ቄሱ ለጥያቄዎቹ መልስ አገኘ
ኤሊሶ የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር አንዲትን ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ሁለት ያልተጠበቁ እንግዶች ወደ ሴትየዋ ቤት መጡ። የመጡት አንድ ቄስና ባለቤቱ ነበሩ። ሰዎቹ ከጥቂት ጊዜ በፊት ብቸኛ ልጃቸው ታሞ እንደሞተባቸው ለኤሊሶ ነገሯት።
ኤሊሶ በልጃቸው ሞት ከልቧ ማዘኗን ስትገልጽላቸው ቄሱና ባለቤቱ ምርር ብለው ማልቀስ ጀመሩ። ከዚያም ቄሱ በቁጣ እንዲህ አለ፦ “አምላክ እንዲህ ያለ ፈተና እንዲደርስብኝ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም! አንድ ልጄን እንዴት ይወስድብኛል? ለ28 ዓመታት አምላክን አገልግያለሁ፤ ብዙ መልካም ነገሮች ሠርቻለሁ፤ ታዲያ ውለታዬ ይህ ነው? አምላክ ልጄን የገደለብኝ ለምንድን ነው?”
ኤሊሶ ልጃቸውን የገደለባቸው አምላክ እንዳልሆነ ለቄሱና ለባለቤቱ አስረዳቻቸው። ከዚያም ስለ ቤዛውና ስለ ትንሣኤ እንዲሁም አምላክ መጥፎ ነገር እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምን እንደሆነ አወያየቻቸው። ቄሱና ባለቤቱም የሰጠቻቸው መልስ የጸሎታቸው ምላሽ እንደሆነ ነገሯት።
በቀጣዩ ሳምንት ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ቄሱና ባለቤቱ አብረው በጥናቱ ላይ ተካፈሉ። ኤሊሶና ሴትየዋ የሚያጠኑት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ “በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ያላቸው እውነተኛ ተስፋ” የሚለውን ምዕራፍ ነበር። ባልና ሚስቱ በውይይቱ ላይ ሞቅ ያለ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር።
በኋላም ባልና ሚስቱ በተብሊሲ፣ ጆርጂያ በተካሄደው ልዩ የክልል ስብሰባ ላይ ተገኙ። እዚያ ባዩት አንድነትና እውነተኛ ፍቅር ልባቸው በጥልቅ ተነካ፤ እነዚህን ባሕርያት በቤተ ክርስቲያናቸው አባላት ላይ ለመቅረጽ ለረጅም ጊዜ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም ነበር።