በቁጣ ለገነፈሉ ቀሳውስት የተሰጠ የለዘበ ምላሽ
በአርሜንያ የሚኖረው አርቱር የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግላል። አርቱር አንድን ጉባኤ እየጎበኘ ሳለ ጉባኤው በጋሪ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመደርደር በሚካሄደው የአደባባይ ምሥክርነት ተካፍሎ እንደማያውቅ ተገነዘበ። ስለዚህ አርቱር ጉባኤው በዚህ የአገልግሎት መስክ እንዲካፈል ለማበረታታት ሲል የጽሑፍ ጋሪ ይዞ ከባለቤቱ ከአና እና ጂራይር ከሚባል ሌላ የይሖዋ ምሥክር ጋር ወደ አንዲት ትንሽ ከተማ ሄደ። ከዚያም ብዙ እግረኞች በሚመላለሱበት ቦታ ላይ ጋሪውን ይዘው ቆሙ።
በአካባቢው የሚተላለፉት ሰዎች ወዲያውኑ ትኩረታቸው ስለተሳበ ጽሑፍ መውሰድ ጀመሩ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ይህ አዲስ የስብከት ዘዴ የተቃዋሚዎችንም ትኩረት ሳበ። ሁለት ቄሶች ወደ ጋሪው መጡና አንደኛው ቄስ በድንገት ጋሪውን በእርግጫ መትቶ ጣለው። ከዚያም አርቱርን በጥፊ መታውና የአርቱር መነጽር መሬት ላይ ወደቀ። አርቱር፣ አና እና ጂራይር ቄሶቹን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ሊሳካላቸው አልቻለም። ቄሶቹ ጋሪውን ረጋገጡት፤ እንዲሁም ጽሑፎቹን በታተኑ። ከዚያም ከሰደቧቸውና ከዛቱባቸው በኋላ ትተዋቸው ሄዱ።
አርቱር፣ አና እና ጂራይር ክስ ለመመሥረት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ሄዱ። ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ከፖሊሶቹና ከሌሎች ሠራተኞች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በአጭሩ ተወያዩ። ከዚያም ሦስቱ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ኃላፊው ቢሮ ተወሰዱ። ኃላፊው መጀመሪያ ላይ ማወቅ የፈለገው ስለ ክሱ ብቻ ነበር። ፈርጣማ የሆነው አርቱር በጥፊ ሲመታ አጸፋ እንዳልመለሰ ሲሰማ ግን ስለ ክሱ መጠየቁን አቁሞ ስለ እምነታቸው የጠይቀው ጀመረ። በዚህም ምክንያት ለአራት ሰዓታት ተወያዩ። ኃላፊው በሰማው ነገር በጣም ስለተደነቀ “እንዴት ደስ የሚል ሃይማኖት ነው! እኔም ብቀላቀል ደስ ይለኛል!” አለ።
በቀጣዩ ቀን አርቱር በድጋሚ በአደባባይ ምሥክርነት እየተካፈለ ሳለ፣ ያለፈው ቀን ላይ የተከናወነውን ነገር የተመለከተ አንድ ሰው ወደ እሱ መጣ። ሰውየው አርቱር አጸፋ ከመመለስ ይልቅ እርጋታ በማሳየቱ አድናቆቱን ገለጸለት። አክሎም ያየው ነገር ለቄሶቹ የነበረውን አክብሮት እንዳሳጣው ተናገረ።
በዚያ ምሽት የፖሊስ ኃላፊው አርቱርን ወደ ፖሊስ ጣቢያ አስጠራው። ሆኖም ስለ ክሱ ከመጠየቅ ይልቅ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን አቀረበለት። ሁለት ሌሎች ፖሊሶችም በውይይቱ ላይ ተገኝተው ነበር።
በቀጣዩ ቀን አርቱር በድጋሚ ወደ ፖሊስ ኃላፊው ሄደ፤ በዚህ ወቅት አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቪዲዮዎችን ለኃላፊው አሳየው። ኃላፊው ሌሎች ፖሊሶችም መጥተው ቪዲዮዎቹን እንዲያዩ ጠራቸው።
ቄሶቹ ባሳዩት መጥፎ ምግባር የተነሳ በርካታ ፖሊሶች ለመጀመሪያ ጊዜ ሊመሠከርላቸው ችሏል። ይህም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል።