JW.ORGን ለማስተዋወቅ የተደረገ ዓለም አቀፍ ዘመቻ
ነሐሴ 2014 ላይ የይሖዋ ምሥክሮች jw.org የተባለውን ድረ ገጽ የሚያስተዋውቅ ትራክት በዓለም ዙሪያ አሰራጭተዋል። በመሆኑም በዚህ ወር ይህን ድረ ገጽ የቃኙ ሰዎች ቁጥር ከ20 በመቶ በላይ ጨምሯል፤ ይህም ሲባል ወደ 65 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ድረ ገጹን ቃኝተዋል ማለት ነው። በዓለም ዙሪያ 10,000 የሚያህሉ ሰዎች በድረ ገጹ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለመማር ጥያቄ አቅርበዋል፤ ይህም ካለፈው ወር 67 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል! ዘመቻው በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች ጠቃሚ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በአእምሯቸው ውስጥ ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የሚሹ ሰዎችን መርዳት
በካናዳ የምትገኝ አንዲት የይሖዋ ምሥክር በአሳንሰር (ሊፍት) ውስጥ ያገኘቻትን ማደሊን የተባለች ሴት ሰላም ካለቻት በኋላ በዘመቻ የሚሰራጨውን በአእምሯችን ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው? የሚለውን ትራክት አሳየቻት። ማደሊንም ማታ የቤቷ ሰገነት ላይ ሆና እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንድትችል እንዲረዳት ለአምላክ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቅርባ እንደነበረ ነገረቻት። ይህች ሴት ቀደም ሲል ወደ ተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች ደውላ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምሯት ጥያቄ አቅርባ ነበር፤ ይሁንና ከየትኛውም ቤተ ክርስቲያን መልስ አላገኘችም። ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን መማር ጀመረች።
መጽሐፍ ቅዱስን አንብበው የማያውቁ ሰዎችን መርዳት
በፊሊፒንስ የምትገኝ ሮዊነ የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር በአንድ ምግብ ቤት ፊት ለፊት ቆሞ የነበረን አንድ ቻይናዊ አነጋገረች። ትራክቱን ከሰጠችው በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን በነፃ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያስተምሩ ነገረችው።
ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስ አይቶ እንኳ እንደማያውቅ ነገራት። ከዚያ በኋላ ያደረጉት ውይይት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ትልቅ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ አነሳሳው። በስብሰባው ላይ ከተገኘ በኋላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት እንዳደረበትና መጽሐፍ ቅዱሱን ከድረ ገጻችን ላይ ለማውረድ እንዳሰበ ተናግሯል።
መስማት የማይችሉ ሰዎችን መርዳት
በስፔን የሚኖር ጊዬርሞ የሚባል መስማት የተሳነው የይሖዋ ምሥክር እንደ እሱ መስማት ከተሳነው ሆርሄ ከሚባል የቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኛው ጋር ተገናኘ። ሆርሄ በቅርቡ እናቱን በሞት እንዳጣና በዚህም ምክንያት በአእምሮው ውስጥ በርካታ ጥርጣሬዎችና ጥያቄዎች እንደተፈጠሩበት ነገረው። ጊዬርሞ የዘመቻውን ትራክት ከሰጠው በኋላ ለበርካታ ጥያቄዎቹ መልስ ሊሰጡት የሚችሉ በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ መረጃዎችን ከjw.org እንዴት ማግኘት እንደሚችል አብራራለት። በተጨማሪም በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ጋበዘው። ሆርሄ በስብሰባ ላይ የተገኘ ሲሆን ቤቱ ከአዳራሹ 60 ኪሎ ሜትር የሚርቅ ቢሆንም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከስብሰባ ቀርቶ አያውቅም።
ርቆ በሚገኝ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን መርዳት
በግሪንላንድ፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አውጥተው በአንዲት አነስተኛ ጀልባ 280 ሰዎች ወደሚኖሩበት አንድ መንደር ተጓዙ። ጉዞው ስድስት ሰዓት የሚወስድ ነበር። እዚያ ምሥራቹን የሰበኩ ከመሆኑም ሌላ ትራክቶችን አሰራጩ፤ እንዲሁም ስለ jw.org የሚናገረውን ቪዲዮ በግሪንላንድ ቋንቋ አሳዩ። በተጨማሪም እዚያ ያገኟቸውን አንድ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማር ጀመሩ። በአሁኑ ጊዜ በስልክ አማካኝነት በሳምንት ሁለት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን እያስተማሯቸው ነው።
እንዲህ ያለው ጥረት የተደረገው በሰሜን ዋልታ አካባቢ በምትገኘው በግሪንላንድ ብቻ አይደለም። በኒካራጉዋ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ትራክቱን በካሪቢያን ደን ውስጥ ለሚኖሩ የማያንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች አሰራጭተዋል። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች መጀመሪያ አንድ አሮጌ አውቶቡስ ተሳፍረው በተቆፋፈረ መንገድ ላይ ያለምንም እረፍት ለ20 ሰዓታት ጉዞ አደረጉ። ከዚያም የማያንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወደሚኖሩበት መንደር ለመድረስ በእግራቸው 11 ሰዓት ተጓዙ፤ አንዳንድ ጊዜ ማጥ የበዛበት ጭቃ ያጋጥማቸው ነበር። እዚያ ከደረሱ በኋላ ትራክቶችን ያሰራጩ ከመሆኑም በላይ በማያንኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን አሳይተዋል። ይህ ሁኔታ የአካባቢውን ነዋሪዎች በጣም ያስገረማቸው ከመሆኑም ሌላ አስደስቷቸዋል።
በብራዚል የምትኖር ኤስቴላ የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር በአማዞን ደን ውስጥ አንዲትን አነስተኛ ከተማ አቋርጦ ይጓዝ ለነበረ አንድ ሰው ትራክቱን አበረከተችለት። ሰውየው ብዙም ፍላጎት ስላልነበረው ትራክቱን አጣጥፎ ኪሱ ከተተው። ቤቱ ከመድረሱ በፊት የጀልባው ሞተር ስለተበላሸበት ጉዞውን ለማቆም ተገደደ። የሚረዱት ሰዎች እስኪደርሱለት ድረስ ትራክቱን አነበበ። ከዚያም ሞባይል ስልኩን ተጠቅሞ jw.orgን በመክፈት የተለያዩ ርዕሶችን ያነበበ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ቪዲዮዎችን አወረደ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሰውየው ከኤስቴላ ባለቤት ጋር የተገናኘ ሲሆን ትራክቱን ስለሰጠችው ኤስቴላን እንዲያመሰግንለት ነገረው። ሰውየው እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ጀልባዬ ወንዙ ላይ ቆማ በነበረበት ጊዜ ያነበብኳቸው ርዕሶች የሚረዳኝ ጀልባ እስኪደርስልኝ ድረስ ተረጋግቼ እንድጠብቅ ረድተውኛል። ልጆቼ የካሌብን ቪዲዮዎች ወደዋቸዋል። ወደፊትም jw.orgን መጠቀሜን እቀጥላለሁ።”