በሺንጉ ወንዝ ዳርቻዎች ምሥራቹን መስበክ
በሐምሌ 2013 መጀመሪያ ላይ፣ በብራዚል የሚኖሩ 28 የይሖዋ ምሥክሮች ከሳኦ ፌሊክስ ዱ ሺንጉ ተነስተው የካያፖ እና የዩሩና ሕንዶች ወደሚገኙበት ክልል መጓዝ ጀመሩ። የይሖዋ ምሥክሮቹ 15 ሜትር ርዝመት ባላት ጀልባ ላይ ተሳፍረው በሺንጉ ወንዝ ላይ ሽቅብ መጓዝ ጀመሩ፤ ይህ ወንዝ በስተ ሰሜን አቅጣጫ 2,092 ኪሎ ሜትር በመሄድ ከአማዞን ወንዝ ጋር ይቀላቀላል።
የይሖዋ ምሥክሮቹ ይህን ጉዞ ያደረጉት በወንዙ ዳርቻዎች ላይ በሚገኙት መንደሮች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ ነበር። በሦስተኛው ቀን ኮክራይሞሮ የምትባል መንደር ደረሱ። እንግዳ ተቀባይ የሆኑት የመንደሪቱ ነዋሪዎች እንግዶቹን በፈገግታ ተቀበሏቸው። እንዲያውም በዚያ ያገኟት አንዲት ሴት አንድ ለየት ያለ ምልክት አሳየቻቸው። ከይሖዋ ምሥክሮቹ ጋር አብሮ ይጓዝ የነበረ አንድ የአካባቢው ሰውም ሴትየዋ ያሳየችው ምልክት “ሁላችሁም ወደዚህ ኑ። ከሁላችሁም ጋር መተዋወቅ እንፈልጋለን!” የሚል መልእክት እንዳለው ገለጸላቸው።
የይሖዋ ምሥክሮቹ የመንደሪቱን ነዋሪዎች በሙሉ ማነጋገር የቻሉ ሲሆን ይህን ያደረጉት አንዳንዶቹን በፖርቹጋልኛ ቋንቋ፣ ሌሎቹን ደግሞ በምልክት ተጠቅመው በማነጋገር ነበር። የይሖዋ ምሥክሮቹ የያዟቸው ማራኪ የሆኑ ሥዕሎች ያሏቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በዚህ ረገድ እጅግ ጠቃሚ ድርሻ አበርክተዋል፤ በርካታ የመንደሪቱ ነዋሪዎች ጽሑፎችን በተለይም ደግሞ አምላክን ስማ የተባለውን ብሮሹር ወስደዋል።
በሳኦ ፌሊክስ ዱ ሺንጉ ልዩ አቅኚ ሆኖ የሚያገለግለው ዤርሶ አንድ የመንደሪቱ ነዋሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ሲያገኝ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ “መጽሐፉን አተኩሮ ካየው በኋላ በሁለቱም እጆቹ ሙጭጭ አድርጎ ያዘው፤ ለጥቂት ሰከንድ እንኳ ከእጁ ሊለየው አልፈለገም” ብሏል።
የይሖዋ ምሥክሮች በወንዙ ዳርቻ ላይ በሚገኙት መንደሮች ውስጥ ለሚኖሩ አድናቂ የሆኑ ሰዎች ወደ 500 የሚደርሱ መጽሐፍት፣ መጽሔቶችና ብሮሹሮች አበርክተዋል። የካዋቲሪ መንደር ነዋሪዎች ወደፊት ምድራችን ገነት እንደምትሆን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ በታላቅ ጉጉት አዳምጠዋል። የካያፖ ሕንዶች ወገን የሆነውና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የሚታይበት ቶንግዣይክዋ “ሰዎች በገነት ውስጥ ልክ የእኛ ዓይነት ኑሮ ይኖራሉ” በማለት ወደፊት ሊሆን ይችላል ብሎ የሚገምተውን ተናግሯል።
አብዛኞቹ የሳኦ ፌሊክስ ዱ ሺንጉ ከተማ ነዋሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች ለማድረግ ስላሰቡት ጉዞ ያውቁ ነበር። በዚህ ጉዞ ላይ የተካፈለችው ሲሞን አንዳንዶቹ የመንደሯ ነዋሪዎች እሷም ሆነች የጉዞ ጓደኞቿ ወደ መንደሮቹ እንዳይገቡ ሊከለከሉ እንደሚችሉ ስጋት እንዳላቸው ገልጸውላት እንደነበር ተናግራለች። ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት ችግር አልገጠማቸውም። ሲሞን “ሰዎቹ ጥሩ አቀባበል አድርገውልናል፤ እኛ ደግሞ ለሁሉም ሰብከንላቸዋል” በማለት ተናግራለች።