በፊሊፒንስ ያሉ መምህራን የJW.ORGን ጥቅም ተገነዘቡ
በ2016፣ የይሖዋ ምሥክሮች በፊሊፒንስ ባለው ዛምቧንጋ ዴል ኖርቴ ግዛት ላሉ መምህራን jw.org የተባለው ድረ ገጻችን ላይ የሚገኙት ቪዲዮዎችና ርዕሶች ስላላቸው ጥቅም የማስተዋወቅ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ይህን ከማድረጋቸው በፊት ግን በርዕሰ ከተማዋ በዲፖሎግ የሚገኘውን የግዛቱን የትምህርት ቢሮ ለማነጋገር ሄደው ነበር። ኃላፊዎቹ በjw.org በጣም በመደነቃቸው የይሖዋ ምሥክሮቹ በዛምቧንጋ ዴል ኖርቴ በሚሰጡ ሦስት ሴሚናሮች ላይ ለመካፈል ከተለያዩ ከተሞች ለሚመጡ አስተማሪዎች የ30 ደቂቃ ገለጻ እንዲያደርጉ ጋበዟቸው።
ገለጻዎቹ የተሰጡት እንዴት ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች በእያንዳንዱ ሴሚናር ላይ ለተገኙ ወደ 300 የሚጠጉ አስተማሪዎች የተወሰኑ ቪዲዮዎችንና ድረ ገጻችን ላይ የሚገኙ ርዕሶችን አሳይተዋል። ተሳታፊዎቹ በተለይ “ዕዳ በሚኖርባችሁ ጊዜ” የሚለው ርዕስ ትኩረታቸውን ስቦት ነበር። ብዙዎቹ አስተማሪዎች፣ የተሰጣቸው ገለጻ ለተማሪዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ለእነሱም ጠቃሚ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ሁሉም መምህራን በርካታ ጠቃሚ መረጃዎች የያዘውን ድረ ገጻችንን የሚያስተዋውቀውን በአእምሯችን ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው? የተባለውን ትራክት ወስደዋል። እንዲያውም አንዳንድ አስተማሪዎች ከድረ ገጻችን ላይ ቪዲዮዎችን አውርደዋል።
በሦስቱም ሴሚናሮች ላይ የተደረጉት ገለጻዎች በጣም የተሳኩ ስለነበሩ የግዛቱ የትምህርት ቢሮ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ 600 ለሚጠጉ የትምህርት አማካሪዎችና መምህራን ተጨማሪ ገለጻዎችን እንዲሰጡ ዝግጅት አደረገ። በዚህ ወቅት የነበሩት ተሳታፊዎችም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
“ድረ ገጻችሁ በጣም ጠቃሚ ነው”
ከተሳታፊዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ገለጻዎቹና ድረ ገጹ እንደጠቀማቸው ከጊዜ በኋላ ተናግረዋል። አንዲት መምህር “ምስጋናዬን መግለጽ እፈልጋለሁ። ድረ ገጹ ተማሪዎቼን ሳስተምር ጠቅሞኛል” ስትል ተናግራለች። ሌላ መምህርም እንዲህ ብላለች፦ “ስለተለያዩ ጉዳዮች በተለይም ውጥረትን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ ማወቅ እፈልግ ነበር። ድረ ገጻችሁ ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን በዕድሜ ከፍ ላሉትም በጣም ጠቃሚ ነው።”
JW.ORG ስለተባለው ድረ ገጽ የተሰጡትን ገለጻዎች የሰሙ ከ350 የሚበልጡ ባለሙያዎች ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። የይሖዋ ምሥክሮቹም ጥያቄ ላቀረቡላቸው ሁሉ ተጨማሪ ጽሑፎችን የሰጡ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጠቃሚ ምክሮችም አካፍለዋቸዋል።
ከ1,000 የሚበልጡ መምህራን በዛምቧንጋ ዴል ኖርቴ የተካሄዱትን የjw.org ገለጻዎች በመስማታቸውና jw.org ለማስተማር የሚረዱ ጠቃሚ መረጃዎችን የያዘ መሆኑን በመገንዘባቸው የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ተደስተዋል። ይህ ጠቃሚ የማስተማሪያ ድረ ገጽ ከባሕርይ፣ ከሥነ ምግባር እንዲሁም ከመንፈሳዊነት ጋር የተያያዙ በርካታ መመሪያዎችን የያዘ በመሆኑ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ መምህራንን ሊጠቅም ይችላል። a
a በፊሊፒንስ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎቻቸው እውቀት ከማስተላለፍ ባለፈ ተማሪዎቻቸው “የሥነ ምግባርና የሃይማኖት መመሪያዎችን እንዲከተሉ የመርዳት [እንዲሁም] ጥሩ ምግባርና የተገራ ባሕርይ እንዲኖራቸው የማገዝ” ኃላፊነት አለባቸው።”—የ1987 የፊሊፒንስ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 14፣ ንዑስ አንቀጽ 3.2