በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች እስረኞችን በመርዳታቸው አድናቆት ተቸራቸው

የይሖዋ ምሥክሮች እስረኞችን በመርዳታቸው አድናቆት ተቸራቸው

በአውስትራሊያ የሚኖሩ ዘጠኝ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በአገሪቱ ውስጥ ባለ ትልቅ የሕገ ወጥ ስደተኞች እስር ቤት ውስጥ ለሚገኙት እስረኞች ላበረከቱት “ላቅ ያለ አገልግሎት” ምስጋና የያዘ የምሥክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። ይህን የምሥክር ወረቀት ለይሖዋ ምሥክሮቹ የሰጠው በምዕራብ አውስትራሊያ በምትገኘው በደርቢ ከተማ አቅራቢያ ያለው የከርተን የሕገ ወጥ ስደተኞች እስር ቤት ማዕከል a ነው።

የይሖዋ ምሥክሮቹ፣ በየሳምንቱ እስረኞቹን በመጠየቅ ታሪካቸውን ሲናገሩ ያዳምጧቸዋል፤ እንዲሁም አጽናኝና ተስፋ ሰጪ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ይነግሯቸዋል። የማዕከሉ የሃይማኖትና የባሕል አማካሪ የሆኑት ክሪስቶፈር ሪዶክ “የይሖዋ ምሥክሮቹ የሚያደርጉት ጉብኝት በእስረኞቹ ላይ የሚያመጣውን ውጤት ወዲያውኑ ማየት ይቻላል” በማለት ተናግረዋል። በተጨማሪም የእስረኞቹ ጠባይ እንደተሻሻለና ከእያንዳንዱ ጉብኝት በኋላ ደስታቸው እንደሚጨምር ገልጸዋል፤ ይህም የሆነው እስረኞቹ “የእነሱ ደህንነት ከልብ የሚያሳስባቸው ሰዎች እንዳሉ በማወቃቸው” እንደሆነ አማካሪው ተናግረዋል።

አቶ ሪዶክ እንደተናገሩት ማዕከሉ የምስጋና ወረቀቱን ለይሖዋ ምሥክሮቹ የሰጠው ‘በማዕከሉ ሥር ያሉት ግለሰቦች ሕይወት እንዲሻሻል’ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አድናቆቱን በጥቂቱ ለመግለጽ ነው። አክለውም የይሖዋ ምሥክሮቹ “ለቤተሰባቸው፣ ለጉባኤያቸውና ለእምነታቸው ክብር አምጥተዋል” ብለዋል።

a ማዕከሉ 1,500 ሰዎችን የመያዝ አቅም አለው።