በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዓይነ ስውር የሆነች ሴት ያቀረበችው ጸሎት መልስ አገኘ

ዓይነ ስውር የሆነች ሴት ያቀረበችው ጸሎት መልስ አገኘ

 የንሜ የተባለች በእስያ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር ሚንግጂየ የተባለችን ዓይነ ስውር ሴት መንገድ አሻገረቻት። a ሚንግጂየም “አመሰግናለሁ። አምላክ ይባርክሽ!” አለቻት። ከዚያም የንሜ፣ ሌላ ጊዜ ተገናኝተው መጽሐፍ ቅዱስን አብረው እንዲያጠኑ ለሚንግጂየ ግብዣ አቀረበችላት። ሚንግጂየ አምላክ ወደ እውነተኛ የክርስቲያን ጉባኤ እንዲመራት በየዕለቱ ትጸልይ እንደነበር ከጊዜ በኋላ ተናግራለች። ሚንግጂየ እንዲህ ያለ ልመና ያቀረበችው ለምንድን ነው?

 ሚንግጂየ፣ አንዲት ዓይነ ስውር ጓደኛዋ የአካል ጉዳተኞችን ወደሚረዳ አንድ ቤተ ክርስቲያን እንድትሄድ ያቀረበችላትን ግብዣ ተቀብላ በ2008 ሄዳ ነበር። ሚንግጂየ ስብከቱን ካዳመጠች በኋላ ቄሱን ከየትኛው መጽሐፍ እየጠቀሰ እንዳስተማረ ጠየቀችው። እሱም ያስተማረው፣ እውነት ከሆነው የአምላክ ቃል ይኸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ነገራት። ሚንግጂየ ይህን መጽሐፍ ለማንበብ በጣም ጓጓች። በቻይንኛ ብሬይል የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ካገኘች በኋላ 32ቱን ጥራዞች በስድስት ወር ገደማ አንብባ ጨረሰች። ሚንግጂየ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበበች ስትሄድ፣ እሷ በምትገኝበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያስተምሩት የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ስህተት እንደሆነ እና የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ተገነዘበች።

 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ሚንግጂየ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ምግባር ቅር ያሰኛት ጀመር። የአባላቱ ምግባር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምታነበው ጋር እንደማይስማማ አስተዋለች። ለምሳሌ፣ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኑ አባላት የሚቀርብላቸው ትኩስ ምግብ ሲሆን ዓይነ ስውራን ለሆኑት ግን የተራረፈ ምግብ ይሰጣቸው ነበር። ሚንግጂየ እንዲህ ባለው መድልዎ ስሜቷ ስለተጎዳ በአካባቢዋ ሌሎች ቤተ ክርስቲያኖችን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመረች። አምላክ ወደ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ እንዲመራት መጸለይ የጀመረችው ለዚህ ነበር።

 ሚንግጂየ፣ የንሜ ያሳየቻት ደግነት ልቧን ስለነካው መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና ያቀረበችላትን ግብዣ ተቀበለች። ከዚያም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኘች። ሚንግጂየ እንዲህ ብላለች፦ “ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ የሄድኩበትን ቀን መቼም አልረሳውም። ሁሉም ወንድሞችና እህቶች ሞቅ አድርገው ሰላም አሉኝ። ይህም ልቤን በጥልቅ ነካው። ዓይነ ስውር ብሆንም እንኳ ከአድልዎ ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳሳዩኝ ተሰምቶኝ ነበር።”

 ሚንግጂየ በጥናቷ የገፋች ሲሆን በስብሰባዎች ላይ አዘውትራ መገኘት ጀመረች። በስብሰባዎች ላይ መዝሙሮችን መዘመር በጣም ያስደስታት ነበር፤ ሆኖም እሷ ማንበብ በምትችለው ብሬይል የተዘጋጀ መዝሙር መጽሐፍ ስላልነበረ መዘመር ቀላል አልሆነላትም። በመሆኑም ሚንግጂየ የጉባኤው አባላት እየረዷት የራሷን መዝሙር መጽሐፍ አዘጋጀች። በመጽሐፉ ላይ ያሉትን 151 መዝሙሮች በብሬይል ለመገልበጥ 22 ሰዓት ፈጅቶባታል! ሚንግጂየ ሚያዝያ 2018 ምሥራቹን ለሰዎች መስበክ የጀመረች ሲሆን ከዚያ ጊዜ አንስቶ በየወሩ በስብከቱ ሥራ 30 ሰዓት ያህል ታሳልፋለች።

አንድን መጽሐፍ በብሬይል መገልበጥ በጣም አድካሚ ሥራ ነው

 የንሜ፣ ሚንግጂየን ለጥምቀት ለማዘጋጀት ስትል የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በድምፅ ቀዳችላት። ሐምሌ 2018 ሚንግጂየ ተጠመቀች። እንዲህ ብላለች፦ “በዚያ ትልቅ ስብሰባ ላይ ወንድሞችና እህቶች ያሳዩኝ ፍቅር በጣም አስደስቶኝ ነበር። በመጨረሻ በአምላክ እውነተኛ ጉባኤ ውስጥ መታቀፍ በመቻሌ በጣም ስለተደሰትኩ አለቀስኩ።” (ዮሐንስ 13:34, 35) ሚንግጂየ ሌሎች ለእሷ ያሳዩአትን ፍቅር እሷም በተራዋ ለሰዎች ለማሳየት ስትል አሁን የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆና እያገለገለች ነው።

a ስሞቹ ተቀይረዋል።