የይሖዋ ምሥክሮች ረስቶፍ አን ዳን የተባለችውን ከተማ በማስዋቡ ሥራ ተካፈሉ
በደቡባዊ ሩሲያ ከሚገኙ ከተሞች መካከል ትልቋ የሆነችው የረስቶፍ አን ዳን ከተማ ዋና አስተዳዳሪ፣ ግንቦት 20, 2015 ለይሖዋ ምሥክሮች የምስጋና ደብዳቤ ላኩ፤ ይህን ደብዳቤ የላኩት የይሖዋ ምሥክሮች “በጸደይ ወቅት በሚደረገው ከተማዋን የማስዋብ ሥራ ላይ ላደረጉት ንቁ ተሳትፎ” ለማመስገን ነው።
ከአራት ጉባኤዎች የተውጣጡ የይሖዋ ምሥክሮች ከተማዋን ለማስዋብ በተደረገው ዘመቻ የተካፈሉ ሲሆን በከተማዋ መንገዶችና በወንዝ ዳርቻዎች የተከማቸውን ቆሻሻና ፍርስራሽ ሰብስበዋል። በጥቂት ሰዓታት የሞሏቸውን 300 ገደማ የሚሆኑ የቆሻሻ ከረጢቶች የቆሻሻ ማንሻ መኪና መጥቶ ወስዷቸዋል።
እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበረሰቡ በሚያከናውነው ሥራ ላይ ለመሳተፍ ይህን ያህል ጥረት ያደረጉት ለምንድን ነው? የ67 ዓመቷ ራይሳ እንዲህ ብላለች፦ “ጉዳዩ እኔንም ይመለከታል። የምኖርባት ከተማ ንጹሕ እንድትሆን የምፈልገው ነዋሪዎቿ በሙሉ ንጹሕ በሆነ ቦታ እንዲኖሩ ስለምፈልግ ነው። የሠራነውን ሥራ ብዙ ሰዎች ልብ ባይሉትም በዚህ ሥራ ላይ መካፈሌ ያስደስተኛል። ደግሞም ይሖዋ ሥራችንን እንደሚያይ እርግጠኛ ነኝ።” አሌክሳንደርም እንዲህ ብሏል፦ “ለሰዎች ከመስበክ በተጨማሪ እነሱን የሚጠቅሙ ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት እንፈልጋለን። ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ነገር ሳደርግ ደስታና እርካታ ይሰማኛል።”
የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ በአካባቢው የነበሩትን ሰዎች አስደንቋቸዋል። አንድ የአካባቢው ነዋሪ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያከናውኑት ሥራ ገንዘብ እንደማይከፈላቸው ሲያውቅ በጣም ተገረመ። ከዚያም አብሯቸው በጽዳቱ ሥራ ለመካፈል ወሰነ፤ በኋላም እንዲህ ብሏል፦ “አካባቢን ማጽዳት ይህን ያህል አስደሳችና አርኪ ሊሆን ይችላል ብዬ አስቤ አላውቅም! አንዳንዶቻችሁ የምትኖሩት በዚህ አካባቢ ባይሆንም አካባቢያችንን ለማጽዳት ስትሉ ወደዚህ መጥታችኋል!”
አንድ የከተማዋ ባለ ሥልጣን አንድን አካባቢ ሲያጸዱ የነበሩ ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ብዙ ቆሻሻ እንደሰበሰቡ ተመለከተ። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮቹን ከሰበሰቡት የቆሻሻ ከረጢት ጎን ፎቶግራፍ ካነሳቸው በኋላ ፎቶግራፉን “ሥራው እንዴት መሠራት እንዳለበት ለሌሎች ለማሳየት” እንደሚጠቀምበት ተናግሯል።