ለመቶ ዓመታት አምላክን በመዝሙር ማወደስ
“በኒው ዮርክ ሲቲ ወዳለው ወደ ኮሎምቢያ ስቱዲዮ ሄደህ ከመዝሙሮቻችን መካከል አንዱን እንድትዘምር እፈልጋለሁ። እነሱም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ይቀዱታል። ይህን ጉዳይ ለማንም እንዳትናገር።”
በ1913 መገባደጃ ላይ ዊልያም ማክሪጅ ከቻርልስ ቴዝ ራስል a የተሰጠውን ይህን ለየት ያለ ኃላፊነት መወጣት ችሏል። በብዙዎች ዘንድ “አስደሳች የሆነው የወደፊት ጊዜ” በመባል ይታወቅ የነበረው ይህ መዝሙር በኋላ ላይ በሸክላ ተቀድቷል። ቆየት ብሎ ዊልያም፣ መዝሙሩ የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችና ድምፅ አልባ ፊልሞች በመስታወት ስላይዶች ላይ ከተሳሉ ሥዕሎች ጋር ተቀናብረው ለሚታዩበት “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለ ተንቀሳቃሽ ፊልም መክፈቻ ሆኖ እንዳገለገለ ተገነዘበ። “ፎቶ ድራማ” ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ የቀረበው ጥር 1914 በኒው ዮርክ ሲቲ ነበር።
ዊልያም የዘመረው መዝሙር በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚቀርበው “ፎቶ ድራማ” ላይ ፎኖግራፍ አጫዋቾቹ ከሚከፍቷቸው ከ50 የሚበልጡ መዝሙሮች መካከል አንዱ ነበር። አብዛኞቹ መዝሙሮች ከሌሎች የተወሰዱ ቢሆኑም ዊልያም የዘመረውን ጨምሮ አንዳንዶቹን መዝሙሮች ያዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበሩ፤ እነዚህ መዝሙሮች የተወሰዱት ሂምስ ኦቭ ዘ ሚሌኒያል ዶውን ከተባለው የመዝሙር መጽሐፋቸው ላይ ነበር።
መዝሙሮቹ የሚያስተላልፉትን ሐሳብ በቁም ነገር መመልከት
ለበርካታ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ የሚጠቀሙት ሌሎች ሰዎች በጻፏቸው መዝሙሮች ነበር። ይሁን እንጂ መዝሙሮቹ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ካላቸው ግንዛቤ ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ ሲሉ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በቃላቶቹ ላይ ማስተካከያ ያደርጉ ነበር።
ለምሳሌ ያህል “በፎቶ ድራማ” ላይ ከሚዘመሩት መዝሙሮች አንዱ “ንጉሣችን ወደ ፊት እየገሰገሰ ነው” የሚል ርዕስ (እንግሊዝኛ) የነበረው ሲሆን ሐሳቡ የተወሰደው “የሪፐብሊኩ የጦርነት መዝሙር” ከተባለ መዝሙር (እንግሊዝኛ) ላይ ነበር። “የጦርነት መዝሙር” የተባለው መዝሙር የመጀመሪያ ስንኝ “ዓይኔ የጌታን መምጣት ግርማ ይመለከታል” የሚል ነው። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስንኙን “ዓይኔ የጌታን መገኘት ግርማ ያያል” በሚል ለውጠውታል። ይህን ያደረጉት የኢየሱስ ክርስቶስ ግዛት የእሱን መምጣት ብቻ ሳይሆን እሱ የሚገኝበትንም ዘመን እንደሚጨምር ያምኑ ስለነበር ነው።—ማቴዎስ 24:3
በልባችሁ የምስጋና መዝሙር አዚሙ የተባለው የመዝሙር መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) በ1966 ሲወጣ ዓለማዊ ምንጭ ያላቸው ወይም ከሌሎች ሃይማኖቶች የተወሰዱ መዝሙሮችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። በዚያኑ ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች አንድ አነስተኛ ኦርኬስትራ በማቋቋም በመጽሐፉ ላይ የሚገኙትን 119 መዝሙሮች በሙሉ ቀድተዋል። ጉባኤዎች እነዚህን መዝሙሮች በስብሰባዎቻቸው ላይ ይዘምሯቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸውም ውስጥ ያዳምጧቸው ነበር።
የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ ዘምሩ የተሰኘ አዲስ የመዝሙር መጽሐፍ በ2009 አሳተሙ። እነዚህ መዝሙሮች በበርካታ ቋንቋዎች በድምፅ እየተዘመሩ ተዘጋጅተዋል። በ2013 የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ልጆች የሚዘምሩባቸውን ቪዲዮዎች አዘጋጅተው አወጡ። በማንኛውም ጊዜ ጸልዩ (እንግሊዝኛ) የሚለው መዝሙር ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው። jw.org የተባለውን ድረ ገጽ የሚጎበኙ ሰዎች በየወሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መዝሙሮችን ያወርዳሉ።
ብዙዎች ለእነዚህ መዝሙሮች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ጁሊ የተባለች አንዲት ሴት ለይሖዋ ዘምሩ የተባለውን የመዝሙር መጽሐፍ አስመልክታ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “አዲስ የወጡት መዝሙሮች እጅግ ማራኪ ናቸው! ብቻዬን በምሆንበት ጊዜ የውስጥ ስሜቴን የሚገልጹልኝን መዝሙሮች እዘምራለሁ። ከዚህም የተነሳ ከይሖዋ ጋር ያለኝ ግንኙነት ይበልጥ እንደተጠናከረ ይሰማኛል፤ እሱን በሙሉ ነፍስ ለማገልገል ያደረግኩትንም ውሳኔ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጠናክሮልኛል።”
የሰባትና የዘጠኝ ዓመት ልጆች ያሏት ሄዘር የምትባል አንዲት እናት በማንኛውም ጊዜ ጸልዩ የተሰኘው ቪዲዮ በልጆቿ ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ቪዲዮው፣ ጠዋት ላይ ወይም ከእኛ ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ይሖዋን ማነጋገር በፈለጉ ሰዓት ሁሉ እንዲጸልዩ ረድቷቸዋል።”
a ቻርልስ ቴዝ ራስል (1852–1916) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን (በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ይጠራሉ) በግንባር ቀደምትነት ይመራ ነበር።