በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በላፕላንድ የተደረገ ውጤታማ ዘመቻ

በላፕላንድ የተደረገ ውጤታማ ዘመቻ

የሳሚ ሕዝቦች ስዊድንን፣ ኖርዌይንና ፊንላንድን በሚያካትተው በጣም ሰፊ ክልል ላይ ይኖራሉ፤ እነዚህ ሕዝቦች የራሳቸው ባሕሎች፣ ልማዶችና ቋንቋዎች አሏቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ለሳሚ ሕዝቦች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማካፈል በቅርቡ ሁለት ነገሮችን አድርገው ነበር።

በመጀመሪያ፣ በ2015 የመከር ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን በሳሚ ቋንቋ መተርጎም ጀመሩ። a ሁለተኛ፣ በ2016 እና በ2017 በተካሄዱ ሁለት ልዩ ዘመቻዎች ወደ ላፕላንድ ተጓዙ፤ የይሖዋ ምሥክሮች በርካታ ርኤሞች (የደጋ አጋዘኖች) ወደሚገኙበት ወደዚህ ራቅ ያለ ስፍራ የተጓዙት የተተረጎሙትን ጽሑፎች ለሳሚ ሕዝቦች ለማድረስ ነበር።

“ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ሥራ”

ግንቦት 2017 በተደረገው ልዩ ዘመቻ ከስዊድን፣ ከኖርዌይና ከፊንላንድ የተውጣጡ ከ200 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበው ነበር፤ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በላፕላንድ በሺዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ውስጥ ተበታትነው ወደሚገኙ ትናንሽ መንደሮች ለመሄድ ፈቃደኞች ነበሩ። አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች የተወሰኑ የሳሚ ቋንቋ አገላለጾችን በመማር ለዘመቻው ዝግጅት አድርገው ነበር፤ ይህም የሳሚ ሕዝቦችን አስገርሟቸዋል። በካሪጋስኒኤሚ ያገለገለው ዴኒስ “የሳሚ ሕዝቦች በቋንቋቸው ለመናገር ያደረግነው ጥረት አስደስቷቸዋል ብሎም እንደምናስብላቸው እንዲሰማቸው አድርጓል” ሲል ተናግሯል።

የሳሚ ሕዝቦች ተፈጥሮንና የዱር እንስሳትን ስለሚወዱ ምድር ገነት እንደምትሆን የሚገልጸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኝ ተስፋ መስማት ያስደስታቸዋል። (መዝሙር 37:11) ለምሳሌ፣ አንዲት የሳሚ ሴት ከአምላክ የተላከ ምሥራች! በተባለው ብሮሹር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች፤ ይህች ሴት አምላክ ወደፊት ለሰው ልጆች የሚያደርገውን ነገር ስትማር እሷ ያለችበት ሃይማኖት አገልጋይ ምድር ገነት እንደምትሆን አንድም ቀን ያልነገራት ለምን እንደሆነ በግርምት ትጠይቅ ነበር።

ብዙዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው ስለጎበኟቸው ምስጋናቸውን ገልጸዋል። አንድ ባለሱቅ ያገኛቸውን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች አመስግኗቸዋል። ግለሰቡ “አስፈላጊና ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ሥራ” እያከናወኑ እንዳሉ ገልጾላቸዋል፤ እንዲያውም ወደ ሱቁ ገብተው የሚፈልጉትን ምግብ እንዲወስዱ የይሖዋ ምሥክሮቹን ጋብዟቸዋል። ከዚያም የወሰዱትን ዕቃ ዋጋ ከፍሎላቸዋል።

በዘመቻው ወቅት የሳሚ ሕዝቦች ወደ 180 የሚሆኑ ቪዲዮዎችን ያዩ ሲሆን ከ500 የሚበልጡ ጽሑፎችንም ወስደዋል። ብዙዎች፣ በሚናገሩት ቋንቋ የተዘጋጀ ማንኛውም ጽሑፍ እንዲሰጣቸው ይጠይቁ ነበር። በተጨማሪም 14 የሳሚ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረዋል።

“ባለሙያዎች የደከሙበት ሥራ”

የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች ያነበቡ የተለያዩ የሳሚ ሰዎች ለትርጉም ሥራው ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። አስተማሪና የሳሚ ፓርላማ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል የሆነው ኒላ ታፒኦላ “ጽሑፎቻችሁ በጣም በጥሩ መንገድ ተተርጉመዋል” ብሏል። አክሎም ጽሑፎቹ “ለማንበብ ቀላል እንዲሁም የቋንቋውን ለዛ በጠበቀ መንገድ” የተዘጋጁ እንደሆኑ ተናግሯል። በፊንላንድ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ የሚኖር አንድ የሳሚ ሰው “ባለሙያዎች የደከሙበት ሥራ እንደሆነ ያስታውቃል” በማለት ተናግሯል።

በፊንላንድ እና በኖርዌይ ድንበር ላይ በምትገኘው በካሪጋስኒኤሚ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ የሳሚ ሰው ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለውን ብሮሹር የመጀመሪያ ትምህርት አወያይተውት ነበር። ጽሑፉ የተተረጎመበት ጥራት ያስደነቀው ይህ አስተማሪ፣ የሳሚ ቋንቋን ለተማሪዎቹ ለማስተማር ብሮሹሩን ትምህርት ቤት ውስጥ መጠቀም ይችል እንደሆነ የይሖዋ ምሥክሮቹን ፈቃድ ጠይቋቸዋል።

የተለያዩ ቪዲዮዎችና ትራክቶች እንዲሁም አንድ ብሮሹር ወደ ሳሚ ቋንቋ ተተርጉመዋል። jw.org የተባለው ድረ ገጻችን ከየካቲት 29, 2016 አንስቶ በሳሚ ቋንቋ ይገኛል። የሳሚ ቋንቋ ተናጋሪዎች ድረ ገጻችንን በየወሩ ከ400 ጊዜ በላይ የሚጎበኙ ሲሆን 350 የሚያህሉ ርዕሶችን፣ በድምፅ የተቀዱ ነገሮችን እንዲሁም ቪዲዮዎችን ያወርዳሉ።

በዘመቻው፣ የሳሚ ሰዎችም ሆኑ በፈቃደኝነት ሄደው የጎበኟቸው የይሖዋ ምሥክሮች ተደስተዋል። ወደ ኡትዝዮኪ መንደር ሄደው ያገለገሉት ሄንሪክ እና ሂልያ ማሪያ፣ የሳሚ ሕዝቦች “መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበረሰባቸውን በብዙ መንገዶች እንደሚጠቅመው” ማስተዋል ችለዋል ሲሉ ተናግረዋል። ወደ ኡትዝዮኪ ሄደው የነበሩት ላውሪ እና ኢንጋም እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ዘመቻ አምላክ እንደማያዳላ አስታውሶናል። እኛም በእነዚህ ራቅ ባሉ ቦታዎች ለሚገኙ ሰዎች የእሱን ዓይነት ፍቅር ማሳየታችን አስደስቶናል።”

a የሳሚ ሕዝቦች የሚናገሯቸው በርካታ ቋንቋዎች አሉ። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው የሳሚ ሕዝብ የደቡብ ሳሚ ቋንቋን ይናገራል” ሲል ይገልጻል። የይሖዋ ምሥክሮችም ጽሑፎቻቸውን ወደ ደቡብ ሳሚ ቋንቋ ተርጉመዋል። ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል ይህ ርዕስ አብዛኞቹ የሳሚ ሕዝቦች የሚናገሩትን ቋንቋ ለማመልከት “የሳሚ ቋንቋ” የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል።