መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
እውነተኛ ሀብት አገኘሁ
የትውልድ ዘመን፦ 1968
የትውልድ አገር፦ ዩናይትድ ስቴትስ
የኋላ ታሪክ፦ ሀብታም ለመሆን ይጸልይ የነበረ የንግድ ኃላፊ
የቀድሞ ሕይወቴ
ያደግኩት በሮችስተር፣ ኒው ዮርክ ሲሆን ካቶሊክ ነበርኩ። የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ ተለያዩ። ስለዚህ በሳምንቱ ቀናት ከእናቴ ጋር ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት አፓርታማ፣ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ከአባቴ ጋር በሀብታሞች ሰፈር እኖር ነበር። እናቴ እኔን ጨምሮ ስድስት ልጆችን ለማሳደግ ምን ያህል እንደምትለፋ ሳይ ሀብታም ሆኜ ቤተሰቤን መርዳት ሕልሜ ሆነ።
አባቴ በሕይወቴ ስኬታማ እንድሆን ይፈልግ ስለነበር ስመ ጥር የሆነን አንድ የሆቴል አስተዳደር ትምህርት ቤት እንድጎበኝ አመቻቸልኝ። ትምህርት ቤቱን ስለወደድኩት ወዲያው ተመዘገብኩ፤ አምላክ ሀብታምና ደስተኛ እንድሆን ያቀረብኩትን ጸሎት እየመለሰልኝ እንዳለ ተሰማኝ። ለአምስት ዓመት ያህል የሆቴል አስተዳደር፣ የንግድ ሕግና ፋይናንስ አጠናሁ፤ በዚህ ወቅት በላስ ቬጋስ፣ ኔቫዳ ባለ ቁማር የሚያጫውት ሆቴል ውስጥም እሠራ ነበር።
በ22 ዓመቴ፣ ቁማር የሚያጫውት አንድ ሆቴል ረዳት ምክትል ፕሬዚደንት ሆንኩ። በብዙዎች ዘንድ ሀብታምና ስኬታማ ተደርጌ እቆጠር ነበር፤ ምርጥ ምግቦችን እመገብ እንዲሁም በጣም ውድ የወይን ጠጆችንና መጠጦችን እጠጣ ነበር። በሥራ የማውቃቸው ጓደኞቼ “ዓለምን የሚያሽከረክረው ገንዘብ ነው፤ በእሱ ላይ ትኩረት አድርግ” ይሉኝ ነበር። በእነሱ አመለካከት ለእውነተኛ ደስታ ሚስጥሩ ገንዘብ ነው።
ሥራዬ ቁማር ለመጫወት ወደ ላስ ቬጋስ የሚመጡትን በጣም ሀብታም ሰዎች ማስተናገድን ይጨምር ነበር። እነዚህ ሰዎች ሀብታም ቢሆኑም ደስተኛ አይመስሉም ነበር። እኔም ደስታዬን ማጣት ጀመርኩ። እንዲያውም ይበልጥ ገንዘብ ባገኘሁ መጠን ይበልጥ እየተጨነቅኩ መጣሁ፤ እንቅልፍ አጥቼ የማድርባቸው ሌሊቶችም እየበዙ ሄዱ። በዚህ መልኩ በሕይወት መኖሬን መቀጠል ምንም ትርጉም እንደሌለው ማሰብ ጀመርኩ። በሕይወቴ ግራ ስለተጋባሁ አምላክን “እውነተኛ ደስታ የማገኘው ከየት ነው?” ብዬ ጠየቅኩት።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሁለት እህቶቼ በዚያው ሰሞን ወደ ላስ ቬጋስ ተዛወሩ። የሚሰጡኝን ጽሑፎች ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆንም አብሬያቸው የራሴን መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ተስማማሁ። እኔ በያዝኩት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኢየሱስ የተናገራቸው ሐሳቦች በቀይ ተጽፈው ነበር። ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ሁሉ እቀበል ስለነበር እህቶቼ በዋነኝነት እሱ በተናገራቸው ሐሳቦች ላይ ያተኩሩ ነበር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ለብቻዬ አነብ ነበር።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበብኳቸው በርካታ ነገሮች በጣም አስገረሙኝ። ለምሳሌ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ፤ እነሱ ቃላት በማብዛት ጸሎታቸው የሚሰማላቸው ይመስላቸዋል።” (ማቴዎስ 6:7) አንድ ቄስ የኢየሱስን ምስል ከሰጠኝ በኋላ ምስሉን እያየሁ አሥር አባታችን ሆይና አሥር ውዳሴ ማርያም ከደገምኩ አምላክ የፈለግኩትን ያህል ገንዘብ እንደሚሰጠኝ ነግሮኝ ነበር። አንድ ዓይነት ቃላትን አሥሬ መደጋገም ማለት ማነብነብ ማለት አይደል? በተጨማሪም “አባታችሁ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ” የሚለውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ አነበብኩ። (ማቴዎስ 23:9) ‘ታዲያ እኔም ሆንኩ ሌሎች የካቶሊክ አማኞች ቀሳውስታችንን “አባ” ብለን የምንጠራው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጠረብኝ።
