መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
ያገኘሁት ከሁሉ የሚበልጥ ሽልማት
የትውልድ ዘመን 1967
የትውልድ አገር ፊንላንድ
የኋላ ታሪክ ፕሮፌሽናል ቴኒስ ተጫዋች
የቀድሞ ሕይወቴ
ያደግኩት ፊንላንድ ውስጥ ከምትገኘው ከታምፐሬ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ነው፤ አካባቢያችን ለምለም ሲሆን ግርግር ያልበዛበት ነበር። ወላጆቼ እምብዛም ሃይማኖተኛ ባይሆኑም ለትምህርትና ለመልካም ምግባር ከፍ ያለ ግምት ነበራቸው። እናቴ ጀርመናዊት ስለሆነች ትንሽ ልጅ እያለሁ አያቶቼን ለመጠየቅ አልፎ አልፎ ወደ ምዕራብ ጀርመን እሄድ ነበር።
ከልጅነቴ ጀምሮ ስፖርት እወድ ነበር። በልጅነቴ በሁሉም ዓይነት ስፖርቶች እካፈል የነበረ ቢሆንም 14 ዓመት ሲሆነኝ በቴኒስ ላይ ለማተኮር ወሰንኩ። በ16 ዓመቴ በየቀኑ ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ልምምድ አደርግ ነበር፦ከአሠልጣኜ ጋር በቀን ሁለት ጊዜ የምለማመድ ሲሆን አመሻሹ ላይ ደግሞ ለብቻዬ እለማመዳለሁ። የጨዋታው የተለያዩ ገጽታዎች ቀልቤን ስበውት ነበር፤ ቴኒስ መጫወት አእምሯዊም ሆነ አካላዊ ብቃቴን ለመፈተሽ ያስችለኝ ነበር። ከጓደኞቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍና አልፎ አልፎ ቢራ መጠጣት ቢያስደስተኝም በዕፅም ሆነ በአልኮል ምክንያት ችግር ውስጥ ገብቼ አላውቅም። ሕይወቴ በቴኒስ ዙሪያ ያጠነጠነ ነበረ፤ ከምንም በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ለቴኒስ ነበር።
አሥራ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ኤቲፒ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ላይ መካፈል ጀመርኩ። a በበርካታ ውድድሮች ላይ ስላሸነፍኩ በአገር አቀፍ ደረጃ ዝና አተረፍኩ። በ22 ዓመቴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ብቃት ካላቸው 50 የቴኒስ ተጫዋቾች አንዱ ለመሆን በቃሁ።
ለብዙ ዓመታት በዓለም ዙሪያ ወደተለያዩ ቦታዎች እየተጓዝኩ በቴኒስ ውድድሮች ላይ ተካፍያለሁ። በጉዞዬ ላይ አንዳንድ አስደናቂ ቦታዎችን ተመልክቻለሁ፤ ይሁን እንጂ በርካታ ዓለም አቀፍ ችግሮች እንዳሉም ማስተዋል ችያለሁ፤ ከእነዚህም መካከል ወንጀል፣ ዕፅን አላግባብ መውሰድና የአካባቢ ብክለት ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ሳለን በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች ወንጀል በጣም ስለተስፋፋ ወደዚያ እንዳንሄድ ይነገረን ነበር። ይህ ሁሉ በጣም ይረብሸኝ ጀመር። ከዚህም ሌላ ሥራዬን የምወደው ቢሆንም ውስጤ ባዶነት ይሰማኝ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
የሴት ጓደኛዬ ሳና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር። ለሃይማኖት ትኩረት መስጠቷ ቢያስገርመኝም ማጥናቷን አልተቃወምኩም። በ1990 ከሳና ጋር ተጋባን፤ በቀጣዩ ዓመት ሳና ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። እኔ ግን አምላክ መኖሩን ባምንም ሃይማኖተኛ ሰው እንደሆንኩ አይሰማኝም ነበር። ጀርመናዊት የሆነችው አያቴ መጽሐፍ ቅዱስን ብዙ ጊዜ ታነብ እንደነበረ አስታውሳለሁ፤ እንዲያውም እንዴት መጸለይ እንዳለብኝ አስተምራኛለች።
