ጀርመን ውስጥ “ሽርሽር የሄዱ” የጽሑፍ ጋሪዎች
በዓለም ዙሪያ በትላልቅ ከተሞች ውስጥ በርካታ እግረኞች የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጇቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች የያዙ ጋሪዎች ብዙ ጊዜ ይመለከታሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክሮች ጀርመን ውስጥ በበርሊን፣ በኮሎን፣ በሃምቡርግ፣ በሙኒክና ሕዝብ በሚበዛባቸው ሌሎች ከተሞች ጽሑፎችን ይዘው ይቆማሉ።
ይሁን እንጂ በጽሑፍ ጋሪ አማካኝነት የሚሰጠው ምሥክርነት ጀርመኖች የእረፍት ጊዜ ለማሳለፍ በሚሄዱባቸው ትንንሽ ከተሞችም ውጤታማ ሊሆን ይችላል? ይህ ዘዴ በሰሜናዊ ጀርመን በሚገኙት ብዙዎች ለሽርሽር የሚሄዱባቸው ከተሞችና በባሕር ዳር በሚኖሩ ሰዎች እንዲሁም በባልቲክና በሰሜን ባሕር ላይ በሚገኙ ደሴቶች ዘንድ ተቀባይነት ይኖረው ይሆን? በ2016 በማዕከላዊ አውሮፓ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ያደራጀው ልዩ ዘመቻ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ አስገኝቷል። ከግንቦት እስከ ጥቅምት ድረስ ባሉት ወራት በቪየና፣ ኦስትሪያ የሚኖሩትን ጨምሮ 800 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በሰሜናዊ ጀርመን ውስጥ 60 በሚያህሉ ቦታዎች ጋሪዎቹን አቁመው ለማገልገል ራሳቸውን አቀረቡ፤ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ቀደም በትላልቅ ከተሞች የጽሑፍ ጋሪዎችን ተጠቅመው ይሰብኩ ነበር።
“እንደ እንግዳ አልቆጠሩንም”
የይሖዋ ምሥክሮቹ ወደ አካባቢው ሲደርሱ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር። አንዲት እህት የሚከተለውን ተናግራለች፦ “ብዙ ሰዎች ፍላጎት አሳይተዋል። ሰዎቹ ተግባቢና የማወቅ ጉጉት ያላቸው ከመሆናቸውም ሌላ ከእኛ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኞች ነበሩ።” ወደ ፕሎን ከተማ የተጓዘችው ሄይዲ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደ እንግዳ አልቆጠሩንም። የሚያውቁን አንዳንድ ሰዎች ሲያዩን እጃቸውን በማውለብለብ ሰላም ይሉን ነበር።” መስማትና መናገር የተሳነው አንድ ሰው በምልክት ቋንቋ “የማትገኙበት ቦታ የለም!” ብሏቸዋል። ይህ ሰው ከጓደኞቹ ጋር በደቡባዊ ምሥራቅ ጀርመን ከተደረገ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ስብሰባ እየተመለሰ ሲሆን እዚያም የይሖዋ ምሥክሮችን አግኝቶ ነበር።
አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ ለመስጠትም ጭምር ተነሳስተዋል። በቫንገሮገ ደሴት፣ አንድ የፖሊስ መኮንን ወደ ምሥክሮቹ ቀርቦ ጽሑፋቸውን ለብዙ ሰዎች ማድረስ የሚችሉበትን መንገድ በደግነት ጠቁሟቸዋል። በቫረን አን ደር ሚዩሪትስ፣ አንድ የጉብኝት ጀልባ ካፕቴን ተሳፋሪዎቹን አስደሳች የሆኑ አንዳንድ ቦታዎችን እያሳያቸው ነበር። ከዚያም በወደቡ አጠገብ ወዳለው የጽሑፍ ጋሪ ሲደርስ “እዚህ ደግሞ ስለ አምላክ መማር ትችላላችሁ” አላቸው። ለመዝናናት ከመጡት ሰዎች መካከል አብዛኞች ወደ ጋሪው በመምጣት በጋሪው ላይ የተለጠፈውን ፖስተር ያነብቡ ነበር።
ቀጥሎ የተዘረዘሩት ሦስት ብሮሹሮች ለመዝናናት የመጡትን ሰዎችም ሆነ የአካባቢውን ነዋሪዎች ትኩረት ስበዋል፦
አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? አንድ ጎብኚ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ጥያቄ ለረጅም ጊዜ ራሴን ስጠይቅ ኖሬያለሁ። ይኸው አሁን በእረፍት ጊዜዬ ስለዚህ ጉዳይ የማነብበት አጋጣሚ አግኝቻለሁ።”
ከአምላክ የተላከ ምሥራች! አንድ አረጋዊ ሰው በሃይማኖት ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ለይሖዋ ምሥክሮቹ ነገሯቸው። እነሱም ሰዎች ለችግሮቻችን መፍትሔ ማምጣት እንደማይችሉና ይህን ማድረግ የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ረዷቸው። ሰውየውም ብሮሹሩን በደስታ የተቀበሉ ሲሆን እንደሚያነቡትም ቃል ገብተዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ መማሪያዬ። አንድ አባት፣ ለትናንሽ ልጆች ታስቦ የተዘጋጀውን ይህን ብሮሹር ትንሽ የሆነችው ሴት ልጁ እንድትወስድ ፈቀደላት። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተሰኘውን መጽሐፍ የወሰደ ሲሆን “ይህ ለቤተሰቤ ይጠቅማል” ብሏል።
በጽሑፍ ጋሪዎቹ አካባቢ የሚያልፉ ሰዎች ከ3,600 በላይ ጽሑፎችን ወስደዋል። አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸው እንዲመጡና ከእነሱ ጋር ቀጣይ ውይይት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በሥራው ላይ የተካፈሉት የይሖዋ ምሥክሮችም በዚያ ባሳለፉት ጊዜ ተደስተዋል። ጆርጅ እና ሚስቱ ማሪና በባልቲክ ባሕር አቅራቢያ ወደሚገኝ አንድ አካባቢ ተጉዘው ነበር። እንዲህ ብለዋል፦ “ያሳለፍነው ጊዜ ልዩ ስጦታ ነበር። የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች በማየት ተደስተናል፤ እግረ መንገዳችንንም ስለ እሱ ለሌሎች መናገር ችለናል።” የ17 ዓመት ልጅ የሆነው ሉቃስ “በጣም ወድጄዋለሁ! ደስታ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጠቃሚ ነገር መስጠት ችያለሁ” ብሏል።