በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የስፓንኛ ቋንቋ የትርጉም ቡድን ወደ ስፔን ተዛወረ

የስፓንኛ ቋንቋ የትርጉም ቡድን ወደ ስፔን ተዛወረ

ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች በመላው ምድር ለሚኖሩ ሕዝቦች እንደሚሰበክ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ከ1909 ጀምሮ ወደ ስፓንኛ ቋንቋ ሲተረጎሙ ቆይተዋል፤ ይህም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰሙ አስችሏል። በአሁኑ ጊዜ ስፓንኛ፣ በተናጋሪዎች ብዛት ከቻይንኛ ቀጥሎ ሁለተኛውን ደረጃ የያዘ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ወደ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ስፓንኛ ቋንቋ ይናገራሉ።

የስፓንኛ ቋንቋ የትርጉም ቡድን አባል የሆነው ዊልያም እንዲህ ብሏል፦ “ስፓንኛ የተለያየ ባሕል ባላቸው በርካታ አገራት ውስጥ የሚነገር ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው፤ ዋናው ግባችን የተለያየ አስተዳደግ እንዲሁም የትምህርትና የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች ልብ የሚነካ ትርጉም ማዘጋጀት ነው።” በተለያየ ሁኔታ ላይ የሚገኙ አንባቢዎችን ልብ መንካት የሚችል ትርጉም ማዘጋጀት የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለማቅለል ሲባል የትርጉም ቡድኑ ከሜክሲኮ፣ ከስፔን፣ ከአርጀንቲና፣ ከኡራጓይ፣ ከኤል ሳልቫዶር፣ ከኮሎምቢያ፣ ከዮናይትድ ስቴትስ፣ ከጓቲማላ፣ ከፖርቶ ሪኮና ከቬኔዙዌላ የተውጣጡ ተርጓሚዎችን ያቀፈ እንዲሆን ተደርጓል።

ላለፉት አሥርተ ዓመታት፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሜክሲኮ፣ በስፔን እና በአርጀንቲና በሚኖሩና ተርጓሚ በሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻቸው እየታገዙ በዮናይትድ ስቴትስ ውስጥ ጽሑፎቻቸውን ወደ ስፓንኛ ሲተረጉሙ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ በ1993 የስፓንኛ ቋንቋ የትርጉም ቡድን ወደ ፖርቶ ሪኮ ተዛወረ፤ ይህም ተርጓሚዎቹ ሁሉ በአንድ አካባቢ እንዲሰባሰቡ ለማድረግ አስችሏል።

በመጋቢት 2012 የስፓንኛ ቋንቋ የትርጉም ቡድን በድጋሚ ወደ ሌላ አካባቢ ይኸውም በስፔን ወዳለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲዛወር ተወሰነ። ኤድዋርድ ሁኔታውን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ማዛወር የሚጠበቅብን ሰዎችን፣ የግል መገልገያ ቁሳቁሶችንና ሌሎች ዕቃዎችን ብቻ አልነበረም፤ በጣም ጠቃሚ የሆነውን የትርጉም ቡድናችንን ‘አባል’ ማለትም የትርጉም ክፍላችንን ቤተ መጻሕፍትም ይዘን መሄድ ነበረብን።” በቤተ መጻሕፍቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ጨምሮ 2,500 የሚያክሉ ማመሣከሪያ መጻሕፍት አሉት።

በስፔን ሞቅ ያለ አቀባበል ሲደረግላቸው

ግንቦት 29, 2013 የስፓንኛ ቋንቋ የትርጉም ቡድን አባላት ወደ አዲሱ መኖሪያቸው ደረሱ፤ በዚህ ጊዜ፣ በስፔን የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገላቸው። ተርጓሚዎቹ፣ ማመሣከሪያ መጻሕፍቱና ቁሳቁሶቹ የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጠው የሄዱ ቢሆንም እንኳ አስቀድሞ ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ በመነደፉና ትጋት የተሞላበት ጥረት በመደረጉ የይሖዋ ምሥክሮች በስፓንኛ ቋንቋ የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች የሚያነቡ ሰዎች ጽሑፎቹን በወቅቱ ማግኘታቸውን ቀጥለው ነበር። ኤድዋርድ እንዲህ ብሏል፦ “ከሁሉም ነገር የሚበልጠው የመንግሥቱን መልእክት የማወጁ ሥራ ነው፤ ስለሆነም በተቻለን መጠን፣ ስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ሁሉ መልእክቱን እንዲያነቡ እንፈልጋለን።”