በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች በለቪፍ አቅራቢያ የሚገኝን አንድ ደን በማጽዳት ሥራ ተካፈሉ

የይሖዋ ምሥክሮች በለቪፍ አቅራቢያ የሚገኝን አንድ ደን በማጽዳት ሥራ ተካፈሉ

ግንቦት 6, 2017፣ 130 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በለቪፍ፣ ዩክሬን አቅራቢያ የሚገኘውን የብርዩኮቪቺ ደን በማጽዳቱ ሥራ ላይ ተካፍለው ነበር። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከ22 ዓመት አንስቶ እስከ 80 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን የሚኖሩት ከደኑ አቅራቢያ በሚገኘው የዩክሬን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ነው። በጽዳቱ የተካፈሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች በሦስት ሰዓት ውስጥ ብቻ 50 ሄክታር የሚያክል ቦታ ያጸዱ ሲሆን 600 ኪሎ ግራም ገደማ ቆሻሻ ሰብስበዋል።

የለቪፍ ፎረስት ብሪዲንግ ኤንድ ድሪሊንግ ሴንተር ዋና መሐንዲስ የሆኑት ሚካይሎ ስፕላቪንስኪ “የደኑን ዓመታዊ ጽዳት ለመደገፍ የመጀመሪያ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ ከ2014 አንስቶ በየዓመቱ በጽዳት ሥራው ላይ እየተካፈሉ ነው” ብለዋል።

ደኑ መጸዳት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ስፕላቪንስኪ እንዲህ ብለዋል፦ “ደኑ እንዲቆሽሽ የሚያደርጉት ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛ፣ ሰዎች ደኑ ውስጥ ቆሻሻ ጥለው ይሄዳሉ። ሁለተኛው ደግሞ፣ ከግንባታ ቦታዎችና ከተለያዩ ቦታዎች የተነሱ ቆሻሻዎች በትላልቅ መኪኖች ተጭነው ደኑ ውስጥ ይደፋሉ።”

በደኑ ውስጥ የሚጣለው ቆሻሻ ደኑን በእጅጉ ሊጎዳው ይችላል። ሚካይሎ ስፕላቪንስኪ እንዲህ ብለዋል፦ “ቆሻሻው በጊዜ ሂደት ይበሰብሳል። ከዚያም በመሬቱ ውስጥ ያለውን ውኃ የሚበክለው ሲሆን ይህም በሥነ ምህዳር ላይ ችግር ያስከትላል።” ከዚህም ሌላ የፀሐይ ጨረር በተጣሉት መስተዋቶች ላይ ሲያርፍ ሙቀት እንዲፈጠር ስለሚያደርግ ሰደድ እሳት እንዲነሳ ሊያደርግ ይችላል። በተጨማሪም የጠርሙስ ስብርባሪዎችና የተጣሉ ሲሪንጆች በተለይ በትናንሽ ልጆች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ሚካይሎ ስፕላቪንስኪ “ቆሻሻውን በመሰብሰብ እነዚህን ችግሮች ማስቀረት ይቻላል” ብለዋል።

ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ሄክታር ስፋት ያለውን ደን ማጽዳት በጣም ከባድ ነው። እኚህ ሰው አክለው እንዲህ ብለዋል፦ “ያሉን የደን ጠባቂዎች አምስት ብቻ ናቸው፤ ስለዚህ ይህን የሚያክል ትልቅ ቦታ በራሳችን ማጽዳት አንችልም። በመሆኑም በዓመት አንድ ጊዜ ሕዝቡን አስተባብረን ደኑን ለማጽዳት እንሞክራለን።”

መሰብሰብ፣ መለየትና ማስወገድ

የይሖዋ ምሥክሮቹ ጓንትና ቅጠል መጥረጊያዎችን ተጠቅመው ጠርሙሶችን፣ የመኪና ጎማዎችን፣ ስብርባሪ መስተዋቶችን፣ ብረቶችን፣ ወረቀቶችን፣ ፕላስቲኮችንና ስሪንጆችን በመሰብሰብ ከረጢት ውስጥ ይከታሉ። በዚህም ምክንያት፣ ደን ጠባቂና ተንከባካቢ የሆኑት ኢሆር ፌዳክ እንደተናገሩት “ለይሖዋ ምሥክሮች የተመደበው ቦታ በጣም ንጹሕ ነው።”

ፈቃደኛ ሠራተኞቹ የሰበሰቡትን ቆሻሻ ጠርሙሱን፣ ወረቀቱንና ፕላስቲኩን ለየብቻ በማድረግ በዓይነት በዓይነት ይለያሉ፤ ይህም እነዚህን ነገሮች በድጋሚ ጥቅም ላይ ለማዋል ያስችላል። ይህን የሚያደርጉት ሕጉ ስለሚያስገድዳቸው ሳይሆን በፈቃደኝነት ነው። ቀጥሎም ቆሻሻው ወደ አንድ ቆሻሻ አስወጋጅ ድርጅት ይወሰዳል። ከ2016 አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች የሰበሰቡትን ቆሻሻ ለማስወገድ የሚያስፈልገውን ወጪ በራሳቸው ተነሳሽነት መክፈል ጀምረዋል። ኢሆር ፌዳክ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያደርጉልን እገዛ ማመስገን እፈልጋለሁ። በጣም ትልቅ እርዳታ እያደረጉልን ነው።”

“ማጽዳት ክብሬን አይቀንሰውም”

የይሖዋ ምሥክሮቹ በየዓመቱ በሚደረገው ደን ማጽዳት ሥራ መካፈል ያስደስታቸዋል። ለማኅበረሰቡ እንዲሁም ለደኑ ደህንነት አስተዋጽኦ ማበርከት ይፈልጋሉ። ፎልከር የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር የተናገረው ሐሳብ የብዙዎቹን አመለካከት ይገልጻል፦ “ማጽዳት ክብሬን አይቀንሰውም። ሌሎችን የሚጠቅም ነገር ማድረግ የሚያስከብር ድርጊት ነው፤ ለእኔም እርካታ ይሰጠኛል።”

አንጄሊካ ደግሞ “ለእኔ ዋናው ነገር ‘ቆሻሻውን የጣለው ማን ነው?’ የሚለው ሳይሆን ‘አካባቢውን ለማጽዳት እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ?’ የሚለው ነው” በማለት ተናግራለች። የ78 ዓመት አረጋዊ የሆኑት ሎይስ የተባሉ ሴትም በዚህ ዘመቻ ተካፍለው ነበር። እንዲህ ብለዋል፦ “በጫካው ውስጥ ስትንሸራሸሩ በምታዩት ቆሻሻ ከመበሳጨት ይልቅ ቆሻሻውን በማንሳት አካባቢውን ማጽዳት የተሻለ ነው።”

ቭየስላቭ እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚያዩን ጥሩ ልብስ ለብሰንና ከረባት አድርገን እምነታችንን ለሌሎች ለማካፈል ስንሄድ ነው። ሆኖም እጅጌያችንን ሰብስበን ደን ለማጽዳትም ሆነ ሰዎችን በሚጠቅም ሌላ ሥራ ለመሥራትም ፈቃደኞች ነን።”