ዴይ “ከጊዜ በኋላ በጦርነት የሞቱ ወታደሮች የሚታሰቡበት ዕለት ሆነ።”—ሂስቶሪካል ዲክሽነሪ ኦቭ አውስትራሊያ
የአርበኞች ቀን (ቬተራንስ ዴይ፣ ሪሜምበራንስ ዴይ፣ ሪሜምበራንስ ሰንዴይ ወይም ሜሞሪያል ዴይ)። እነዚህ በዓላት የሚከበሩት “ለጦር አርበኞችና ጦር ሜዳ ለሞቱት” ክብር ለመስጠት ሲባል ነው።—ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ
በዓሉ ከአንድ አገር ታሪክ ወይም የነፃነት ቀን ጋር የተያያዘ ከሆነ። ኢየሱስ ተከታዮቹን በተመለከተ “እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:16) የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አንድ አገር ታሪክ ማወቅ ቢያስደስታቸውም ቀጥሎ እንደተጠቀሱት ባሉ ዝግጅቶች ላይ አይሳተፉም፦
አውስትራሊያ ዴይ። ወርልድማርክ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ካልቸርስ ኤንድ ዴይሊ ላይፍ እንደገለጸው ይህ በዓል የሚከበረው “በ1788 የእንግሊዝ ወታደሮች በአውስትራሊያ ምድር ባንዲራቸውን ያውለበለቡበትንና አውስትራሊያ አዲስ ቅኝ ግዛት መሆኗን ያወጁበትን ዕለት” ለማሰብ ነው።
ጋይ ፎውክስ ዴይ። ይህ በዓል “ብሔራዊ በዓል ነው፤ ጋይ ፎውክስ እና የካቶሊክ እምነት ደጋፊዎች በ1605 ንጉሥ ቀዳማዊ ጄምስንና [የእንግሊዝ] ፓርላማን ለመደምሰስ ያደረጉት የከሸፈ ሙከራ የሚታሰብበት በዓል ነው።”—ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ኢንግሊሽ ፎልክሎር
የነፃነት ቀን (ኢንዲፔንደንስ ዴይ)። በብዙ አገሮች፣ ይህ በዓል “አገሪቱ ነፃ የወጣችበትን ቀን ለማሰብ በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው።”—ሜሪያም ዌብስተርስ አነብሪጅድ ዲክሽነሪ
በዓሉ ላይ መረን የለቀቀ ወይም ነውረኛ ምግባር ይታያል?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅባቸው ድርጊቶች በመፈጸም፣ ልቅ በሆነ የሥጋ ፍላጎት፣ ከልክ በላይ በመጠጣት፣ መረን በለቀቀ ድግስ፣ በመጠጥ ግብዣዎችና በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ በመካፈል የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ጊዜ ይበቃል።”—1 ጴጥሮስ 4:3
የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መመሪያ ስለሚከተሉ የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ ከሚጠጣባቸውና መረን የለቀቀ ድግስ ከሚደረግባቸው በዓላት ይርቃሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ከወዳጆቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስታቸዋል፤ አንዳንድ ጊዜም የአልኮል መጠጦችን በመጠኑ ለመጠጣት ሊመርጡ ይችላሉ። “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” የሚለውን ምክር ለመከተል የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።—1 ቆሮንቶስ 10:31
በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዛቸው ልቅ የሆኑ ድርጊቶች በሚታዩባቸው ካርኒቫሎች ወይም መሰል በዓላት ላይ አይሳተፉም። ፑሪም የተባለው የአይሁዳውያን በዓል ለዚህ አንዱ ምሳሌ ነው። እርግጥ ነው፣ ፑሪም ከጥንት ጊዜ አንስቶ ይከበር የነበረው አይሁዳውያን በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ. ነፃ የወጡበትን ጊዜ ለማሰብ ነው፤ አሁን ግን ኢሴንሻል ጁዳይዝም የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “በአይሁዳውያን ዘንድ እንደ ማርዲ ግራ ወይም እንደ ካርኒቫል የሚከበር በዓል” ሆኗል። በዓሉ ላይ “ወጣ ያሉ አልባሳትን መልበስ (ብዙውን ጊዜ ወንዶች የሴቶች ልብስ ይለብሳሉ)፣ ነውጠኛ ባሕርይ ማሳየት፣ ከልክ በላይ መጠጣትና መጮህ” የተለመደ ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ በዓላትን አለማክበራቸው ቤተሰባቸውን እንደማይወዱ ያሳያል?
አያሳይም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እምነታቸው ምንም ይሁን ምን ሁሉንም የቤተሰባችንን አባላት መውደድና ማክበር እንዳለብን ያስተምረናል። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2, 7) እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር ሲሆንና በአንዳንድ በዓላት ላይ መካፈሉን ሲያቆም አንዳንድ ዘመዶቹ ሊከፋቸው፣ ቅር ሊሰኙ ወይም እንደተከዱ ሊሰማቸው ይችላል። በመሆኑም ብዙዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ቅድሚያውን ወስደው ቤተሰቦቻቸውን እንደሚወዷቸው ያረጋግጡላቸዋል፤ በዓል ላለማክበር የወሰኑበትን ምክንያት በአክብሮት ያስረዷቸዋል እንዲሁም ከበዓል ጊዜ ውጭ ባሉ ሌሎች ወቅቶች ላይ ሄደው ይጠይቋቸዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሌሎች ሰዎች በዓላትን እንዳያከብሩ ይከለክላሉ?
አይከለክሉም። እያንዳንዱ ሰው የግሉን ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት ይገነዘባሉ። (ኢያሱ 24:15) ሰዎች ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን፣ የይሖዋ ምሥክሮች ‘ሁሉንም ዓይነት ሰው ያከብራሉ።’—1 ጴጥሮስ 2:17