እንደምትወጂያቸው ንገሪያቸው
ኦንግሊ በቡልጋሪያ የምትኖር የይሖዋ ምሥክር ናት። ይህች እህት ዝላትካ የተባለችን አንዲት ወጣት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናለች። የዝላትካ ባለቤት ግን መጽሐፍ ቅዱስን አያጠናም። ኦንግሊ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን ስለ ቤተሰብ ሕይወት ስንወያይ፣ ለትዳር ጓደኛችንና ለልጆቻችን ፍቅራችንን በቃላት መግለጻችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ነገርኳት። ዝላትካ በሐዘን በተሞላ ፊት አየት አደረገችኝ፤ ከዚያም ለባለቤቷም ሆነ ለዘጠኝ ዓመት ሴት ልጇ እንደምትወዳቸው አንዴም እንኳ ነግራቸው እንደማታውቅ ገለጸችልኝ!”
ዝላትካ እንዲህ ብላለች፦ “ለእነሱ ስል ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ነኝ፤ እነዚያን ቃላት ከአንደበቴ ማውጣት ግን በጣም ይከብደኛል። እናቴ እንደምትወደኝ አንድ ጊዜም እንኳ ነግራኝ አታውቅም፤ አያቴም ብትሆን ለእናቴ እንደምትወዳት ነግራት አታውቅም።” ኦንግሊ፣ ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን እንደሚወደው በግልጽ እንደተናገረ ለዝላትካ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየቻት። (ማቴዎስ 3:17) ከዚያም ጉዳዩን አስመልክታ ወደ ይሖዋ እንድትጸልይ እንዲሁም ለባሏና ለልጇ እንደምትወዳቸው ለመናገር የታሰበበት ጥረት እንድታደርግ አበረታታቻት።
ኦንግሊ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ከሁለት ቀን በኋላ ዝላትካ በደስታ ወደ እኔ መጥታ ይሖዋ እንዲረዳት እንደጸለየች ነገረችኝ። ባለቤቷ ወደ ቤት ሲመጣ፣ ሚስቶች ባሎቻቸውን ማክበራቸውና መውደዳቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ ላይ እንደተማረች ገለጸችለት። ከዚያም ትንሽ ካሰበች በኋላ፣ በጣም እንደምትወደው ነገረችው! ልጇ ወደ ቤት ስትመለስ ደግሞ እቅፍ አድርጋ እንደምትወዳት ነገረቻት! ዝላትካ እንዲህ አለችኝ፦ ‘አሁን እፎይታ ተሰምቶኛል። ለበርካታ ዓመታት ስሜቴን አምቄ ኖሬ ነበር፤ በይሖዋ እርዳታ ግን ለቤተሰቤ ፍቅሬን መግለጽ ችያለሁ።’”
ኦንግሊ አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ከአንድ ሳምንት በኋላ ከዝላትካ ባለቤት ጋር ተገናኘን፤ እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘ብዙ ሰዎች ዝላትካ ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደሌለባት ነግረውኝ ነበር። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቷ ለቤተሰባችን በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ምንም አልጠራጠርም። የቤተሰባችን ሕይወት ከበፊቱ ይበልጥ ፍቅርና ደስታ የሰፈነበት ሆኗል።’”