ስላገኘሁት ዓለማዊ ስኬት ቆም ብዬ እንዳስብ ያደረገኝ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የያዕቆብን መጽሐፍ ማንበቤ ነው። በምዕራፍ 4 ላይ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከዓለም ጋር መወዳጀት ከአምላክ ጋር ጠላትነት መፍጠር እንደሆነ አታውቁም? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን የአምላክ ጠላት ያደርጋል።” (ያዕቆብ 4:4) ቁጥር 17 ላይ ያለው “አንድ ሰው ትክክል የሆነውን ነገር እንዴት ማድረግ እንዳለበት እያወቀ ሳያደርገው ቢቀር ኃጢአት ይሆንበታል” የሚለው ሐሳብ ደግሞ ይበልጥ አስገረመኝ። ከዚያም እህቶቼን ጠራኋቸውና ቁማር በሚያጫውት ሆቴል ውስጥ መሥራቴን እንደማቆም ነገርኳቸው፤ ምክንያቱም ይህ ሥራ ቁማርንና ስግብግብነትን ጨምሮ አሁን ሕሊናዬ ከማይቀበላቸው ነገሮች ጋር ያነካካኛል።
“ስላገኘሁት ዓለማዊ ስኬት ቆም ብዬ እንዳስብ ያደረገኝ . . . የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የያዕቆብን መጽሐፍ ማንበቤ ነው”
ከአምላክ ጋር እንዲሁም ከወላጆቼም ሆነ ከወንድሜና ከእህቶቼ ጋር ያለኝን ግንኙነት ማሻሻል ፈልጌ ነበር። ስለዚህ አኗኗሬን ቀለል በማድረግ ለእነሱ በቂ ጊዜ ለመስጠት ወሰንኩ። ይህን ማስተካከያ ማድረግ ግን ቀላል አልነበረም። ለምሳሌ ቁማር በሚያጫውት ሆቴል ንግድ ዘርፍ እድገት የሚያስገኝና ቀደም ሲል አገኝ ከነበረው ሁለት ወይም ሦስት እጥፍ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ እንድሠራ ግብዣ ቀርቦልኝ ነበር። ሆኖም ስለ ጉዳዩ ከጸለይኩ በኋላ ዳግመኛ ወደዚያ ሕይወት ላለመመለስ ወሰንኩ። እናቴ ቤት ውስጥ ያለውን የመኪና ማቆሚያ ቦታ ካስተካከልኩ በኋላ ሥራዬን ትቼ እዚያ መኖር ጀመርኩ፤ ከዚያም አነስተኛ ንግድ በማቋቋም ለምግብ ቤቶች የምግብ ዝርዝር ወረቀቶችን በመጠረዝ ሥራ ላይ ተሰማራሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ ቅድሚያ የምሰጣቸውን ነገሮች እንዳስተካክል ቢረዳኝም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት አልጀመርኩም ነበር። እህቶቼ የይሖዋ ምሥክሮችን የማልወዳቸው ለምን እንደሆነ ጠየቁኝ። እኔም እንዲህ ስል መለስኩላቸው፦ “አምላካችሁ ይሖዋ ቤተሰቦችን ስለሚለያይ ነው። ከቤተሰባችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ የምችልበት ብቸኛው አጋጣሚ በገናና በልደት በዓላት ወቅት ነው፤ እናንተ ደግሞ እነዚህን በዓላት አታከብሩም።” አንዷ እህቴ እያለቀሰች እንዲህ ስትል ጠየቀችኝ፦ “በዓመቱ ውስጥ ባሉት ሌሎች ቀናት አንተ የት አለህ? አንተን ለመቀበል በራችን ሁሌም ክፍት ነው። አንተ ግን እኛ ጋር መምጣት የምትፈልገው በበዓላት ቀን ላይ ብቻ ነው፤ እሱም ግዴታ ስለሆነብህ ነው።” የተናገረችው ነገር ልቤን በጥልቅ ስለነካው አብሬያት ማልቀስ ጀመርኩ።
የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰባቸውን ምን ያህል እንደሚወዱና ስለ እነሱ ያለኝ አመለካከት በጣም የተሳሳተ እንደነበር ስገነዘብ በአቅራቢያዬ ወዳለ የስብሰባ አዳራሽ ሄጄ ስብሰባቸው ላይ ለመገኘት ወሰንኩ። በዚያም ኬቨን ከተባለ ጎበዝ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ጋር የተዋወቅኩ ሲሆን ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።
ኬቨን እና ባለቤቱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ በመርዳቱ ሥራ የተቻላቸውን ያህል ብዙ ተሳትፎ ለማድረግ ሲሉ ቀለል ያለ ሕይወት ይመሩ ነበር። የሚያገኙትን ገቢ ተጠቅመው ወደ አፍሪካና ወደ ማዕከላዊ አሜሪካ በመጓዝ የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይገነቡ ነበር። በጣም የሚዋደዱና ደስተኛ ባልና ሚስት ነበሩ። ‘የምፈልገው እንዲህ ዓይነት ሕይወት መምራት ነው’ ብዬ አሰብኩ።
ኬቨን በሚስዮናዊ አገልግሎት መካፈል ስለሚያስገኘው ደስታ የሚገልጽ ቪዲዮ አሳየኝ፤ እኔም እንዲህ ዓይነት ሕይወት ለመምራት ወሰንኩ። ለስድስት ወራት ያህል መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ካጠናሁ በኋላ በ1995 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። አምላክን ሀብት እንዲሰጠኝ ከመለመን ይልቅ “ድሃም ሆነ ባለጸጋ አታድርገኝ” ብዬ መለመን ጀመርኩ።—ምሳሌ 30:8
ያገኘሁት ጥቅም
አሁን እውነተኛ ሀብት አግኝቻለሁ፤ ይህ ሀብት ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ነው። በሆንዱራስ ሳለሁ ከውዷ ባለቤቴ ከኑሪያ ጋር የተዋወቅኩ ሲሆን ከእሷ ጋር በፓናማና በሜክሲኮ ሚስዮናዊ ሆነን አገልግለናል። “የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤ እሱም ከበረከቱ ጋር ሥቃይን አይጨምርም” የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ምንኛ እውነት ነው!—ምሳሌ 10:22