ቦትስዋና ውስጥ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ማዕድናት ለአውደ ርዕይ ቀረቡ
በዓለም ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የአልማዝ ማዕድን በሚገኝባት በቦትስዋና ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከነሐሴ 22 እስከ 28, 2016 በተዘጋጀው የግብይት አውደ ርዕይ ላይ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ማዕድናት ለሕዝብ እይታ አቅርበው ነበር። በተሰጣቸው ኪዮስክ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን፣ የjw.org ድረ ገጽንና ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር እንዲኖር የሚያበረታቱ ቪዲዮዎችን ለእይታ አቅርበው ነበር።
ኪዮስኩን የጎበኙ ወላጆችና ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋል የሚቻልበትን መንገድ በሚያስተምሩት የይሖዋ ወዳጅ ሁን በሚል ርዕስ በቀረቡት ተከታታይ የአኒሜሽን ቪዲዮዎች ተማርከው ነበር። የቦትስዋና ብሔራዊ ቋንቋ በሆነው በሴጽዋና የተዘጋጁ አኒሜሽን ቪዲዮዎች ጥቂት በመሆናቸው በአውደ ርዕዩ ላይ የተገኙት ብዙ ሰዎች የተመለከቷቸውን ቪዲዮዎች ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ጠይቀዋል።
ከመላ አገሪቱ የመጡት ጎብኚዎች በግምት 10,000 የሚሆኑ የታተሙ ጽሑፎችን የወሰዱ ሲሆን 120 ሰዎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለመማር ጥያቄ አቅርበዋል። ብዙ ሰዎች በአውደ ርዕዩ ላይ የእንግሊዝኛና የሴጽዋና ቋንቋ ጉባኤዎች ተባብረው ሲሠሩ በማየታቸው ተደንቀዋል።
አዘጋጆቹ በአውደ ርዕዩ ላይ የተለያዩ ነገሮች ለእይታ የቀረቡባቸውን ኪዮስኮችና ሌሎች ማሳያዎችን ከገመገሙ በኋላ አንደኛ ለወጣው ሽልማት የሰጡ ሲሆን ይህን ሽልማት ያገኙትም የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።