በቶሮንቶ በተካሄደው የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ላይ JW.ORGን ማስተዋወቅ
ከኅዳር 13 እስከ 16, 2014 በሜትሮ ቶሮንቶ የስብሰባ ማዕከል ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ የቀረበ ሲሆን የታተሙና በኤሌክትሮኒክ ፎርማት የተዘጋጁ መጻሕፍት በዐውደ ርዕዩ ላይ ለእይታ ቀርበው ነበር። በአራት ቀናት ውስጥ ከ20,000 በላይ ሰዎች ዐውደ ርዕዩን ጎብኝተውታል።
በዐውደ ርዕዩ ላይ ከተካፈሉት መካከል የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል፤ የይሖዋ ምሥክሮች የሕትመት ውጤቶቻቸውን የደረደሩበት መንገድ ቀልብ የሚስብ ከመሆኑም ሌላ ተመልካቾችን የሚያሳትፍ ነበር። በተጨማሪም የታብሌት ተጠቃሚዎች jw.orgን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ የሚያሳዩ መደርደሪያዎች ነበሩ።
ከዐውደ ርዕዩ አዘጋጆች መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ድረ ገጻችሁ በጣም ዘመናዊ ነው። ሌሎች ተሳታፊዎች ከእናንተ አቀራረብ ትምህርት መቅሰም ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ።” አንዳንድ ጎብኚዎች ድረ ገጹ ደረጃውን የጠበቀና ለአጠቃቀም ቀላል እንደሆነ እንዲሁም ወሳኝ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። በተጨማሪም ድረ ገጹ ሰዎች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮችና ለሚያሳስቧቸው ነገሮች የሚሆን የመፍትሔ ሐሳብ ይዟል፤ ይህም ብዙዎችን አስደንቋል።
መደርደሪያዎቹ ጋ ቆመው ሰዎችን የሚያስተናግዱት የይሖዋ ምሥክሮች፣ አብዛኞቹ ጎብኚዎች ከዐውደ ርዕዩ በፊት ስለ jw.org ሰምተው እንደማያውቁ ተናግረዋል። እያንዳንዱ ጎብኚ ማለት ይቻላል የአድራሻ ካርድ ወይም በአእምሯችን ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው? የተባለውን ትራክት ተቀብሏል። ብዙዎች ድረ ገጹን በድጋሚ እንደሚያዩት የገለጹ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸው መጥተው እንዲያነጋግሯቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
ዐውደ ርዕዩ በታየበት ሳምንት፣ ዓርብ “የልጆች ቀን” ስለነበር የይሖዋ ምሥክሮች jw.org ላይ የወጡ የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽኖችን የማሳየት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ከአስተማሪዎቻቸው ጋር በቡድን ሆነው የመጡ ተማሪዎችም መደርደሪያዎቹ ጋ ቆመው ቪዲዮዎቹን ተመልክተዋል።
ቺካጎ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሶችን በሚያትም ድርጅት ውስጥ የሚሠራ አንድ ሰው፣ ለእይታ በቀረበው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የጥራት ደረጃ በጣም እንደተደነቀ ተናግሯል። ግለሰቡ የዚህን መጽሐፍ ቅዱስ አሳታሚዎች ማግኘት እንደሚፈልግ ስለገለጸ የአድራሻ ካርድ ተሰጥቶታል።
በድረ ገጹ ላይ ከሚገኙት ከ700 የሚበልጡ ቋንቋዎች መካከል ጎብኚዎች 16ቱን ይኸውም የሚከተሉትን አይተዋል፦ ሂንዲ፣ ስዊድንኛ፣ ስፓንኛ፣ ቤንጋሊ፣ ታሚል፣ ትግርኛ፣ ቻይንኛ፣ አማርኛ፣ ኡርዱ፣ እንግሊዝኛ፣ ኮሪያኛ፣ ጉጃራቲ፣ ግሪክኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ፖርቱጋልኛና ቬትናምኛ።
ጎብኚዎችን ያስተናግድ የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር፣ ለሰዎች ስለ ድረ ገጻችን እንዲሁ በቃል ከመንገር ይልቅ በቀጥታ ድረ ገጹን ከፍቶ ማሳየት ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጿል። “ድረ ገጹን ለማስተዋወቅ ግሩም አጋጣሚ አግኝተን ነበር” ብሏል።