“ከየትኛውም ፊልም የተሻለ”
የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ በትላልቅ ስብሰባዎቻቸው ላይ የሚቀርቡ በርካታ ቪዲዮዎችን ያዘጋጃሉ። አብዛኞቹ ቪዲዮዎች መጀመሪያ የሚዘጋጁት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው። ሆኖም እነዚህ ትላልቅ ስብሰባዎች የሚዘጋጁት በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ነው፤ ታዲያ ከእንግሊዝኛ ውጭ ባሉ ቋንቋዎች በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሰዎች እነዚህን ቪዲዮዎች መረዳት የሚችሉት እንዴት ነው? በቪዲዮዎቹ ውስጥ ያሉት ንግግሮች ወደተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመው በድምፅ ከተቀረጹ በኋላ ከቪዲዮው ጋር ይቀናበራሉ። በተለያዩ ቋንቋዎች በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሰዎች በቋንቋቸው የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን ሲመለከቱ ምን ይሰማቸዋል?
በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን በተመለከተ የተሰጡ አስተያየቶች
በሜክሲኮና በማዕከላዊ አሜሪካ በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ የተገኙ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች የሰጧቸውን አስተያየቶች እንመልከት፦
“ቪዲዮውን በሚገባ መረዳት ብቻ ሳይሆን ፊልሙ የራሴ ታሪክ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር። ቪዲዮው ልቤን ነክቶታል።”—በፖፖሉካ ቋንቋ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ የተገኘ ሰው፣ ቬራክሩዝ፣ ሜክሲኮ
“ወደ ትውልድ አካባቢዬ ሄጄ ከቅርብ ጓደኛዬ ጋር እያወራሁ እንዳለ ተሰምቶኝ ነበር። ከየትኛውም ፊልም የተሻለ ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም ነገር ገብቶኛል።”—በናዋትል ቋንቋ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ የተገኘ ሰው፣ ኑኤቮ ሌኦን፣ ሜክሲኮ
“በቋንቋዬ የተዘጋጁትን ቪዲዮዎች ሳይ ቪዲዮዎቹ ውስጥ ያሉት ሰዎች እኔን እንደሚያነጋግሩኝ ተሰማኝ።”—በቾል ቋንቋ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ የተገኘች ሴት፣ ታባስኮ፣ ሜክሲኮ
“ይህ ድርጅት ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩ ለመርዳት ትልቅ ጥረት ያደርጋል። እንዲህ ያለ ሌላ ድርጅት የለም!”—በካክቺኬል ቋንቋ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ የተገኘ ሰው፣ ሶሎላ፣ ጓቴማላ
የይሖዋ ምሥክሮች ቪዲዮዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ሲያዘጋጁ በዚህ ሙያ የሠለጠኑ ቴክኒሽያኖችን ወይም የድምፅ ተዋናዮችን አይቀጥሩም፤ በተጨማሪም የድምፅ ቅጂውን የሚያከናውኑት በአብዛኛው ራቅ ብለው በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች ነው። ታዲያ ጥራት ያላቸው ቪዲዮዎችን ማዘጋጀት የቻሉት እንዴት ነው?
“ከየትኛውም ሥራ በላይ አርኪ የሆነ ሥራ”
በ2016 የማዕከላዊ አሜሪካ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በትላልቅ ስብሰባ ላይ የሚታዩ ቪዲዮዎች በስፓንኛና በሌሎች 38 የአካባቢው ቋንቋዎች እንዲቀዱ ዝግጅት አድርጎ ነበር። 2,500 ገደማ የሚሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች በሥራው ተካፍለዋል። ቴክኒሽያኖችና የትርጉም ቡድኖች የድምፅ ቀረጻውን ያከናወኑት በቅርንጫፍ ቢሮው ወይም በርቀት የትርጉም ቢሮዎች ውስጥ አሊያም በሌሎች ቦታዎች በሚገኙ ጊዜያዊ የድምፅ ቀረጻ ስቱዲዮዎች ነው። የትርጉም ቡድኖቹ በቤሊዝ፣ በጓቴማላ፣ በሆንዱራስ፣ በሜክሲኮና በፓናማ በሚገኙ ከ20 የሚበልጡ ቦታዎች የድምፅ ቀረጻ አከናውነዋል።
ጊዜያዊ ስቱዲዮዎችን ማዘጋጀት ከባድ ሥራና ዘዴኛ መሆን ይጠይቃል። ስቱዲዮዎቹ ድምፅ የማያስገቡ እንዲሆኑ ለማድረግ ብርድ ልብሶችንና ፍራሾችን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ ነገሮች ጥቅም ላይ ውለዋል።
የድምፅ ተዋንያን ሆነው የሠሩት አብዛኞቹ ሰዎች ድሆች ሲሆኑ በአቅራቢያቸው ወዳለው የቀረጻ ስቱዲዮ ለመምጣት እንኳ ትልቅ መሥዋዕት ከፍለዋል። አንዳንዶቹ ለ14 ሰዓት መጓዝ አስፈልጓቸዋል። በአንድ ቀረጻ ላይ የተካፈሉ አባትና ልጅ ወደ ስቱዲዮው ለመምጣት ለስምንት ሰዓታት በእግር መጓዝ አስፈልጓቸዋል።
ናኦሚ ከልጅነቷ አንስቶ ቤተሰቦቿ ጊዜያዊ ስቱዲዮ ሲያዘጋጁ ታግዛቸው ነበር። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “የድምፅ ቀረጻ የሚካሄድበትን ጊዜ ሁሌም በጉጉት እንጠብቅ ነበር። አባቴ ሥራውን ለማቀናጀት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ይሠራ ነበር። አንዳንድ ጊዜ እናቴ 30 ለሚያክሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ምግብ ማዘጋጀት ያስፈልጋት ነበር።” ናኦሚ በአሁኑ ጊዜ ሜክሲኮ ውስጥ በሚገኝ አንድ የትርጉም ቢሮ ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኛ ናት። እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲሰሙ መርዳት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከየትኛውም ሥራ በላይ አርኪ የሆነ ሥራ ላይ እንደተሰማራሁ ይሰማኛል።”
የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ ትላልቅ ስብሰባዎችን በዓለም ዙሪያ የሚያካሂዱ ሲሆን ማንኛውም ሰው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችላል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የክልል ስብሰባዎች የሚለውን የድረ ገጻችንን ክፍል ተመልከት።