መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
ሕይወቴ ከቁጥጥሬ ውጭ ነበር
የትውልድ ዘመን፦ 1971
የትውልድ አገር፦ ቶንጋ
የኋላ ታሪክ፦ ዕፅ ይወስድ የነበረና እስር ቤት ገብቶ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ
ተወልጄ ያደግኩት ቶንጋ ነው፤ ቶንጋ 170 ደሴቶች ያሏት በደቡብ ምዕራብ ፓስፊክ የምትገኝ አገር ናት። በቶንጋ ስንኖር ኤሌክትሪክንና መኪናን ጨምሮ ብዙ ቁሳዊ ነገር አልነበረንም። ያም ቢሆን የቧንቧ ውኃ ነበረን፤ እንዲሁም ጥቂት ዶሮዎች ነበሩን። ትምህርት ቤት ሲዘጋ እኔና ሁለት ወንድሞቼ አባታችንን በእርሻ ሥራ እናግዘው ነበር፤ እርሻው ላይ ሙዝና ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ ሥራ ሥሮችን ተክለን ነበር። አባቴ ቤተሰባችንን የሚያስተዳድረው እነዚህን ምርቶች በመሸጥና አንዳንድ ተባራሪ ሥራዎችን በመሥራት ነበር። በደሴቶቹ ላይ እንደሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ ቤተሰባችንም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት ነበረው፤ እንዲሁም አዘውትረን ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ነበር። ያም ቢሆን ጥሩ ሕይወት መምራት ከፈለግን ወደበለጸገ አገር መሄድ እንደሚያስፈልገን ይሰማን ነበር።
አሥራ ስድስት ዓመት ሲሞላኝ አጎቴ ወደ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደን እንድንኖር ሁኔታዎችን አመቻቸልን። እዚያ ስንሄድ ባሕሉን መልመድ በጣም ከብዶን ነበር። ኑሯችን በተወሰነ መጠን ቢሻሻልም የምንኖርበት አካባቢ ድህነት፣ ወንጀልና ዕፅ የተስፋፋበት ነበር። ብዙ ጊዜ ማታ ማታ ተኩስ እንሰማ ነበር፤ አብዛኞቹ ጎረቤቶቻችን የወንጀለኛ ቡድኖችን ይፈሩ ነበር። ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከልና ግጭቶችን ለመፍታት ሲሉ መሣሪያ ይታጠቁ ነበር። እንዲህ ባለ ግጭት ምክንያት የተተኮሰብኝ ጥይት አሁንም ድረስ ደረቴ ውስጥ አለ።
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ እንደ ሌሎቹ ወጣቶች መሆን እፈልግ ነበር። በመሆኑም መረን በለቀቁ ግብዣዎች ላይ መገኘት፣ ከልክ በላይ መጠጣት፣ በዓመፅ ድርጊቶች መካፈል እንዲሁም ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ። ውሎ አድሮ የኮኬይን ሱሰኛ ሆንኩ። ዕፅ ለመግዛት ስል ደግሞ መስረቅ ጀመርኩ። ቤተሰቦቼ አዘውትረው ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን መጥፎ ነገር እንዳደርግ የሚደርስብኝን ጫና ለመቋቋም የሚረዳ ምክር አላገኘሁም። የዓመፅ ድርጊቶች በመፈጸሜ ምክንያት ብዙ ጊዜ ፖሊስ ይይዘኝ ነበር። ሕይወቴ ከቁጥጥሬ ውጭ ነበር! በስተ መጨረሻ ወህኒ ወረድኩ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
በ1997 እስር ቤት ሳለሁ አንድ እስረኛ መጽሐፍ ቅዱስ በእጄ እንደያዝኩ አስተዋለ። ወቅቱ የገና በዓል የሚከበርበት ጊዜ ነበር፤ ገና ለቶንጋ ነዋሪዎች በጣም ቅዱስ በዓል ነው። እስረኛው፣ ኢየሱስ ስለተወለደበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል አውቅ እንደሆነ ጠየቀኝ፤ እኔ ግን ስለ ጉዳዩ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ኢየሱስ ልደት የሚናገረውን ዘገባ አሳየኝ፤ በገና በዓል ላይ የሚደረጉት አብዛኞቹ ልማዶች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሌሉ አስተዋልኩ። (ማቴዎስ 2:1-12፤ ሉቃስ 2:5-14) በጣም ስለገረመኝ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ሌላስ ምን ያስተምር ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። ሰውየው የይሖዋ ምሥክሮች እስር ቤት ውስጥ በየሳምንቱ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ይገኝ ነበር፤ እኔም አብሬው ለመሄድ ወሰንኩ። በወቅቱ የሚወያዩት በራእይ መጽሐፍ ላይ ነበር። የሚናገሩት ነገር ብዙም ባይገባኝም ትምህርታቸው በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ተገነዘብኩ።
የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ያቀረቡልኝን ግብዣ በደስታ ተቀበልኩ። ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ያኔ ነው። (ኢሳይያስ 35:5-8) አምላክን ማስደሰት ከፈለግኩ በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ተረዳሁ። ይሖዋ አምላክ መጥፎ አኗኗሬን ይዤ ወደ ገነት እንድገባ እንደማይፈቀድልኝ ግልጽ ሆነልኝ። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) በመሆኑም ቁጣዬን ለመቆጣጠር እንዲሁም ከሲጋራ፣ ከመጠጥና ከዕፅ ሱስ ለመላቀቅ ቆረጥኩ።
የእስር ፍርዴን ሳላጠናቅቅ በ1999 ወደ ስደተኞች መጠለያ ተላክሁ። ለአንድ ዓመት ያህል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት አልቻልኩም ነበር። ሆኖም ሕይወቴን ለማስተካከል ቆርጬ ነበር። በ2000 መንግሥት የመኖሪያ ፈቃዴን ስለቀማኝ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ቶንጋ ተላክሁ።
ቶንጋ ስመለስ ወዲያውኑ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጌ ጥናቴን ቀጠልኩ። ትምህርቱን ወደድኩት፤ ልክ ዩናይትድ ስቴትስ እንደነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ ቶንጋ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮችም ትምህርታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ስመለከት በጣም ተደነቅኩ።
አባቴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥልጣን ስላለው በማኅበረሰቡ ውስጥ አክብሮት ያተረፈ ሰው ነበር። ስለዚህ መጀመሪያ አካባቢ ቤተሰቦቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በማጥናቴ ይገረሙ እንዲያውም ይበሳጩ ነበር። በኋላ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ሕይወቴን ለማስተካከል እንደረዱኝ ሲመለከቱ ወላጆቼ ተደሰቱ።
ለውጥ ለማድረግ በጣም ከተቸገርኩባቸው ነገሮች አንዱ በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ከልክ በላይ የሚጠጡትን አንድ መጠጥ መተው ነበር። ብዙ የቶንጋ ወንዶች ካቫ የተባለ የሚያደነዝዝ መጠጥ በመጠጣት በየሳምንቱ ብዙ ሰዓት ያጠፋሉ። ስለዚህ ወደ ትውልድ አገሬ ስመለስ እኔም በየቀኑ ምሽት ላይ ካቫ ወደሚቀርብበት መጠጥ ቤት እየሄድኩ ራሴን እስክስት ድረስ እጠጣ ነበር። ለዚህ የዳረገኝ አንዱ ነገር የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ከማያከብሩ ሰዎች ጋር መወዳጀቴ ነው። በጊዜ ሂደት ግን ይህ ልማድ አምላክን እንደሚያሳዝነው ተማርኩ። በመሆኑም የአምላክን በረከትና ሞገሱን ማግኘት እንድችል ለውጥ አደረግኩ።
የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ይሖዋን ለማስደሰት ከሚጥሩ ሰዎች ጋር መቀራረቤ ፈተናዎችን ለማሸነፍ ረድቶኛል። በ2002 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ያገኘሁት ጥቅም
አምላክ ታጋሽ መሆኑ በጣም ጠቅሞኛል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው” ይላል። (2 ጴጥሮስ 3:9) አምላክ ይህን ብልሹ ሥርዓት ከረጅም ጊዜ በፊት ሊያጠፋው ይችል ነበር፤ ሆኖም በመታገሡ እንደ እኔ ያሉ ሰዎች ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ችለዋል። ሌሎችም ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንዲችሉ ለመርዳት እኔን ሊጠቀምብኝ እንደሚችል ይሰማኛል።
ይሖዋ ስለረዳኝ ሕይወቴን መልሼ መቆጣጠር ችያለሁ። አሁን ጎጂ የሆነ ልማዴን ለማርካት አልሰርቅም። ከዚህ ይልቅ ጎረቤቶቼም የይሖዋ ወዳጆች እንዲሆኑ ለመርዳት ጥረት አደርጋለሁ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ወዳጅነት በመመሥረቴ በጣም የምወዳት ባለቤቴን ቲያን ማግኘት ችያለሁ። ከልጃችን ጋር ሆነን አስደሳች ሕይወት እንመራለን። መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ሰላም በሰፈነበት ገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር እንደምንችል የሚሰጠውን ተስፋ ለሌሎች እናሳውቃለን።