አንድ ቀን እኔና ሳና የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ባልና ሚስት ጋር እያለን ባልየው ካሪ ‘ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት’ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አሳየኝ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ይህም በጣም አስደነቀኝ፤ ምክንያቱም በዓለም ላይ አስከፊ ነገሮች የበዙት ለምን እንደሆነ ተረዳሁ። ያን ዕለት ስለ ሃይማኖት ብዙም አልተነጋገርንም። ሆኖም ከዚያች ዕለት ጀምሮ ከካሪ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ጀመርኩ፤ የተማርኩት ነገር ሁሉ አሳማኝ ነበር። ፕሮግራሜ በጣም የተጣበበ ከመሆኑም ሌላ አዘውትሬ እጓዝ ስለነበር ከካሪ ጋር በቋሚነት መገናኘት አስቸጋሪ ቢሆንብንም ካሪ ተስፋ አልቆረጠም። በጥናታችን ወቅት ላነሳኋቸው ጥያቄዎች በደብዳቤ መልስ ይሰጠኝ ነበር። ሕይወትን በተመለከተ ለተፈጠሩብኝ ጥልቀት ያላቸው ጥያቄዎች ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳማኝ መልስ አገኘሁ፤ ውሎ አድሮም የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ጭብጥ ይኸውም የአምላክ መንግሥት የአምላክን ዓላማ ዳር እንደሚያደርስ ማስተዋል ቻልኩ። የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን መማሬና ለእኛ ያደረገውን ነገር መረዳቴ በጥልቅ ነካኝ። (መዝሙር 83:18) ከሁሉም ይበልጥ ልቤን የነካው ነገር የቤዛው ዝግጅት ነው፤ አምላክ ይህን ዝግጅት ያደረገው እንዲሁ ሕጋዊ አሠራር ለመከተል ብሎ ሳይሆን ለሰው ልጆች ፍቅር ስላለው ነው። (ዮሐንስ 3:16) በተጨማሪም የአምላክ ወዳጅ የመሆንና ሰላም በሰፈነበት ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደተዘረጋልኝ ተማርኩ። (ያዕቆብ 4:8) በመሆኑም “ለዚህ ሁሉ አመስጋኝነቴን ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?” እያልኩ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ።
ሕይወቴን ስለምመራበት መንገድ ቆም ብዬ አሰብኩ። የላቀ ደስታ የሚገኘው በመስጠት እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተማርኩ የማምንባቸውን ነገሮች ለሌሎች የማካፈል ምኞት አደረብኝ። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ፕሮፌሽናል የቴኒስ ተጫዋች እንደመሆኔ መጠን በውድድሮች ለመሳተፍ ወደተለያዩ ቦታዎች ስለምጓዝ በየዓመቱ ለ200 ቀናት ያህል ቤቴ አልኖርም ነበር። የቤተሰብ ሕይወታችን በእኔ ፕሮግራም ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር፤ በሌላ አባባል የሥልጠና ፕሮግራሜ፣ ዕለታዊ እንቅስቃሴዬ እንዲሁም ሥራዬ በቤተሰባችን ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበረው። ስለዚህ ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።
