የታመሙ ሰዎችን ማጽናናትና መርዳት
ከባድ የጤና እክል የገጠማቸው ሰዎች በቀላሉ በጭንቀት ሊዋጡ ይችላሉ፤ በሆስፒታል ክትትል ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ደግሞ የሚሰማቸው ጭንቀት ይበልጥ ሊጨምር ይችላል። ከዚህ አንጻር፣ ለጤና ባለሙያዎች የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ “የሕሙማንን ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ለጤናቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ” ይላል። a
የይሖዋ ምሥክሮችም ይህንኑ በመገንዘብ፣ ሆስፒታል ገብተው የሚታከሙ የእምነት አጋሮቻቸውን ለማጽናናትና ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። የጉባኤ ሽማግሌዎች ቅድሚያውን ወስደው፣ በጉባኤያቸው ውስጥ ያሉ የታመሙ ሰዎችን ይጠይቃሉ። ይሁንና አንድ የይሖዋ ምሥክር ከሚኖርበት ቦታ ራቅ ብሎ በሚገኝ ሆስፒታል ሕክምና መከታተል ቢያስፈልገውስ? የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ የሕሙማን ጠያቂ ቡድኖችን አደራጅተዋል። በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች ከሌላ አካባቢ አልፎ ተርፎም ከሌላ አገር የመጡ የታመሙ የይሖዋ ምሥክሮችንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ አዘውትረው ወደ ሆስፒታሎች ያቀናሉ። በስድስት አህጉራት ውስጥ በሚገኙ ወደ 1,900 የሚጠጉ የሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ውስጥ በፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ከ28,000 በላይ ወንድሞች አሉ። b
የሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ምን መንፈሳዊ ማጽናኛ ይሰጣሉ?
በሕሙማን ጠያቂ ቡድን ውስጥ የሚያገለግለው ዊልያም እንዲህ ብሏል፦ “የታመሙት የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የቤተሰባቸው አባላት በሆስፒታሉ ተገኝቼ እነሱን ማዳመጤና ማነጋገሬ ብቻ እንኳ ያጽናናቸዋል። ይሖዋ አምላክ ያሉበትን ሁኔታ እንደሚያውቅና እንደሚያስብላቸው እነግራቸዋለሁ። ታማሚዎቹም ሆኑ የቤተሰባቸው አባላት አብሬያቸው ስጸልይ ይደሰታሉ።”
በርካታ ወንድሞችና እህቶች የሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ባደረጉላቸው ጉብኝት ላገኙት ማበረታቻ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ከ7,000 በላይ የሕሙማን ጠያቂ ቡድን አባላት ባሉባት በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች የሰጧቸው አስተያየቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
ፕሪሲላ እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ አንጎሉ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት ሆስፒታል በገባበት ወቅት መጥታችሁ ስለጠየቃችሁት አመሰግናለሁ። እሱም በጉብኝታችሁ ልቡ በጣም ተነክቷል! እንዲህ ያለ ዝግጅት መኖሩ አስደንቆታል። ያደረጋችሁለት ጉብኝት ከሕመሙ ቶሎ እንዲያገግም የረዳው ይመስለኛል።”
ታመው የነበሩትን እናቷን በሞት ያጣችው ኦፊልያ ለአንዱ የሕሙማን ጠያቂ ቡድን አባል እንዲህ ብላው ነበር፦ “እናቴ ስለጠየቃችኋት በጣም ተደስታ ነበር! ይሖዋ ወደ እሷ እንደላካችሁ እርግጠኛ ነበረች። ላሳያችሁን ፍቅርና አሳቢነት ከልብ አመሰግናችኋለሁ።”
አንድ ታማሚ፣ በሕይወት የሚቀጥለው ለተወሰኑ ቀናት ብቻ እንደሆነ ስለተነገረው በጣም ተረብሾና ተጨንቆ ነበር። የሕሙማን ጠያቂ ቡድን አባል የሆነው ጄምስ ከዚህ ግለሰብ ጋር አብሮ ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በማሳየት አጽናናው። ጄምስ እንዲህ ብሏል፦ “በቀጣዩ ቀን ልጠይቀው ስሄድ አመለካከቱ በአስደናቂ መልኩ ተቀይሮ ነበር። ሊሞት የቀረው ጥቂት ቀናት ብቻ እንደሆነ ቢያውቅም ይሖዋ እንደሚረዳው ተማምኖ ነበር፤ እንዲያውም እኔንም አበረታቶኛል!”
የሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ምን እርዳታ ያደርጋሉ?
ርቆ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ባሏ የሞተባት ፖሊን እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ቤተሰባችን ባሳለፋቸው በጣም አስጨናቂ ጊዜያት ላደረጋችሁልን እርዳታ እጅግ እናመሰግናለን። በቀጣዩ ቀን ወደ ሥራ መሄድ ቢጠበቅባችሁም እኛን ለማግኘት በእኩለ ሌሊት ወደ ሆስፒታል ለመምጣት ፈቃደኛ መሆናችሁን ማወቃችን አጽናንቶናል። ለአሥራ አንዳችንም ማረፊያ ቦታ ስላመቻቻችሁልን እንዲሁም እስከ መጨረሻው ከጎናችን ስላልተለያችሁ እናመሰግናለን። ይሖዋ እና ድርጅቱ እኛን ለማጽናናት እንዲህ ያለ ዝግጅት ስላደረጉልን በጣም አመስጋኝ ነኝ።”
ኒኪ፣ ጌልና ሮቢን ከቤታቸው 300 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኝ ቦታ የመኪና አደጋ ደርሶባቸው ነበር። የሕሙማን ጠያቂ ቡድን አባል የሆነው ካርሎስ ስለ ጉዳዩ ሲሰማ እነሱን ለማግኘት ወደ ሆስፒታል ሄደ። ካርሎስ “የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውንም እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኔን ገለጽኩላቸው፤ ከዚያም ኒኪ ወደ ውስጥ ገብታ ሕክምና እንድታገኝ የኒኪን ቡችላ ያዝኩላት” ሲል ተናግሯል። ቀጥሎም በሕሙማን ጠያቂ ቡድን ውስጥ የሚያገለግለው ከርትስ ከባለቤቱ ጋር ወደ ሆስፒታሉ መጣ። እነዚህ ባልና ሚስት በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የቤተሰባቸው አባላት እስኪደርሱላቸው ድረስ ለበርካታ ሰዓታት በሆስፒታሉ ውስጥ ቆይተዋል። የዚህ ቤተሰብ ወዳጅ የሆነ አንድ ግለሰብ እንዲህ ብሏል፦ “ሦስቱም በተደረገላቸው እንክብካቤ ተበረታተዋል። በተለይ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነችው የኒኪ እህት ሮቢን የሕሙማን ጠያቂ ቡድን አባላት ባደረጉላቸው እርዳታ በጣም ተደንቃ ነበር።”
a “የሕሙማንን ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት” በሚል ርዕስ ዘ ጆይንት ኮሚሽን ጆርናል ኦን ዘ ኳሊቲ ኤንድ ፔሸንት ሴፍቲ፣ ታኅሣሥ 2003፣ ጥራዝ 29፣ ቁ. 12፣ ገጽ 661 ላይ የታተመ
b ልክ እንደ ሁሉም የጉባኤ ሽማግሌዎች ሁሉ በሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉት ሽማግሌዎችም መንፈሳዊ እረኞች፣ አስተማሪዎች እንዲሁም ወንጌላውያን በመሆን የጉባኤያቸውን አባላት ይረዳሉ። ለሚያከናውኑት አገልግሎት ክፍያ አይቀበሉም፤ ያም ቢሆን በፈቃደኝነት እና ለማገልገል በመጓጓት ሥራቸውን ያከናውናሉ።—1 ጴጥሮስ 5:2