በማዕከላዊ አውሮፓ ለስደተኞች የተበረከተ እርዳታ
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከደቡባዊ እስያ የመጡ በርካታ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ጎርፈዋል። የመንግሥት ድርጅቶችና ፈቃደኛ ሠራተኞች እነዚህን ስደተኞች ለመርዳት ሲሉ ምግብ፣ መጠለያና የሕክምና አገልግሎት እየሰጧቸው ነው።
ሆኖም ስደተኞች ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ቁሳዊ እርዳታ ብቻ አይደለም። ብዙዎቹ ባሳለፉት አሰቃቂ ነገር የተነሳ የስሜት ቀውስ ገጥሟቸዋል፤ በመሆኑም መጽናኛና ተስፋ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በማዕከላዊ አውሮፓ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ስደተኞቹን ትኩረት ሰጥተው በማዳመጥና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን አጽናኝ መልእክት በማካፈል የስደተኞቹን ሥነ ልቦናዊ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት እያደረጉ ነው።
ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኝ መጽናኛ
ከነሐሴ 2015 አንስቶ በኦስትሪያና በጀርመን ውስጥ ከሚገኙ ከ300 በላይ ጉባኤዎች የተውጣጡ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ስደተኞችን ለማጽናናት ልዩ ጥረት አድርገዋል። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ስደተኞች መጽሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች በሚሰጠው መልስ ላይ መወያየት በጣም እንደሚያስደስታቸው አስተውለዋል፦
በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከነሐሴ እስከ ጥቅምት 2015 ባሉት ወራት ውስጥ ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮ በማዘዝ ጽሑፎቹን በነፃ ለስደተኞቹ አበርክተዋል።
የቋንቋ ልዩነትን ማሸነፍ
አብዛኞቹ ስደተኞች የሚናገሩት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ብቻ ነው። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች የተለያዩ ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን የያዘውን jw.org የተባለ ድረ ገጽ ይጠቀማሉ። በኤርፉርት፣ ጀርመን ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው የሚያገለግሉት ማቲያስና ፔትራ “አንዳንድ ጊዜ የምንግባባው በአካላዊ መግለጫዎች፣ በፎቶ ወይም በሥዕል ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ቋንቋ ለመማር እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀውን JW Language የተባለ አፕሊኬሽን በመጠቀም ለስደተኞቹ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመናገር ጥረት ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ በበርካታ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችና ቪዲዮዎች የያዘውን JW Library የተባለውን አፕሊኬሽን፣ ጥቅሶችንና ቪዲዮዎችን ለማሳየት ይጠቀሙበታል።
ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል
በሽቫይንፉርት፣ ጀርመን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል፦ “በጣም ብዙ ሰዎች ከበቡን። በሁለት ሰዓት ተኩል ጊዜ ውስጥ 360 የሚሆኑ ጽሑፎችን ለስደተኞች አበርክተናል። ብዙዎቹ ጭንቅላታቸውን ጎንበስ በማድረግ አመስጋኝነታቸውን ይገልጹ ነበር።” በዲትስ፣ ጀርመን ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ የሚያገለግለው ቮልፍጋንግም እንዲህ ብሏል፦ “ስደተኞቹ ትኩረት የሚሰጣቸው ሰው መኖሩ በጣም ያስደስታቸዋል። አንዳንድ ጊዜ በአምስት ወይም በስድስት የተለያዩ ቋንቋዎች ጽሑፎችን እንድንሰጣቸው ይጠይቁናል።”
ብዙዎቹ ጽሑፉ እንደተሰጣቸው ማንበብ ይጀምራሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ተመልሰው በመምጣት የይሖዋ ምሥክሮቹን ያመሰግኗቸዋል። በበርሊን፣ ጀርመን የምትኖር ኢሎንካ የተባለች የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “ሁለት ወጣቶች ጽሑፎች ወሰዱ። ከዚያም ከግማሽ ሰዓት በኋላ በስጦታ መልክ ሊያበረክቱልን ዳቦ ይዘው መጡ። አመስጋኝነታቸውን ለመግለጽ ሊሰጡን የሚችሉት ሌላ ነገር የሌላቸው በመሆኑ ይቅርታ ጠየቁን።”
‘እናመሰግናለን! በጣም እናመሰግናለን!’
የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች፣ ባለ ሥልጣናትና በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች በፈቃደኝነት የሚያከናውኑትን ሥራ በአድናቆት ይመለከቱታል። ወደ 300 ለሚጠጉ ስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ አንድ የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ እንዲህ ብሏል፦ “እናመሰግናለን! ለውጭ አገር ሰዎች ደህንነት ይህን ያህል ትኩረት ስለሰጣችሁ በጣም እናመሰግናለን!” በአንድ የስደተኞች መጠለያ የሚሠራ ሌላ የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ ደግሞ ስደተኞቹ “በቀን ውስጥ ሦስቴ ከመመገብ ውጪ ሌላ የሚያደርጉት ነገር ስለሌላቸው” በቋንቋቸው የሚያነቡት ጠቃሚ ነገር ማግኘታቸው በጣም ጥሩ እንደሆነ ተናግሯል።
በኦስትሪያ የሚኖሩት ሜሪየንና ባለቤቷ ስቴፈን በዚያ ለጥበቃ ተመድበው ለመጡ ሁለት ፖሊሶች፣ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው የሚያገለግሉት ለምን እንደሆነ አብራሩላቸው። ፖሊሶቹ ካመሰገኗቸው በኋላ ሁለት መጽሐፍ እንዲሰጧቸው ጠየቁ። ሜሪየን “ፖሊሶች ለምንሠራው ሥራ ያላቸውን አድናቆት በተደጋጋሚ ይገልጹልናል” ስትል ተናግራለች።
አዘውትራ ለስደተኛ መጠለያው አንዳንድ ነገሮችን በስጦታ የምታበረክት በኦስትሪያ የምትኖር አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች የአየር ሁኔታው ምንም ዓይነት ቢሆን ስደተኞቹን ለመርዳት እንደሚመጡ አስተዋለች። አንድ ቀን እንዲህ አለቻቸው፦ “ስደተኞቹ ቁሳዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ከሁሉም ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ግን ተስፋ ነው። እናንተ ደግሞ ይህን እየሰጣችኋቸው ነው።”