በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የጤና ችግር ሌሎችን ከማጽናናት አላገዳትም

የጤና ችግር ሌሎችን ከማጽናናት አላገዳትም

 ክሎዲን በደቡብ አፍሪካ የምትኖር የይሖዋ ምሥክር ናት፤ ከባድ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ሆስፒታል ገብታ ነበር። የተለያዩ የጤና እክሎች ስለነበሩባት የምትወስደውን ሕክምና በጥንቃቄ መምረጥ ነበረባት። ከቀዶ ሕክምናው በፊትም ሆነ በኋላ ከፍተኛ ድካምና ሥቃይ ነበራት፤ እንዲሁም ሁኔታው ያስከተለባት ውጥረት ነበር። ወደ ቤቷ ከተመለሰች ከአሥር ሳምንት በኋላም እንኳ ቀና ብላ መቀመጥ አልቻለችም። በዚያ ላይ ደግሞ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ሰው ሄዶ ሊጠይቃት አይችልም።

 ክሎዲን ስለ ችግሯ እያሰበች መቆዘም አልፈለገችም፤ ስለዚህ ሌሎችን ለማጽናናት አቅም እንዲሰጣት አምላክን ለመነችው። በኋላ ላይ ቀና ብላ መቀመጥ እንደቻለች የጎረቤቷን እህት ለማነጋገር ጥረት አደረገች። ይህች ሴት በአንድ ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና የነበረ ቢሆንም ጥናቷን አቁማ ነበር። ክሎዲን ከአምላክ ቃል ላይ የሚያበረታታ ሐሳብ ለዚህች ሴት ነገረቻት፤ ይህም ሴትየዋ ጥናቷን እንድትቀጥል አነሳሳት። በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘቷ ለምን እንደሚጠቅማት አብራራችላት፤ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የእሷ ጉባኤ ላይ መገኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነም አስረዳቻት። ሴትየዋም እንደተባለችው አደረገች፤ እንዲያውም በጥያቄና መልስ በሚካሄደው የስብሰባው ፕሮግራም ላይ ሐሳብ መስጠት ቻለች።

 ክሎዲን የዚህችን ጥናቷን ታናሽ እህትም ማነጋገር ጀመረች፤ እሷም መጽሐፍ ቅዱስን መማር ትፈልግ ነበር። እንዲያውም ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ለክሎዲን ነገረቻት። ውጤቱ ምን ሆነ? ክሎዲን ሌሎች አራት ሴቶችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረች። ታሪኩ ግን በዚህ አያበቃም!

ክሎዲን

 ክሎዲን ለሌሎች ትኩረት ለመስጠት ጥረት ማድረጓ አሁን ካሏት በተጨማሪ አሥር ሴቶችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር አስችሏታል፤ በዚህ የወረርሽኝ ጊዜ በድምሩ 16 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማግኘት ችላለች! አንዳንዶቹ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት አዘውትረው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። ክሎዲን በዚህ መንገድ በሥራ መጠመዷ የራሷን ችግር ብቻ እያሰበች እንዳትብሰለሰል ረድቷታል። ደግሞም “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ በመከራዎቿ የሰጣት መጽናኛ እሷም ሌሎችን እንድታጽናና እንደረዳት ይሰማታል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

 ክሎዲን መጽሐፍ ቅዱስን የምታስተምራቸው ሴቶችስ ስለተማሩት ነገር ምን ይሰማቸዋል? አንደኛዋ እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ጥቅም አግኝቻለሁ። ለእኔ ግን ከምንም በላይ ያስደሰተኝ የአምላክን ስም ማወቄ ነው። ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንድመሠርት ረድቶኛል።” ክሎዲን ያገኘቻት የመጀመሪያዋ ሴትስ ምን ደረሰች? አሁን የምትጠመቅበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቀች ነው። ክሎዲን እንዲህ ያለ ውጤት በማግኘቷ በጣም ተደስታለች። ካደረገችው የቀዶ ሕክምናም ጥሩ እያገገመች ነው።