የይሖዋ ምሥክሮች ከፍቅር ጓደኝነት ጋር በተያያዘ የሚከተሉት መመሪያ አላቸው?
የይሖዋ ምሥክሮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችና ደንቦች አምላክን የሚያስደስቱና ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን ለማድረግ እንደሚረዷቸው ያምናሉ። (ኢሳይያስ 48:17, 18) እነዚህን መመሪያዎችና ደንቦች ያወጣናቸው እኛ ባንሆንም እንመራባቸዋለን። የፍቅር ጓደኛ ከመመሥረት ጋር በተያያዘ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን መመሪያዎች እንዳሉ እስቲ እንመልከት። a
ትዳር ዘላቂ ጥምረት ነው። (ማቴዎስ 19:6) የይሖዋ ምሥክሮች የፍቅር ጓደኛ መያዝን ትዳር ለመመሥረት እንደሚወሰድ አንድ እርምጃ አድርገው ይቆጥሩታል፤ በዚህም የተነሳ አክብደው ይመለከቱታል።
የፍቅር ጓደኛ መያዝ ያለባቸው ለጋብቻ የደረሱ ሰዎች ብቻ ናቸው። እነዚህ ሰዎች “አፍላ የጉርምስና ዕድሜን” ማለትም የፆታ ስሜት የሚያይልበትን ዕድሜ ያለፉ ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 7:36
የፍቅር ጓደኛ የሚይዙ ሰዎች የማግባት ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል። አንዳንዶች በሕግ ቢፋቱም እንኳ በአምላክ እይታ እንደገና የማግባት ነፃነት የላቸውም፤ ምክንያቱም በአምላክ መሥፈርት መሠረት ትዳርን ለማፍረስ ምክንያት ሊሆን የሚችለው የፆታ ብልግና ብቻ ነው።—ማቴዎስ 19:9
ክርስቲያኖች ትዳር መመሥረት ያለባቸው የእነሱን እምነት ከሚጋራ ሰው ጋር ብቻ መሆን እንዳለበት ታዘዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ይህን ትእዛዝ መሠረት በማድረግ፣ ለትዳር የምናስበው ሰው እንዲሁ የምናምንበትን ነገር የሚያከብርልን ብቻ ሳይሆን እምነታችንን የሚጋራና በመጽሐፍ ቅዱስ የሚመራ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር መሆን እንዳለበት እናምናለን። (2 ቆሮንቶስ 6:14) አምላክ አገልጋዮቹ በትዳር መጣመር የሚኖርባቸው ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር ብቻ ሊሆን እንደሚገባ አዟል። (ዘፍጥረት 24:3፤ ሚልክያስ 2:11) የዚህን ትእዛዝ ጠቃሚነት በዘመናችን ያሉ ተመራማሪዎችም ደርሰውበታል። b
ልጆች ወላጆቻቸውን ሊታዘዙ ይገባል። (ምሳሌ 1:8፤ ቆላስይስ 3:20) ከወላጆቻቸው ጋር አብረው የሚኖሩ ልጆች ደግሞ፣ ወላጆቻቸው የፍቅር ጓደኛ ከመያዝ ጋር በተያያዘ ያወጧቸውን መመሪያዎችም መታዘዝ ይጠበቅባቸዋል። ከእነዚህ መካከል፣ አንድ ልጅ የፍቅር ጓደኛ መያዝ የሚችልበትን ዕድሜ እንዲሁም ምን ምን ነገሮችን ማድረግ እንደሚፈቀድለት የሚጠቁሙ መመሪያዎች ይገኙበታል።
የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች እስካልጣሱ ድረስ፣ የፍቅር ጓደኝነት ከመጀመር እንዲሁም ለጓደኝነት ከሚመርጡት ሰው ጋር በተያያዘ የራሳቸውን ውሳኔ ያደርጋሉ። ይህም “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” ከሚለው መመሪያ ጋር የሚስማማ ነው። (ገላትያ 6:5) ያም ሆኖ ብዙዎች የፍቅር ጓደኝነት ከመመሥረታቸው በፊት፣ ከልብ የሚያስቡላቸውን ብስለት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በማማከር ጥበበኛ መሆናቸውን አሳይተዋል።—ምሳሌ 1:5
ብዙ ሰዎች ከፍቅር ጓደኛቸው ጋር የሚፈጽሟቸው አንዳንድ ድርጊቶች ከባድ ኃጢአት ናቸው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ከፆታ ብልግና እንድንርቅ ያዛል። ይህ ደግሞ የፆታ ግንኙነት መፈጸምን ብቻ ሳይሆን የሌላን ሰው የፆታ ብልት ማሻሸትንና በአፍ ወይም በፊንጢጣ ወሲብ መፈጸምን የመሰሉ ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚደረጉ ርኩስ ድርጊቶችን ያካትታል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) አንድ ሰው የፆታ ግንኙነት ባይፈጽምም እንኳ የትዳር ጓደኛው ያልሆነን ሰው የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ነገር ማድረጉ “ርኩሰት” እንደ መፈጸም የሚቆጠር ሲሆን ይህ ደግሞ አምላክን ያሳዝናል። (ገላትያ 5:19-21) መጽሐፍ ቅዱስ “ጸያፍ ንግግር” ያዘሉ የብልግና ወሬዎችንም ያወግዛል።—ቆላስይስ 3:8
ልባችን ማለትም ውስጣዊ ማንነታችን አታላይ ነው። (ኤርምያስ 17:9) አንድ ሰው ስህተት እንደሆኑ የሚያውቃቸውን ነገሮች እንዲፈጽም ልቡ ሊገፋፋው ይችላል። የፍቅር ጓደኝነት የመሠረቱ ሰዎች ልባቸው እንዳያታልላቸው ሲሉ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ብቻቸውን ጊዜ ከማሳለፍ ይቆጠባሉ። በቡድን በመዝናናት አሊያም ደግሞ ሌላ ሰው አብሯቸው እንዲሆን በማድረግ የጥንቃቄ እርምጃ ይወስዳሉ። (ምሳሌ 28:26) ያላገቡ ክርስቲያኖች፣ ትዳር ፈላጊዎችን የሚያገናኙ ድረ ገጾችን መጠቀም ያለውን አደጋ ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ በተለይ ደግሞ እምብዛም ከማያውቁት ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመር የከፋ መዘዝ እንዳለው ይገነዘባሉ።—መዝሙር 26:4
a በአንዳንድ ባሕሎች የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት የተለመደ ነው፤ በሌሎች ባሕሎች ግን እንዲህ ዓይነት ልማድ ላይኖር ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ በፊት የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ አይናገርም።
b ለምሳሌ ያህል፣ ሜሬጅ ኤንድ ፋሚሊ ሪቪው በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሮ ነበር፦ “ለረጅም ዓመታት በዘለቁ ትዳሮች ላይ የተደረጉ ሦስት የተለያዩ ጥናቶች እንዳሳዩት፣ ዘላቂ ለሆነ ትዳር (ከ25-50 ዓመትና ከዚያ በላይ) ቁልፉ ጥንዶቹ በሃይማኖታዊ አቋማቸውና በሚያምኑባቸው ነገሮች ረገድ መመሳሰላቸው ነው።”—ጥራዝ 38፣ እትም 1፣ ገጽ 88 (2005)