መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
“አሁን የዓመፅ ባሪያ አይደለሁም”
የትውልድ ዘመን፦ 1956
የትውልድ አገር፦ ካናዳ
የኋላ ታሪክ፦ በሕይወቱ ግራ የተጋባ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ይመራ የነበረ እና ጠበኛ
የቀድሞ ሕይወቴ
የተወለድኩት አልበርታ፣ ካናዳ ውስጥ በምትገኘው በካልጋሪ ከተማ ነው። ሕፃን እያለሁ ወላጆቼ ተፋቱ፤ በመሆኑም እኔና እናቴ በአያቶቼ ቤት መኖር ጀመርን። አያቶቼ እኔንም ሆነ እናቴን ይወዱን ነበር፤ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። አስደሳች ስለሆነው ያ የልጅነት ጊዜዬ አሁንም ድረስ ጥሩ ትዝታዎች አሉኝ።
ሰባት ዓመት ሲሆነኝ እናቴና አባቴ እንደገና የተጋቡ ሲሆን በሚዙሪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ወዳለችው ወደ ሴንት ሉዊስ ተዛወርን፤ ከዚያ በኋላ ሕይወቴ ፈተና የበዛበት ሆነ። የአባቴን ጭካኔ ማስተዋል የጀመርኩት በዚህ ጊዜ ነው። ለምሳሌ አዲሱ ትምህርት ቤቴ በገባሁበት ዕለት ልጆች እንደመቱኝና መልሼ እንዳልተደባደብኩ አባቴ አወቀ። አባቴ በዚህ በጣም ስለተናደደ ከልጆቹ የበለጠ ደበደበኝ! እኔም ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ገና በሰባት ዓመቴ መደባደብ ጀመርኩ።
እናቴም በአባቴ ግልፍተኝነት ተማርራ ነበር፤ ብዙ ጊዜ የጦፈ ግጭት ውስጥ ይገቡ ነበር። በ11 ዓመቴ ዕፅ መውሰድና መጠጥ መጠጣት ጀመርኩ። ይበልጥ ጠበኛ እየሆንኩ ሄድኩ፤ ብዙ ጊዜም መንገድ ላይ እደባደብ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ የለየለት ጠበኛ ሰው ሆኜ ነበር።
በ18 ዓመቴ በዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ኃይል ውስጥ ለማገልገል ተመለመልኩ። በዚያም የሰውን ሕይወት ማጥፋት ስለሚቻልበት መንገድ ተማርኩ። ከአምስት ዓመት በኋላ ውትድርናን ለቅቄ ወጣሁ፤ እንዲህ ያደረግኩት በፌደራል የምርመራ ቢሮ (FBI) ውስጥ ሥራ ለማግኘት የሚያስችለኝን የሥነ ልቦና ትምህርት ለመከታተል ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ ባለ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርቱን ከጀመርኩ በኋላ ወደ ካናዳ ተመልሼ መማሬን ቀጠልኩ።
ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ በሰው ዘርና በማኅበረሰቡ ላይ የነበረኝ ተስፋ ሙሉ በሙሉ ጠፋ። ሰዎች በጣም ራስ ወዳድ እንደሆኑ፣ በዓለም ላይ የሚታየው ነገር ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰው ዘር ችግሮች መፍትሔ እንደሌላቸው ይሰማኝ ጀመር። የሰው ልጆች ዓለምን የተሻለ ቦታ እንደሚያደርጓት የነበረኝ ተስፋ ጠፋ።
የሕይወትን ትርጉም ባለማግኘቴ ዕፅ በመውሰድ፣ ከልክ በላይ በመጠጣት፣ ገንዘብ በማሳደድና የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት ጀመርኩ። ፈንጠዝያ ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ እገኝ እንዲሁም ከተለያዩ ሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት እፈጽም ነበር። ባገኘሁት ወታደራዊ ሥልጠና በመተማመን ብዙ ጊዜ እደባደብ ነበር። ትክክል ነው ብዬ ለማስበው ነገር ስል ሌሎችን እንደበደለ በሚሰማኝ በማንኛውም ሰው ላይ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አልልም ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እኔ ራሴ የጠበኝነት ዝንባሌ ተቆጣጥሮኝ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
አንድ ቀን በመኖሪያ ቤቴ በሚገኝ ምድር ቤት ውስጥ እኔና አንድ ጓደኛዬ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የምንሸጠውን ዕፅ እያዘጋጀን ነበር፤ ሁለታችንም ዕፅ ወስደን ነበር፤ በዚህ ጊዜ ጓደኛዬ በአምላክ መኖር አምን እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም “በዓለም ላይ ለሚታየው መከራ ተጠያቂው አምላክ ከሆነ ስለ እሱ ማወቅ አልፈልግም!” ብዬ መለስኩለት። በቀጣዩ ቀን ማለትም አዲስ ሥራ በጀመርኩበት ዕለት፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ የሥራ ባልደረባዬ “በዓለም ላይ ለሚታየው መከራ ተጠያቂው አምላክ ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። ይሄው ጉዳይ ከአንድ ቀን በፊት ተነስቶ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ጥያቄው በጣም አስገረመኝ፤ የጥያቄውን መልስ ለማወቅም ጓጓሁ። በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ከዚህ ሰው ጋር ብዙ የተወያየን ሲሆን ስለ ሕይወት ለነበሩኝ አንዳንድ ከባድ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ሰጠኝ።
በወቅቱ አብራኝ ትኖር የነበረችው እጮኛዬ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምማረውን ነገር እንድነግራት ፈቃደኛ አልነበረችም። አንድ ቀን እሁድ ዕለት፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኑን ቤታችን እንደጋበዝኳቸው ነገርኳት። በቀጣዩ ቀን ከሥራ ስመለስ እጮኛዬ ቤቱ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ሙልጭ አድርጋ ወስዳ ትታኝ ሄዳለች። ወደ ውጭ ወጥቼ አለቀስኩ። አምላክ እንዲረዳኝም ጸለይኩ። አምላክን ይሖዋ በተባለው የግል ስሙ ጠርቼ ለመጀመሪያ ጊዜ የጸለይኩት በዚህ ወቅት ነው።—መዝሙር 83:18
ከሁለት ቀናት በኋላ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። እነሱ ከሄዱ በኋላ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን የማጥኛ መጽሐፍ ማንበቤን ቀጠልኩ፤ የዚያኑ ዕለት ምሽት አንብቤው ጨረስኩ። a ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የተማርኩት ነገር ልቤን ነካው። ይሖዋ ሩኅሩኅ እንደሆነና መከራ ሲደርስብን እንደሚያዝን ተረዳሁ። (ኢሳይያስ 63:9) በተለይ ደግሞ አምላክ ያሳየኝን ፍቅርና ልጁን ለእኔ ሲል መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱን ማወቄ በጥልቅ ነካኝ። (1 ዮሐንስ 4:10) ይሖዋ የታገሠኝ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ” እንደሆነ ተገነዘብኩ። (2 ጴጥሮስ 3:9) ይሖዋ ወደ ራሱ እየሳበኝ እንደሆነ ተሰማኝ።—ዮሐንስ 6:44
በዚያው ሳምንት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በወቅቱ ፀጉሬን አስረዝሜ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የጆሮ ጉትቻ አደርግ ነበር፤ ከዚህም ሌላ መልኬ ያስፈራ ነበር፤ የይሖዋ ምሥክሮቹ ግን ከረጅም ጊዜ በኋላ እንዳገኙት ዘመድ ተቀበሉኝ። ድርጊታቸው እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ያሳይ ነበር። ወደ አያቶቼ ቤት የሄድኩ ያህል ተሰማኝ፤ ሁኔታው ግን በአያቶቼ ቤት ከነበረውም የላቀ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኩትን ነገር በሕይወቴ ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ። ፀጉሬን ተቆረጥኩ፤ የፆታ ብልግና መፈጸሜን አቆምኩ፤ እንዲሁም ዕፅ መውሰዴንና ከልክ በላይ መጠጣቴን ተውኩ። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 11:14) ይሖዋን ማስደሰት ፈልጌ ነበር። በመሆኑም አንድ የማደርገው ነገር በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ሳውቅ ያንን ነገር ላለመተው ሰበብ አልደረድርም። ከዚህ ይልቅ በድርጊቱ በጣም አዝን ነበር። ዳግመኛ እንደዚያ ላለማድረግ ለራሴ ቃል እገባለሁ። ከዚያም ያለምንም ማመንታት አስተሳሰቤንና ድርጊቴን ለማስተካከል እጥር ነበር። በዚህም የተነሳ የይሖዋን መሥፈርቶች ማክበር ያለውን ጥቅም በሕይወቴ ውስጥ በደንብ ማየት ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመርኩ ከስድስት ወር በኋላ ማለትም ሐምሌ 29, 1989 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ያገኘሁት ጥቅም
መጽሐፍ ቅዱስ ማንነቴን ለመቀየር ረድቶኛል። ቀደም ባለው ጊዜ አንድ ሰው ሊጣላኝ ቢፈልግ ብዙውን ጊዜ ለጠብ እጋበዝ ነበር። አሁን ግን “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር” ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ። (ሮም 12:18) ይህን ሁሉ ለውጥ ማድረግ የቻልኩት በራሴ ጥረት ሳይሆን ይሖዋ በቃሉና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ኃይል ስለሰጠኝ ነው፤ በመሆኑም ምስጋና የሚገባው እሱ ነው።—ገላትያ 5:22, 23፤ ዕብራውያን 4:12
በአሁኑ ጊዜ የዕፅ፣ የዓመፅና የመጥፎ ምኞቶች ባሪያ አይደለሁም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ አምላክን ለማስደሰትና ለእሱ ምርጤን ለመስጠት እየጣርኩ ነው። ይህም ሌሎች ስለ እሱ እንዲያውቁ መርዳትን ይጨምራል። ከተጠመቅኩ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ስል ወደ ሌላ አገር ተዛወርኩ። ባለፉት ዓመታት በርካታ ሰዎችን የማስተማር እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተግባራዊ በማድረጋቸው ሕይወታቸው ሲለወጥ የማየት መብት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። በተጨማሪም እናቴ የይሖዋ ምሥክር መሆኗ በጣም አስደስቶኛል፤ ይህን ውሳኔ እንድታደርግ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አስተዋጽኦ ያደረገው በአመለካከቴም ሆነ በምግባሬ ላይ ያደረግኩትን ጥሩ ለውጥ መመልከቷ ነው።
በ1999 ኤል ሳልቫዶር ውስጥ በአሁኑ ወቅት የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተብሎ ከሚጠራው ትምህርት ቤት ተመረቅኩ። ይህ ትምህርት ቤት፣ በወንጌላዊነቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆኜ መሳተፍ እንድችል እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ የማስተማርና የእረኝነት ኃላፊነቴን እንድወጣ አሠልጥኖኛል። በዚያው ዓመት በኋላ ላይ ውዷ ባለቤቴን ዩሄኒያን አገባሁ። በአሁኑ ጊዜ ጓቴማላ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ሆነን እያገለገልን ነው።
አሁን በሕይወት ግራ የተጋባሁ ሰው አይደለሁም፤ ከዚህ ይልቅ በጣም ደስተኛ ነኝ። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረጌ ከፆታ ብልግናና ከጠበኝነት ነፃ ያወጣኝ ሲሆን እውነተኛ ፍቅርና ሰላም የሞላበት ሕይወት እንዲኖረኝ ረድቶኛል።
a በአሁኑ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሙት ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው የማጥኛ መጽሐፍ ነው።