ትልቅ ቦታ ላይ ለመድረስ የሚያስችል የስፖርት ሙያዬን ለሃይማኖት ብሎ መተው ብዙዎች ሊገባቸው የማይችል ውሳኔ እንደሆነ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ ይሖዋን ይበልጥ የማወቅና ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ፣ ቴኒስ በመጫወት ላገኝ ከምችለው ከየትኛውም ሽልማት የበለጠ ነው፤ በመሆኑም ምን ማድረግ እንዳለብኝ መወሰን በጣም ቀላል ነበር። ሰዎች ለሚሰነዝሩት አስተያየት ጆሮ ላለመስጠት ቆርጬ ነበር፤ ይህ እኔ ላደርገው የሚገባ ውሳኔ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ተጽዕኖ እንድቋቋም በጣም የረዳኝ በመዝሙር 118:6 ላይ የሚገኘው “ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” የሚለው ጥቅስ ነው።
እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ባደረግኩበት ጊዜ አንዳንድ ድርጅቶች ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ውል እንድፈርም ግብዣ አቅርበውልኝ ነበር፤ ይህን ውል ብፈርም ለብዙ ዓመታት ምንም ሳልጨነቅ ቴኒስ መጫወት እችል ነበር። እኔ ግን ውሳኔ አድርጌ ስለነበረ ግብዣውን አልተቀበልኩም፤ ውሎ አድሮም ኤቲፒ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ላይ መጫወት አቆምኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን የቀጠልኩ ሲሆን ሐምሌ 2, 1994 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ያገኘሁት ጥቅም
ስለ አምላክ እንዳስብ ያደረገኝ በሕይወቴ ውስጥ ያጋጠመኝ አሳዛኝ ነገር አይደለም። እውነትን ለማግኘት ጥረት የማደርግ ሰውም አልነበርኩም። ሕይወቴ የተደላደለ ነበር፤ ከዚያ የበለጠ የምመኘው ነገርም አልነበረም። ሆኖም ሳላስበው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማግኘት ቻልኩ፤ ሕይወት ጥልቅ ትርጉም እንዳለው የተገነዘብኩ ሲሆን ላስበው ከምችለው የላቀ ሕይወት መምራት ችያለሁ! ቤተሰባችን ከምንጊዜውም ይበልጥ የሚቀራረብና አንድነት ያለው ሆኗል። ሦስቱ ወንዶች ልጆቼ ስፖርተኞች ሳይሆን ክርስቲያኖች በመሆን የእኔን ፈለግ ስለተከተሉ በጣም ደስተኛ ነኝ።
አሁንም ቴኒስ መጫወት ደስ ይለኛል። ባለፉት ዓመታት ከቴኒስ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ሥራዎችን በመሥራት፣ ለምሳሌ በአንድ የቴኒስ ማዕከል ውስጥ አሠልጣኝና ሥራ አስኪያጅ በመሆን መተዳደሪያ ማግኘት ችያለሁ። ይሁንና እንደ ቀድሞው ሕይወቴ በስፖርት ላይ ያተኮረ አይደለም። ከዚህ ቀደም፣ የተሻልኩ ቴኒስ ተጫዋች ለመሆንና በውድድር ለማሸነፍ ስል በየሳምንቱ ለብዙ ሰዓታት ልምምድ አደርግ ነበር። አሁን ግን ሰዎች የእኔን ሕይወት የለወጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንዲያውቁና በሕይወታቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉ በመርዳት የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ አገለግላለሁ፤ ይህም ታላቅ ደስታ አምጥቶልኛል። ከይሖዋ አምላክ ጋር ላለኝ ዝምድና ቅድሚያ መስጠቴና ብሩህ የሆነውን የወደፊት ተስፋዬን ለሌሎች ማካፈሌ ይህ ነው የማይባል እርካታ አስገኝቶልኛል።—1 ጢሞቴዎስ 6:19
a ኤቲፒ (አሶሲዬሽን ኦቭ ቴኒስ ፕሮፌሽናልስ) ማለትም የሜዳ ቴኒስ ባለሙያዎች ማህበር፣ ፕሮፌሽናል የወንድ ቴኒስ ተጫዋቾች የበላይ አካል ነው። ኤቲፒ፣ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የሚካፈሉባቸውን ውድድሮች የሚያዘጋጅ ሲሆን ለአሸናፊዎች ነጥቦችና የገንዘብ ሽልማቶች ይሰጣል። አንድ ተጫዋች በዓለም ላይ የሚኖረው ደረጃ የሚወሰነው፣ በእነዚህ ውድድሮች ላይ የሚያስመዘግባቸውን ጠቅላላ ነጥቦች መሠረት በማድረግ ነው።